>
5:14 pm - Tuesday April 20, 6337

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?”  ( - የመጨረሻ ክፍል - ጌታቸው ረዳ)

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” 
 የመጨረሻ ክፍል
– ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ)
«የማንበብ ችሎታ እያለው ምንም የማያነብ ሰው፥  የማንበብ ችሎታ ከሌለው ሰው እኩል ይቆጠራል!!!»
– ኑ ፡ እውነትን ፡ እናንብብ !  |  {የዕለቱ መልዕክት}
ይህን ጥናታዊ ፅሑፍ ሀገሩን ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ፣ ስህተትን ላለመደጋገም የሚሻ ትውልድ ሁሉ፣ ከታሪካዊ ስህተቱ ለመማርና ለመለወጥ የሚፈልግ ሁሉ ደጋግሞ ሊያነበው የሚገባ ፅሑፍ ነው። መልካም ንባብ።
በድጋሚ ጥብቅ ቅድመ-ንባብ ማሳሰቢያ፦
የዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅራቢ ብዙዎቻችን በቲቪ መስኮት የምናውቀው የወያኔው ጌታቸው ረዳ አይደለም። ይሄኛው የምርምር ፅሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ ሌላ የተከበረ ምሁር ነው።
/ጌታቸው ረዳ …ካለፈው የቀጠለ/
ወደ ደብተራ ፍስሃ ትረካ ልቀጥል….
“…በዛች አምባ መሽገው ብዙ “የሸዋ ሰራዊት” የገደሉት 7 የትግራይ ተዋጊዎች መከላከላቸውን ቀጠሉ። ምሽጉ በድንጋይ በደምብ የተገነባ ሆኖ ከአፋፉ ምሽግ ደጃፍ ላይ ወራሪዎቹን በዘዴ ለመሳብ ሆን ብለው ሰዎቹ አስቀድመው እህል እና ጓዝ እቃ ከምረውበታል። ሲተኰስባቸው ዝም ብለው አድፍጠው ይቆዩ እና “አማራዎቹ” እየተጠጉ እህሉን እና እቃውን ዓይተው ለመጎተት ወደ ዳገቱ ጫፍ ሲጠጉ የጥይት ዶፍ በማውረድ ከገደሉ ወደ ታች እየወደቁ ብዙ ሰው ጎዱባቸው።
“ይህ እንደሰሙ ንጉሡ ወደ ስፍራው በመሄድ ሲመለከቱት አብሯቸው የነበረ ‘ኢልግ’ የተባለ የኢስፏፀራ መድፈኛ መድፉን አነጣጥሮ ዳገቱ ላይ የተገነባው ምሽግ ላይ በመተኮስ አፈራረሰው። ከዚያ በኋላ ነፍጠኞቹ ነፍጣቸውን ወደ ታች ጣሉት።
ንጉሡም ደግ ሰው ነበሩ እና “ተው አትቶኩስባቸው” በማለት እንዳይተኩስ አገዱት።
“ከዚያ በኋላ ንጉሡ 7ቱ ታጣቂዎች በራሳቸው መታጠቃቸው ብዙ አዘኑ። ወዲያውኑ ከአካባቢው ዙርያ ከመሸጉ ባንደኛው አምባ ላይ አስተማማኝ ቦታ ላይ ሆኖ ወደ ታች ሜዳ ድምፁን ከፍ አድርጎ አንድ የትግሬ ሰው ንጉሡን እንዲህ አላቸው፦
“አንተ ሸዌ እንተዋወቃለን እኮ! የማንተዋወቅ እንዳይመስልህ።
አሁንም አንላቀቅም። ዮሐንስ ቢሞት እኛ ወጣት ልጆቹ የሞትን
እንዳይመስልህ! አላቸው።”  /- ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊ – ታሪኽ ኢትዮጵያ 1899/ፈረንጅ ዘመን፤ የእጅ ፅሑፍ፤ ናፖሊ/ኢታሊያ)፤ ገፅ ፻፴፱-፻፵-(139-140) ፤ ትርጉም (የራሴ) ጌታቸው ረዳ::
ከዚህ ፓተርን/አነጋገር/ቅሬታ/ቁጭት ወይንም ዛቻ “ለእነ መለስ ዜናዊ እና መሰሎቹ” ምን የባሕሪ ለውጥ እና ግንዛቤ እንዳስተላለፈባቸው ግንዛቤ መውሰድ የናንተ ይሆናል። በእኔ በኩል የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ የሚለውን ለማመላከት መነሻ መጋረጃውን ከምንጩ ገልጬ እንድታዩት አድርጌአለሁ።
ሃታተየን በዚህ መደምደሚያ ላጠቃልለው።
ወያኔዎች ወደ በረሃ ከወጡ በኋላም ሁላችሁም እንደምታውቁት ለማመጻቸው መነሻ ያደረጉት እና በይፋ በጽሁፍ የገለጹት ዋናው ምክንያታቸውም የሚከተለው እንደነበር ታስታውሳላችሁ።
የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ የካቲት ወር 1968 ዓ.ም. ገጽ 15-16 እጠቅሳለሁ፦
“የትግራይ ህዝብ ለረዢም ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጐ ሲጠላ እና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲደረግበት ቆይቷል። ይህ በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ የመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ ስትሰራበት የቆየች ሲሆን… የ ፫ሺ ዓመታት የሚያኮራ ታሪክና ባህላችን መመኪያቸውና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል። ይህ የታሪክ ስርቆት በአንድ በኩል የአማራው ብሔር መፎከሪያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይ ህዝብ ‘ታሪክ እንደሌለው’ ህዝብ እንዲያስቆጥረው የተደረገ የመንግሥት መመሪያ ነው። የትግራይ ሕዝብ ክብሩና መብቱ እስኪመለስለት ድረስ ትግሉ አያቋርጥም። ጨቋኝዋ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋ እስካላቆመች ድረስ ሕብረተሰብዓዊ ዕረፍት አታገኝም።” (ምንጭ:- የወያኔ ገበና ማህደር፤ ገጽ 21፤ ደራሲ – ጌታቸው ረዳ)።
ከላይ እንደተመለከታችሁት ለትግራይ ሕዝብ በባሕል፤ በታሪክ ባለቤትነት፤ በምጣኔ ሃብት እና ስነ መንግሥታዊ አስተዳደር እየተዳከመ መምጣት ወይንም የተጠቀሱ እሴቶች “ባለቤትነት መነጠቅ” ምክንያት “ጨቋኝዋ የአማራ-ብሔር” እንደሆነች ወያኔ በማያሻማ አገላለጽ አስቀምጦታል።
ለዚህም ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ዋነኛ ጠላት አድርጎ መመልክት ያለበት “አማራ” እንደሆነ ካስቀመጠ ላይቀር የአማራው ህልውና ክር እና ድሩ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ስለሚያምን ኢላማ ውስጥ በማስገባት “ኢትዮጵያን” በጠላቻ እይታ መነፅሩ ክብ ወግቷታል።
“የአማራ ጥላቻው ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞታል” ስል ምን ማለቴ ነው? ወደ ዋናው ማኒፌስቷቸው ስንመለከት አሁንም የሚጦቁመው ‘ጨቋኝዋ ብሔር” (አማራ) ኢትዮጵያ የምትባል አገር የተፈጠረቺው “በጨቋኝዋ ብሔር በአማራው፤ በተለይም በሸዋው አማራ በምኒልክ” እንደሆነ አስቀምጦታል።
ሰለዚህ ኢትዮጵያን የፈጠረ ምኒሊክ “አማራው እና የአማራ ወታደር” የትግራይ ጠላት ስለሆነ የፈጠራት ኢትዮጵያም ከአማራው ባሕል፤ ከአማራው ታሪክ (ምንም እንኳ አማራው የራሱ ታሪክም ባሕልም ስለሌለው ከትግራይ “የተሰረቀ” ባሕልና ታሪክ እያራመደ ነው ብሎ ቢወነጅለውም) በአአጠቃላይ ከአማራው ጋር በመያያዙ “ኢትዮጵያ” የምትባል “የጨቋኝዋ ብሔር” (የአማራው) አገር ስለሆነች፤ የወያኔ ላዕላይ ግቡ የትግራይ ሕዝብ ከጠላቱ እና ከጨቋኝዋ ብሔር/አገር ለመነጠል “አብዮታዊ ትግል” (ወያኔያዊ ትግል) በማካሄድ “…ከባላባታዊ ስርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ነፃ የሆነ” “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም” እንደሆነ በ1968 ያሰራጨው ጽሑፍ አረጋግጦልናል።
ስለዚህም የትግራይ ብሔረተኞች ለአማራ ጥላቻቸው መነሾው ከላይ በ“ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” በግልጽ እንደተቀመጠው አብዛኛዎቹ የትግራይ ብሔረተኞች ነባር እና ወጣት ምሁራን ከዚህ የህወሓት ቅስቀሳ እና እንደዚሁም ከድሮ ከመሳፍንቶች እና በትዕቢት የተወጠሩ የአካባቢው ባላባቶች ሲያንጸባርቁት የነበረው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ፤ ንጉሳችን ቢሞት “እኛ ልጆቹ” አልሞትንም፤ “እንተያያለን” የሚለው በዘመነ ምኒልክ ትግራይ ውስጥ ሲያስተጋቡት የነበረውን የወቅቱ የገጠር ጐሰኛ ወጣት ብሔረተኞች ፉከራ ከስንት አመት በሗላ “በዝግታ ሲከማች ከነበረው የቂም ግምጃ ቤት” በ1935 እና በ1967 ዓ.ም ይፋ ሆኖ “ንጉሳችን ቢሞት እኛ ልጆቹ አልሞትንም” የሚለው “ጸረ አማራ” (“ጸረ ሸዋ”) ጥላቻ የመነጨበት መነሻው ይህ ነው።
“በይኩኖ አምላክ፤ በዘርዓ ያዕቆብ እና ከዚያም አማራዎች ወይንም የአማራ ንጉሦች ብለው በሚጠሯቸው በምኒልክ እና ሃይለስላሴ የተፈጠረቺው ኢትዮጵያ የምትባል አገር” ትግሬዎችን በድላለች በማለት ይህ መጠኑ ያለፈ የትግሬ ብሄረተኞች በአማራ ሕብረተሰብ ህልውና እና ቋንቋው ላይ ጥላቻቸው አስተጋብተውበታል። መረን ያለፈ ጥላቻቸው ለማረጋገጥ ሲሉ “ትምህርት ቤት ውስጥ በአማርኛ መናገር እና ድንጋይ መወርወር የተከለከለ ነው” ሲሉ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ አውጇል።
ዛሬ የትግራይ ምሁራን እነ ፍስሃ ሀብተጽዮን እና እነ ዶ/ር አለምሰገድ አባይ እና ብዙዎቹ የመሳሰሉት “አማርኛን ከብሔራዊ ቋንቋነት ለማስወገድ” በእንግሊዝኛ መተካት አለበት እያሉ ይሟገታሉ። “Tigrayan Modern Elites and their bizarre Love for Colonial Language” በሚል መልስ የጻፍኩትን ብታነቡ ለአማርኛ ቋንቋ ሳይቀር ጥላቻቸው ምን ያህል መስመር እንደዘለለ መመልከት ትችላላችሁ።
ዛሬ ስልጣን ከተቆጣጠሩ ከ1983 ዓ.ም በሗላም በሽግግሩ መንግሥት ወቅት አብረውት ሥልጣኑን ከተቀራመቱት የጐሳ ቡድኖች ጋር ተረባርበው በአማራው ሕብረተሰብና “አማራዎች የፈጠሯት ሰንደቃላማ” በሚሏት አርማችን ላይ ያደረሱት የጥቃት ርብርቦሽ ስናጤን “ጨቋኟ የአማራ ብሔር ሕብረተሰባዊ ሰላም አታገኝም” በማለት በማንፌስቷቸው የዘረጉትን ዛቻ እና ቂም በቀል ስንመረምረው፤ ምንጩ ከላይ በመረጃ ያስቀመጥኩት መነሻ አድርገው ነው።
በኔ በኩል ዋቢ አድረጌ ያቀረብኩት ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነ፤ በብዛት ለሕዝብ ያልተሰራጨ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1891 በእጅ ጽሑፍ የተጻፈ ጣሊያን አገር የተገኘ የትግርኛ መጽሐፍ እና ሌሎች መረጃዎችን ዋቢ አድርጌ ያቀረብኩትን የትግራይ ብሔረተኞች ለአማራ ያላቸው ትምክሕተኛ የጥላቻ መነሻቸው አንድታውቁት አድርጌአለሁ። ማስረጃውየን የመቀበል እና ያለመቀበል ግን የናንተ ድርሻ ነው። በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ ብሎግ አዘጋጅ) getachre@aol.com
———0—————–
(ሙሉ ጥናታዊ ጽሑፉን በpdf  ከዚህ ላይ ያንብቡ)
ምንጭ  ወ ምስጋና ፦
ይህ የጥናታዊ ጽሑፍ በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ነው። ለሀቅ አንገቴን እሰጣለሁ ብለህ የቆምክ፥ አንተ ታላቅ የሀገሬ ምሁር፥ አንተ ኦሪጂናሉ ጌታቸው ረዳ፦ በአክብሮትና ምስጋና ከፊትህ ዝቅ ብዬ እጅ ነሳሁ! አሰፋ ሃይሉ
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ።
መልካም ጊዜ።
Filed in: Amharic