>

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት - (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤


ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት

ደራሲ፡ ጌቱ ሙጨየታተመበት ዓመት፡ 2011
የገፅ ብዛት፡ 200

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋና
ስነፅሁፍ ትም/ት ክፍል መምህር

ክፍል አንድ

ይህ የመፅሃፍ ዳሰሳ ከደራሲው አቀራረብ   ተለየ ደርዝ በአራት ተከታታይ ክፍል የቀረበ ሲሆን መፅሐፉ ተቀዳሚ ትኩረቱ ባደረገባቸው አበይት ተዋናዮች አባ ጃዊና አባ ድፈን ላይ ነው፡፡ የአርበኘጰቹን ማንነትና መልካም ስራዎቹ፣ የትግል ጅማሮ መነሻ ጊዜና ምክኒያቶች፣ ትግሉን እንዲገፋበት ያደረጉ ሰበቦችና አጋጣሚዎች ከዋነኛው የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄና የሐምሌ 05/2008 ዓ.ም ትግል ጋር አሰናስኖ ይተርካል፡፡ በተጨማሪም በዕድሜ ትናንሾቹ ነገርግን በስም፣ በገቢርና በተጋድሏቸው ከደጀን ተራራ የገዘፈ ታሪክና ስብዕናን የታደሉ ስድስት ጎበዛዝት አርበኞች (ሙሐቤ በለጠ፣ ሰጠኝ ባብል፣ ደሳለኝ አዱኛ፣ ሞላጃው ሙላው፣ ቃቁ አወቀና አወቀ አታክልት) በአጭሩ ታሪካቸውን ያወሳል፡፡

የመፅሃፉም ሆነ የዚህ አጭር ፅሁፍ አፅመ ታሪክ በዚች ቃለመሃላ ላይ ያጠነጥናል፤

“ሳንጃ ኪዳነ ምህረት ትታዘባችሁ! የሰጠኝ ባብል አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋችሁ! አበራ ጊዎርጊስ ይታዘባችሁ! የሲሳይ ታከለ አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋችሁ! እነሆ ሰጠኝ በሚያምናት ኪዳነ ምህረት ቅጥር ግቢ ከመቃብሩ ግርጌ አይኑ ሳይፈስ፣ አካሉ ሳይፈርስ፣ በመሃላ ተሳስረን መስቀለ ክርስቶስ መትተን፣ የሞተለትን ዓላማ ከግብ ሳናደርስ ወደ ቤታችን ላንመለስ ቃል ገብተናልና ትግላችን ይቀጥል! ልቦናችን ከሃብት ንብረታችን ይነቀል፤ እያለ ሁሉም በየሸንተረሩ መሰሉን ሰብስቦ ወደ ትግሉ ክተት እንዲል ታወጀ፡፡”

አርበኛ አባ ጃዊ ጎቤ መልኬ ማነው;

ጥቅምት 20/1958 ዓ.ም ወደዚች ዓለም የተቀላቀው ብላቴና የዚህ ድርሳን ዋና ትኩረትና የዘመኑ ለውጥ አብዮተኛና አርበኛ ነው፡፡ በሙሉ ስሙ ጎቤ መልኬ ተገኘ አልያም በቅጽል ስሙ ዋዋ በትግል ወይም የአርበኝነት ስሙ ደግሞ አባ ጃዊ በመባል ይታወቃል፡፡ የትውልድ ቀየውም በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ጎንደር ክፍለ ሐገር ዳባት አውራጃ ጠገዴ ወረዳ አዴት ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ የአርበኝነት መነሻ የዘር ሃረጉ ከነፃነት አርበኛዎቹ እነ መንገሻ ወንዳፍራሽ መመዘዙና በነዚያ ወረራ ዘመናት የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ ወገባቸውን ታጥቀው ከጠላት ጋር ይፋለሙ የነበሩትን የጎንደርና አካባቢዋ አርበኞች እንደነ ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንን ያሉትን ጀግንነትና ተጋድሎ ሲመለከት ማደጉ ነበር፡፡ አባቱ አቶ መልኬ ተገኘም ባለጠጋና ደግነትን የተሞሉ ሰው ነበሩ፤ ነገርግን ወታደራዊው ደርግ ዘርግነዳቸውን ቆጥሮ ፊውዳል እያለ ስቃይና መከራ ቢያፀናባቸው ግዜ ይህን የእኛውን ዘመን ጀግና ሰው ጎቤን ጨምሮ ለልጆቻቸው ሁሉ ደግንትንና መልካም ስብዕናን አውርሰዋቸው አለፉ፡፡ በዚህ ምልካም አስተዳደግ ታንፆ ያደገው አባ ጃዊ ታዲያ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ፣ ትልቅ ትንሽ ሳይል ሰው አክባሪ፣ ድሃ ወዳድ ሃገሩን አፍቃሪ፣ ባለጠግነቱን ለሃገር ዕድገትና ለመልካም ነገሮች የሚያውል ምስጉን ሰው ነበር፡፡ ይህም ደግነቱ ሃብትን በሃብት ላይ እንዲጨምር ያደረገው፣ መንግስት ጋርም ተቀራርቦ ይሰራ ዘንድ የረዳው ቢሆንም ዘመኑ የወለዳቸው የአባቱን መሰል ባላንጣዎች ተነሱበት፤ እናም በ2005 ሳንጃ ከተማን ለቆ የዞኑ ርዕሰ መዲና ጎንደር ከተመ፤ ሆኖም መለስ ቀለስ እያለም ከግብርና ሙያው ዱካ ስር አልጠፋም፡፡ በመልካም ስራዎቹ የሚታወቀው ከመንግስት አካላት ሳይቀር የምስጋናና አድናቆት ምስክርነት የተቸረው አባ ጃዊ ከበርካታ አስተዋፅዎቹ መካከል የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፤
• በትውልድ ቀየው ስሙ በከፍታ ከሚወሳበት አራሽ አንደፋራሽ የግብርና ሰውነቱ ባሻገር መንደሩን ከሌላ መንደር የሚያገናኝ 21 ኪሜ መንገድ ስራ በራሱ ወጭ ማሰራቱ፤
• ከሳንጃ ቅራቅር የሚገናኝ የ48 ኪሜ ጥርጊያ መንገድ የግል የቅየሳ ልምዱንና ሙሉ አቅርቦቶችን በማበርከት መንገድ ቅየሳ ጠረጋና ልማት ስራ መስራት፤• በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠሩ ማንኛውንም አይነት ግጭቶች በመፍታት ደም በማድረቅ፣ ሽምግልናዎችን በማስተባበርና በመምራት ቀዳሚ ተዋናይና መፍትሄ ሰው መሆኑ፤
• በአካባቢው ወላዶች አምቡላንስ ችግር በግል ተሸከርካሪዎቹ አገልግሎት በመስጠት የዝናቶች እንግልት፣ ሞትና የሕፃናት ጤንነት ላይ ጉልህ ሚና መወጣቱ፤
• ዘመድ ከባዕድ ሳይለይ ተቸገርኩ ላለው ሁሉ ፈጥኖ የሚደርስ፣ ዕምባና ብሶት አባሽ፣ የድሆች መከታ፣ ከገንዘቡ ቀንሶ ጎጆ አስቀላሽና ጥሪት አስያዥ ደግ አባት መሆኑ፤
• ማህበራዊ ሕይወቱ ገደብ የለሽለቱ፤ ደስ ባለው ወቅት ከሰንጋው ከመጠጡ አሰናድቶ ጋባዥ፤ ከወጣቱ ጋር እንደ ወጣት፣ ከአዛውንቱ ጋር እንደ አዛውንት ሆኖ ነዋሪነቱ በከፋ ወቅትም መሳርያ አስታጥቆ ታጋይነቱ፤
• እልፍ ሲልም በእንግድነቱ / በባይተዋርነት በቀየው አቅራቢያ ካምፕ ውስጥ የተቀመጡ ወታደሮች ሳይቀሩ በዓልን ፍሪዳ ጥሎ መጠጥ አቅርቦ በፈቃዳቸው በደስታ እንዲያከብሩ በማድረግ ይታወቃል፤ ይህ ደግነት የተደረገለት ሰራዊትም አባ ጃዊ አረሞ ደረሰበት፤ አቸዳ (አዝመራ ስብሰባ) ወቅት ነው ከተባለ ሳያመነቱ ከተፍ የሚሉለት ደግ ሰው ነበር፡፡
በጠቅላላው ለዕውነት እንጅ ማበል ብሎ ነገር ያልፈጠረለት አባ ጃዊ በሃቅ ኑሮ ሕይወቱን ያሸነፈ ሃብታም ገበሬ፤ ልበ ብርሃን፣ ባለምጡቅ አዕምሮና ክንደ ብርቱ ሰው ነበር፡፡

የጎቤ መልኬ ትግል ጅማሮ መቼና ለምን;

ሕዋሃት መራሹ መንግስት ሃገር በተቆጣጠረ በማግስቱ በ1984ዓ.ም በጎቤ የመኖሪያ አቅራቢያ የወሰን ማካለል ስራ አካሄደ፤ በዚህም ወቅት ቀድሞ በአማራ ክልል ስር እንደነበረ የሚታወቀውን ማክሰኞ ገበያ የተባለ ቦታ ከተማ ንጉስ የሚል ስያሜ በመስጠት መርዞ የተሰኘ ክፍለ ሕዝብ ሾመው ግብር በዚያ ብቻ ይፈፅሙ ዘንድ ማስገደድ መጀመር፤ ሌላኛውን ቦታ ደግሞ ቅራቅር በማለት ሰይመው በክልል ሶስት ስር ሐይሌ የተባለ ክፍለ ህዝብ ሾመው ስራቸውን ሲጀምሩ ነገሩ ያላማራቸው የግጨውና አካባቢ 42 ጭስ እያንዳንዳች 20 ብር በድምሩ 840 ብር አዋጥተው ሶስት ሽማግሌዎችን ልከው ለክልላቸው ግብር በመክፈል የወደፊት መራጃቸውን ይይዛሉ፡፡ ይህ የተመለከቱ የአገዛዙ ሰዎች በሽማግሌዎች ላይ ዕስራትና ማዋረድ ያደርሱባቸዋል፤ ግብሩ የሚገባው ወደ ፌደራል መንግስት ነው፤ በመባል ገንዘብ ተነጥቀው ሽመግሌዎቹ ተዋርደው የተመለሱበት የግጨውና አካባቢ ነዋሪ ስለወደፊት ዕጣው በአንድ ቃል መከረ ዘከረ፡፡ ከ1987 ዓም ጀምሮ እየተባባሰና እየከፋ የመጣውን ዕሥራትና እንግልት የተመለከቱ 15 የሚደርሱ የአካባቢው ወጣቶች ነፍጥ አንስተው ተደራጅተው መታወቂያ ይሰጠን ሲሉ ለሳንጃ ወረዳ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ በወቅቱ አስተዳዳሪ በነበሩ ሰው አማካኝነት ታቅዶበት ጥያቄያቸው እንዲዘገይና መልስ እንዳያገኝ ሲደረግ የሳንጃ አስተዳዳሪ፣ የአማራ ቅረቅር ወረዳ አስተዳዳሪ ነኝ ባይና የዳንሻ ክፍለ ሕዝብ መክረው የሕዝቡን ጥያቄ ወደ ጎን ተውት ይባስ ብለውም ግጨው ወደ ክልል አንድ መካለሉን ለህዝቡ ይፋ አደረጉ፤ ህዝቡ ቅሬታውን ሲያሰማም እኛ የመሬት ችግር የለብንም ከፈጋችሁና አማራ ነን ምትሉ ከሆነ ሰሮቃና እርጎየ ሄዳችሁ መኖር ትችላላችሁ ሲሉ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ነገሩ ስር የሰደደ መሆኑን የተረዱ ትልልቅ ሰዎች በዝግታ መከሩ፤ ነገር ግን የዳንሻ አስተዳዳሪ ከመንግስትና ክልል አንድ ልዩ ሃይል ጋር በመሆን በግጨው አካባቢ ታጣቂዎች ላይ መሳሪያ መንጠቅ ብሎም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ማፈንና ማጋዝ ጀመረ፡፡ በወቅቱም በስልጠና ሰበብ መሳሪያዎቻቸውን ከተነጠቁት መካከል የጎቤ ሰዎች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ሐዋሃት ለግጨውና ወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች ማማለያ አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ፤ ትምህርት ቤት፣ ጤና ስርጭት፣ ብድር ይነጉድ ጀመር፤ በ2001 ዓም በግጨው ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ሳሉ ከሶሮቃና እርጎየ በተነሱ ወጣቶች በመቶ አለቃ ደጀኔ ማሩ ፊታውራሪነት ሕውሃት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የመሰረት ድንጋዩ እንዲነሳና ጅምር ስራዎችም እንዲወድሙ ተደረገ፡፡ ጉዳዩ በይደር 2002 ዓም ደረሰ፤ ወደ ከፋም ችግር ተሸጋገረ፤ ሌላ የይገባኛል ጥያቄ በማይምቧና ስላንዴ አካባቢዎች በመቅረቡ ሳቢያ ግጭት ተፈጠረ፤ ሞትም ተስተናገደ፤ ይህም የአካባቢውን ህዝብ የተባበረ ክንዱን ለማሳየት ወደ ፍልሚያ ቦታ ተመመ፡፡ ይህን ተከትሎ ነበር ይህ የቁርጥ ቀን ልጅ አባ ጃዊ ጎቤ መልኬ ትግሉን ይቀላቀል ዘንድ ግድ ያለው፡፡

መጀመሪያ በባለጠግነቱ ትግሉን ቀለብ በመስፈርና ስንቅ በመቋጠር፣ መጓጓዥያ መኪናዎችን በማቅረብ፣ የውጊያ ስልት በመንደፍ፣ ሰልጠናዎችን በመስጠት፣ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ በማስተባበር፣ ብሎም ለክፉ ቀን ያላትን መሳሪያና ጥይት በማስታጠቅ ጉልህ ተሳትፎ አደረገ፡፡

ከጎቤ ጥሪ የደረሰው ሁሉ ከአራቱም አቅጣጫ ከአርማጭሆ፣ ከበለሳ፣ እንቃሽ፣ ከወገራ፣ አብርሃጅራ፣ ቆላ ወገራ ብሎም መላው ጎንደር ክተት አለ፤ እግሩ ቦታዋን እንደረገጠ ወራሪው ሃይል እግሬ እውጭኝ ብሎ ተከዜን ተሻገረ፡፡ ሲፈጅ በማንኪያ፤ ሲበርድ በእጄ ይሉት ፈሊጥ የለመደውና ሲያሻው መደዴ ህገ ወጥ ቀማኛ፤ ሌላ ግዜ ሕጋዊ መንግስት የሚሆነው የወንበዴ ቡድን ሽምግልናንና የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነትን ብቸኛ አማራጩ አደረገ፡፡

ይህም ሲሆን ጎቤን ጨምሮ በርካታ ትግል መሪዎች፣ እንስት ታጋዮችና ሰንቅ አቀባዮች፣ ከዳንሻዎቹ እምቢ ባዮች ጭምር፣ ወጣቶች፣ አዛውንት አርበኞችና የመንግስት ባለስልጣናትም ተካፋዮች ነበሩ፡፡ ለዚህም ከመንግስት ካዝና ወጥቶ ለታጋዮች ይደርስ የነበረ የጦር መሳሪያና የጥይት አቅርቦት ዋና ማሳያው ነበር፡፡ በመጨረሻ የወንበዴው ቡድን መለስ ቀለስ ማለት ያናደደው አባ ጃዊ በርሱ አስተባባሪነት የሳንጃ መንገድ እንዲዘጋ አደረገ፤ በታችኛው የወንበዴው ቡድን ትግራይ ክፍል ማንኛውም አቅርቦት ቆመ፤ መንግስት ነኝ ባዩ መጥቶ ተደራድሮ በሩን አስከፈተ፤ ወንበዴው ቡድንም ጉዳዩን በዚህ መልኩ አለሳልሶ ማቆየት ምርጫው አደረገ፡፡ ኋላም ጉዳዩ በርእሰ ብሄሮቹ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አይተ አባይ ወልዱ መሃል ሆነ፤ ውይይት ተዘጋጀ፤ ከእያንዳንዳቸው 150 በጠቅላላው 300 ያህል ሰዎች ተሳተፉ፡፡ ከአማራው በኩል በርካቶች የተሳተፉ ሲሆን አባ ጃዊ ግን ዋነኛው ነበር፡፡ ወያኔ በሰርጎ ገቦቹ አማካንነት ውይይቱን አቋረጠው፤ የሰው ብዛት ተቀንሶ ውይይት ሲዘጋጅ አባ ጃዊ መሳተፍ አልቻለም፤ ነገርግን ሰዎቹን የቁምነገር ስንቅ አስይዞ ልኮ የነበረው ጀግናው ቡድኖቹ በድል ቢቀዳጁም የአባይ ወልዱ ቡድን ግን በድርቅናው ገፋ፡፡

ነገርግን ቂሙን ቋጥሮ የቆየው የማፍያ ቡድን ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩ የአካባቢውን ሰዎች ማሳደዱን ተያያዘው፡፡ እኒህ ቂም የያዘባቸው ሰዎች በምን ሰበብ ወጥመዴ ውስጥ በገቡ ሲል ሲያውጠነጥን የከረመው የማፊያ ቡድን የቅማንትን አጀንዳ ተጠቅሞ፤ አባ ጃዊ ቅማንቶች አስረዋቸው የነበሩ ሰዎችን ለማስፈታት መንቀሳቀሱን ተከትሎ በእርሱና አጋሮቹ ደጀኔ ማሩ፣ አዋጁ አቡሃይና ሀይሌ ማሞ ላይ ማደኛ አወጣ፤ የመጨረሻ ሁለቱን ወደ ማዕከላዊ ማጋዝ ቢቻለውም የደጄኔ ማሩና አባ ጃዊን እጅ መጨበጥ ነዲድ እንደመጨበጥ ሆኖበት ሳይሞክራት ቀረ፤ የፌደራል መንግስትም ከአማራ ክልል ጋር አምጣ አታምጣ ሙግት ገጠመ፤ የሚያደርገው ቢጠፋውም ቅሉ ወደ መጨረሻዋ ሕቅታ በአብሮነት ማዝገም ጀመረ፡፡

***
በተጨማሪም በህዝቡ፣ በወገኑ፣ በትግል ጓዶቹና በቤተሰቡ ላይ የደረሱ ግፎች ያንገሸገሹት አባ ጃዊ ከተበዳይ አካባቢና ሰው ሁሉ ጎን ተሰልፎ ገፈኞችን ይሞግት፣ ይታገልና ይጥል ነበር፡፡ ወልቃይትና ሕዝቦቿም የዕርሱን አለኝታነት እንደሚሹ ቀድሞ ያወቀው ጎቤ በየመድረኩ ተገኝቶ እሰጥ አገባ ይገጥምላቸው መንግስትንም ብርክ ያሲዝላቸውና ይረታላቸው ጀመር፡፡ ከዚህ በታች በተጠቀሱ አበይት የመድረክ ንግግሮ ለምሳሌ፤ “ወልቃይትን ሲያልባችሁ ትመልሷታላችሁ!”፤ “ምነው ትግሬ እንዲህ መሬት አይንካኝ አለ!”፤ “ስለድንበር ካወራነ የሱዳን ድንበሩ ጓንግ፤ የትግሬ ወሰኑ ተከዜ ነው!” እና “ተከዜም ወንዝ ነው እንጨት አይደል አይቆረጥ፤ ድንጋይ አይደል አይፈለጥ!” ወዘተ በሚሉ የበረቱ ንግግሮቹ ጠንካራ መልዕክቶችን ያስተላለፍና የመድረኩን መጠናቀቅ ሳይጠብቅ ጥሎ ይሄድ ነበር፡፡

እናም እስከ አባቱ ወጀድ ድረስ እየተከተሉ ያሳድዱት ጀመር፤ አጅሬም ቁጣው እንደነብር ነውና ሲነሳባቸው እግሬ አውጭኝ ብለው ከሸሹ በኋላ ቄስና መነኩሴ ይዘው ዕርቅና ድርድር ይጠይቁታል፡፡ እርሱ ይቅር ለእግዜሩ ቢልም እነሱ ግን ቂማቸውን እንደቋጠሩ ቆይተው ጥቃት መሰንዘራቸውን አይቦዝኑለትም ነበር፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ውሸትን በመለዋወጥና አንዴ በጉልበት አንዴ በሽምግልና አንዳንዴ ደግሞ በህግ ሽፋን በህዝቡና በእርሱ ላይ ስቃይን ያሰፈነው መንግስት ነኝ ባይ የወንበዴ ቡድን ዕረፍት ሲነሳው ኖሮ በስተመጨረሻ ለአይን ሕመም ዳረገው፡፡ ሕክምናውንም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአይን ስፔሻሊስት አማካኝት አካሄዶ፤ በሃኪሞችና በቤተሰብ ውትወታ ቀዶ ህክምና አካሂዶ አንድ ዓይኑ ብርሃን አጣ፤ በሕክምና ሳለም የወልቃይት ኮሚቴ አባላት እነ አታላይ ዛፌ፣ ጌታቸው አደመ በሃምሌ 04/2008 ዓ.ም ውድቅት ሌሊት በቁጥጥር ስር ውለው፤ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መከበቡን የሰማው አባ ጃዊ ምንም ሳያቅማማ የተተከሉለትን የህክምና መርፌዎች ነቃቅሎ ወደ ቀበሌ 18 አመራ፤ መሳሪያውን ከቤቱ አስመጥቶ ኪኒናዎቹን በኪሱ እንደያዘ ውጊያውን ተቀላቀለ፡፡

የአባ ጃዊ ትግል መጎምራት ሰበቦችና አጋጣሚዎች

ነገሮች ባሉበት እየቀጠሉ እንዳለ በአጋጣሚ ወይም ይሁነኝ ተብሎ ታስቦበት የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ በኮሚቴ አባላቱና በተቆርቋሪ ግለሰቦች ባለቤትነት ይጧጧፍ ጀመረ፡፡ በይሁነኝ ከተደረጉት እንቅስቃሴዎች መሃል በእነ አታላይ ዛፌና ጌታቸው አደመ “በቃን!” የሚልና በእነ በሪሁን ጥሩ ተደረሱ በራሪ ፅሁፎች ሲገኙበት በአጋጣሚ ደግሞ ከሚወሱት የሕዋሃት ሰው የነበሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ የምስክርነት ቃል በኢሳት ቴሌቭዥን ይጠቀሳሉ፡፡ ወያኔም ሴራ መጠንሰሱን ተያያዘው፡፡ ነገርግን ዙሩ የከረረው የወልቃይት አማራነት ጥያቄ በነሃሴ 2007 የኮሚቴ አባል ሆኖ እንዲታገል ጥሪ የቀረበለት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በጥያቄ መቅረብ ማግስት መስማማቱን ገልፆ “የወልቃይት ጠገዴ ህዝቦች በደልና ሕገመንግስቱ ይነፃፀር!” የሚል በራሪ ፅሁፍ መበተኑ ሌላኛው ወሳኝ ርምጃ ነበር፡፡

ወያኔ ይበልጥ የዕግር እሳት እየሆነ የመጣበት ይህ ጉዳይ አርቄ ቀብሬዋለሁ ያለው ሐቅ መቃብር ፈንቅሎ፣ ግዘፍ ነስቶ መቀመጫ መቆሚያ ነሳው፡፡ ይባስ ብሎም የጎንደር ወጣቶች ጉዳያቸው አድርገው ያነሱት ይጥሉት ይዘዋል፤ ኧረ እንዲያውም ከሌሎች የሃገሪቱ ተመሳሳይ ክፍሎች ራያ፣ መተከል፣ አላማጣ፣ ቆቦና አፋር ህዝቦች ጋር ተዋጅ መቅረብ ጀምሯል፤ ነገሩ ሲጠናም የፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ፤ ወንበዴው ወኔው ይርድ ጀመረ፡፡ በዚህ መሃል ጆሮውን አቅንቶ ወያኔ ከዛሬ ነገ በአካባው ህዝብ ላይ ጦርነት አወረደ እያለ በሚጠብቅበት ሰዓት ወንበዴው የባለስልጣናት ቡድን ግን ትኩረቱን ከመላው ጎንደር አንዲት ውስን ቀበሌና አንድ ግለሰብ የኪራይ ጎጆ ላይ አደረገ፡፡ ይህም ቀበሌ 18 በመጨረሻዋ ሰዓት ትግሉን ከተቀላቀለውና የእግር እሳት ከሆነባቸው ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መኖሪያ ቤት ላይ ነበር፡፡ የዚህም ኦፕሬሽን መሪ አባይ ወልዱ፣ አሳላፊው አባይ ፀሃየ፣ የደህንነቱ ክንፍ ተጫዋች ጌታቸው አሰፋና የፊት ደጀኑ ሳሞራ የኑስ ነበሩ፡፡ እኒህ ሁሉ ከዋክብት አምባገነኖች ተቀናጅተው በማን ይደፍረናል፤ ከቶስ ማን ሊረታን ባይነት አፈና ለመፈፀም ወሰን ጥሰው ሕፃን ከሴት አሸብረው የጥይትና አረር ምክሩን እየተቀባበሉ መሃል ከተማ ደረሱ፤ ነጥብ ሊያስቆጥሩም በቀላሉ ደጅ ደረሱ፤ የኋላ ደጀኑ ብዙና ፈርጣሞች ነበሩና የድረሱልኝ ጥሪው ሲደርሳቸው እነ አባ ጃዊ፣ እነ ሰጠኝ ባብል ፈጥነው ከያሉበት አጥቂውን ከጀርባ ከበቡት ታሪክ በማይረሳው ሁኔታ ጉልበተኞች አቅርማቸው ርዶ፣ ሳይዘጋጁ የሽንፈትን ፅዋ ተጎንጭተው ተመለሱ፡፡
ከህክምና አቋርጦ የተቀላቀለው አባ ጃዊ ለክፉ ቀን ብሎ ያኖረውን ጥይት እያቀበለና እያስተባበረ፤ እነ ሰጠኝ ባብል ግዳይ እየጣሉ ሃምሌ 05/2008 ሙሉ ቀን ገትረው ዋሉ፡፡ ህመም ሳይገድበው የሃምሌ 5ቱን ፍልሚያ ቀዳሚ ተዋናይነቱን በመውሰድ የታሪክ አባል ሆነ፡፡ እናም ሕይወቱን ዘመኑን ሙሉ በትግል ያሳለፈው አባ ጃዊ የትግሉ ፍሬ መጎምራና በድል ከመንግስታዊው ወንበዴ ቡድን ጋር ተፋልሞ ጓዶቹ ድል ያደረጉባት ብሎም ለመላ ሃገሪቱ የለውጥ ማርሽ የተቀየረባትን ቅፅበት መሪ ነበር፤ እናም በዕለቱ አመሻሽ ላይ መረጃ የደረሰው አባ ጃዊ ጀንበር ሳታዘቀዝቅ ድል አድርጋሁ ውጡ ሌሊቱን የሚጨመር ሃይል እንዳለ ሰምቻለሁ ሲል አመራር ሰጠ፡፡

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋና
ስነፅሁፍ ትም/ት ክፍል መምህር  ጸሃፊውን ለማግኘትtadilafiker143@yahoo.com 

 

Filed in: Amharic