>
5:13 pm - Thursday April 19, 1984

ትርጕም የሌለው ‹‹ጦርነት›› (ከይኄይስ እውነቱ)

ትርጕም የሌለው ‹‹ጦርነት››

ከይኄይስ እውነቱ


ኦሮሙማ የሚባለው እንቅስቃሴ ባጠቃላይ÷ የወያኔ ሕወሓት ወራሽ የሆነው ኦሕዴድ በተለይ÷ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማይመለከተውን፣ እነሱ ‹‹ጦርነት›› ወይም ‹‹ግጭት›› የሚሉትን ሌላ ሕዝብን ማስጨረሻ መንገድ እውን አድርገዋል፡፡ የዚህ የጥፋት መንገድ ሌላው ተዋናይ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ወያኔ ሕወሓት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጽሑፎቼ እንደገለጽኹት ወያኔ፣ አስገድዶ የማይደፍራትን ኢትዮጵያ ትጥፋ የሚል ጽኑ አቋም አለው፡፡ የዐቢይና ‹ዘመዶቹም› አቋም የተለየ አይደለም፡፡ ለሥልጣን ሴሰናቸው እና ለማይጠረቃ ዝርፊያቸው ሲሉ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መሥዋዕት ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፤ ይህንንም በማያባራ ጥፋታቸው አሳይተዋል፡፡ አሁንም ቀጥለውበታል፡፡ 

ዐቢይና ድርጅቱ ስለ‹‹ጦርነቱ›› ዓላማ በካድሬአቸው ሬድዋን አማካይነት ነግረውናል፡፡ የኢትዮጵያና የሕዝቧ ህልውና ከምንጊዜውም በተለየ አደጋ ላይ የጣለውን፣ የኦሮሙማ አንድ ተዋናይ የሆነው ኦነግ እና የመንግሥትን ሥልጣን በያዘበትም ወቅት÷ አሁን ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ጉያ በመለ ተወሽቆ የባሕርይው የሆነውን አሸባሪነት እየፈጸመ ያለው ሕወሓት ወያኔ ያዘጋጁት ‹‹የደደቢት ሰነድ››ን ማስጠበቅ ነው ብለውናል፡፡ ሕውሓትም በመቃብሬ ላይ ካልሆነ አይነካም የሚለው ይህንኑ ‹ሰነድ› ነው፡፡ ስለዚህ ጸባቸው ሥልጣንና በዚህም የሚገኘው ዝርፊያ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ‹የዕዳ ደብዳቤ› የሆነ ሰነድ እንዲቀደድለት እንጂ ለአፍታም ሊጠብቀው አይፈልግም፡፡ ማነው ለመጥፊያው ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጠው? ማነው በዝኆኖች ጸብ ውስጥ ገብቶ ለማለቅ ዝግጁ የሚሆነው? እነዚህ ሁለት የጨለማ ኃይሎች ለ27 ዓመታት ባንድነት (አንዱ ጌታ ሌሎቹ ባሪያ ሆነው)፣ ላለፉት 3 ዓመታት የሚቃረብ ጊዜ ደግሞ ኦሕዴድ የተባለው ሎሌ የጌትነቱን ቦታ ይዞ ኢትዮጵያን ምድራዊ ሲዖል ያደረጉ መሆናቸውን፣ በተለይም ደግሞ አማራ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ እና በርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኞችና በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ለመናገርና ለመስማት የሚዘገንን ጭካኔ የፈጸሙና እየፈጸሙ ያሉ ሥጋ የለበሱ አጋንንት መሆናቸው ኢትዮጵያ ህልው ሆና እስካለች ድረስ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተጀመረ የተባለው ‹‹ጦርነት›› ዐቢይና ደብረ ጽዮን የሚወክሉትን ድርጅት ካልሆነ በቀር ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አይመለከትም ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ረገድ የ‹ርዕዮቱ› ወንድሜ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከ‹ጦርነቱ› ውጤቶች ኢትዮጵያዊነት ያተርፋል ወይ በሚል ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ በ8 መለኪያዎች ያቀረበውን ሐተታ በሙሉ ልቤ እስማማበታለሁ፡፡ ወንድሜ ቴዎድሮስ ያስቀመጣቸው መመዘኛዎች የሚከተሉት ናቸው ፤

1/ ‹ሕገ መንግሥት› ተብዬው ይለወጣል ወይ?

2/ የዘር መዋቅሩ በሌላ ዘመንንና ኢትዮጵያን በሚመጥን አዋሐጅ መዋቅር ይተካል ወይ?

3/ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሁሉም ኢትዮጵያ ክፍል ባለቤት ይሆናል ወይ?

4/ የአማራና የኦርቶዶክሳውያን ጭፍጨፋ ይቆማል ወይ?

5/ የአ.አ. ልዩ ጥቅም ተብዬ ይሠረዛል ወይ?

6/ በታሪካችን ላይ መግባባት ፈጥረን እውነተኛው የኢትዮጵያ የቀደመው አዋሐጅ እውነት ወደ ገዢ ሥፍራውና ርዕዮትነቱ ይመለሳል ወይ?

7/ ንጹሑ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን የጋራ መገለጫችን ሆኖ ከፍ ይላል ወይ?

8/ የባሕር በራችን ይመለሳል ወይ?

እነዚህ ስምንት ቁም ነገሮች አሁን ለተቀሰቀሰው ‹ጦርነት› መነሻም መድረሻም አይደሉም፡፡ ሁለቱም ቡድኖች እነዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውን እንዲሆኑለት ከሚመኛቸው ህልሞች በተጻራሪው የቆሙ ናቸው፡፡ ስለሆነም ‹ጦርነቱ› የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ ሕይወት መቅጠፉ፣ ሀብት ማባከኑና ማውደሙ ግን አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ አጥፊ ክስተት ውስጥ ከአንደኛው ቡድን ወግኖ መቆም ለዕብዶቹ ድንጋይ ከማቀበል ያለፈ ውጤት የለውም፡፡ የሕዝብ ድርሻ ‹ጦርነቱን› አውግዞ እላይ የተጠቀሱትን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎቶችን እውን ለማድረግ ወገቡን ታጥቆና ተደራጅቶ በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ፣ ለዚህም እንዲረዱት ቡራኬ ሰጥቶ ያሰማራቸውን ወይም በዝምታ ፈቅዶላቸው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ኃይሎችን፣ ሕወሓትን ጭምር መታገል ነው፡፡

በሌላ በኩል የአማራውና የትግራይ ማኅበረሰብ በተለይ፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ ባጠቃላይ ተጨማሪ እልቂትና ውድመት ከመከተሉ በፊት በዚህ ‹ጦርነት› ውስጥ መሳተፍ ከጠላት ኃይሎች ጋር ማበር መሆኑን በግልጽ ሊረዳ ይገባል፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብ በሕዝብ ደረጃ ጠላትነት አለመኖሩን ተረድታችሁ ለተረኞች መጠቀሚያ መሆን የለባችሁም፡፡ ከማንም በላይ የምትቀራረቡ የአንድ አገር ልጆች መሆናችሁን ለአፍታ መዘንጋት የለባችሁም፡፡ በመሠሪ ፖለቲከኞችና ካድሬዎቻቸው የፈጠራ ትርክትና የሐሰት ወሬዎች መፈታት የለባችሁም፡፡ በተለይም ወጣቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ልታደርጉ ይገባል፡፡ ሕወሓት – የኢትዮጵያና አካላችንም የሆነው የትግራይ ሕዝብ – ጠላት እንጂ ታዳጊ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ብአዴን ደግሞ ከፈጣሪው ሕወሓትም የከፋ፣ የምድር ዳርቻ ቢሄዱ የማይገኝ የዓለም ሁሉ ማፈሪያ የሆነ የሙታን ስብስብ ነው፤ የአማራው ማኅበረሰብ የምንጊዜም ደመኛ ጠላቱ ነው፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ከነዚህ ደመኛ ጠላቶቹ ጋር ነው ተደራጅቶ መፋለም የሚገባው፡፡ በየዋሕነት ሕወሓት በወረራ የወሰዳቸውን መሬቶች ማስመለሻ አጋጣሚ ነው በሚል አስተሳሰብ ከበድኑ ብአዴን ጋር ሆናችሁ ከንቱ መሥዋዕትነት እንዳትከፍሉ አደራ እላለሁ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለመንቀልም ለመትከልም፡፡ ኢትዮጵያ የጐሣ ሥርዓትን/የጐሣ ፖለቲካን፣ ለዚህም መሠረት የሆነውን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› ካስወገደች ዜጎች ያገራቸው ባለቤት የማይሆኑበት ምክንያት ስለማይኖር፣ ትግሉ በቅድሚያ የአገር ባለቤት (ባለ ሀገር) ለመሆን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን የዘር መድልዎ (አፓርታይድ) የነገሠበትን የወያኔ ፋሺዝምን እና የኦነግ (የኦሮሙማ) ናዚዝም ሥርዓትን ነቅላ ህልው ሆና እስከቀጠለች ድረስ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በኃይል የተወሰዱ ቦታዎች የትም አይሄዱም፡፡ በመደማመጥ ተወያይተን ሁላችንን በፍትሐዊነት በሚጠቅም መልኩ መፍትሄ ማበጀት ይቻለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

እነዚህ ሁለት የጥፋት ኃይሎች (ሕወሓት እና ኦሕዴድ/ኦሮሙማ) እስከነ አሸባሪ ግብረ አበሮቻቸው እየፈጸሙ ያሉት ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ፍጅቶች ሳያንስ እነሱ በፈጠሩት ‹ጦርነት› ውስጥ መማገድ ከሁለት አንዱን የጥፋት ኃይሎች የሚረዳ እንጂ አንዳንዶች ‹ተማርን› የሚሉ ጭምር እንደሚሉት የተከሰተው ሁናቴ ‹ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እንቁም› የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ይህ የስንፍና ንግግር ነው፡፡ ይህ አላዋቂነት ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት የተባለው ከማን ጋር ነው የቆመው? ለመሆኑ ዐቢይ ክተት ያለው የመከላከያ ሠራዊት ‹የአገር መከላከያ ሠራዊት› ኢትዮጵያዊ ቁመና አለው ወይ? በተለይም አመራሩ? ለዚህ ጥያቄ ማነው ርግጠኛ መልስ የሚሰጠን? ወያኔም ሆነ የእነ ዐቢይ ኦሕዴድ በዘር መሥፈርትና መዋጮ ያደራጁት ኃይል አይደለም ወይ? በውድም ሆነ በግድ ለኦሕዴድ የገበረ ኃይል አይደለም ወይ? አንዳንዱ ንጹሑን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አታሳዩኝ እያለ ሰንደቁን የያዙ ዜጎችን የሚያሳድድ መሆኑን አልታዘብንም ወይ? በደም ባጥንት የቆየ ሰንደቁን የሚጠላ የየትኛው አገር መከላከያ ኃይል ነው? የየትኛው አገር የፖሊስ ሠራዊት ኃይል ነው? ከፍ ብዬ እንደገለጽኹት ዜጎች በማንነታቸው የጅምላ ፍጀት (ጄኖሳይድ) ሲፈጸምባቸው በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ዝም ብሎ ሲመለከት፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ከአሸባሪ ኃይሎች ጋር ሲተባበር አልታዘብንም? በፈሪዎች ጭካኔ በተለያዩ የአገራችን ግዛቶች የሚያልቀው ወገኑ መሆኑን ተረድቷል ወይ? ከእንግዲህ ወዲህ ዓይናችንን ጨፍነን ‹በአገር ሉዐላዊነት› ሽፋን በደመ ነፍስ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በአስተውሎት ቆም ብለን ልናስብበት ይገባል፡፡ ሠራዊቱም እውነተኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከሆነ ውገናውን ከማን ጋር ማድረግ እንዳለበት ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜ ልንሰጠው ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የቀሰቀሱት ‹ጦርነት› የርስ በርስ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ በየትኛውም ወገን ያለ ሰላማዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰለባ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ‹ጦርነቱ› በየትኛወም ቡድን የበላይነት ቢደመደም ወይም አሸናፊ ባይኖረው፣ የአገዛዝን ሥርዓት የሚያራዝም እንጂ የአገዛዝ ሥርዓትን አያስወግድልንም፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከገቡበት ምስቅልቅል አያወጣንም፡፡ ሰቈቃውን፣ ዋይታውን፣ ልቅሶውን አይስቀርልንም፡፡ ቆም ብለን እናስተውል፡፡ በጥላቻና በቂም በቀል ተገፋፍተን ከጫንቃችን ላይ ልናወርዳቸው የሚገቡ አገዛዞችን ዕድሜ ለማራዘም ከንቱ መሥዋትነት ከመክፈል እንቆጠብ፡፡ የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም ወክላችሁ ጥፋትን የምታራግቡ ወገኖች ሁሉ በምታምኑት ፈጣሪ ወይም እምነት ከሌላችሁና ኅሊና ካላችሁ ስለ ኅሊናችሁ ብላችሁ አደብ እንድትገዙ እጠይቃችኋለሁ፡፡ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!

የኢትዮጵያ አምላክ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ክፉ የሚመኙ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን ከእግሯ በታች ፈጥኖ ያስገዛላት፡፡ ለሕዝባችን ፍቅርና መተሳሰብን ይስጥልን፡፡

Filed in: Amharic