>

የዘመናዊ ፖለቲካችን ፍኖተ ካርታ !  (አንዷለም አራጌ) 

የዘመናዊ ፖለቲካችን ፍኖተ ካርታ ! 
አንዷለም አራጌ 
የኃላ ነገራችንን መተረክ ብዙም ደስታ አይሰጠኝም፡፡ ብዙዎች ብዙ ያሉበት ስለሆነ፡፡ የተለየ ምርምር ያላደረኩበትን ጉዳይ የብዙኃንን ጠቅላላ ዕውቀት መልሶ ማስተጋባት ይመስለኛል፡፡ የሚታወቀውን መድገም ደግሞ ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ ነገር ግን ቀጥታ ያለንበትን ዘመን ከመተንተን ይልቅ ከወዲያኛው ዘመን ላይ ሆኖ ወደ አሁኑ ለመመልከት ወታደራዊ ገዥ መሬትን የመቆጣጠር አይነት ስሜት ይፈጥራል፡፡
በእስር ቤት ቆይታዬ ብዙ ካሰብኩባቸውና ከፃፍኳቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡ የሀገራችንን የፖለቲካ ችግሮች በጥልቀት ለማየት ስሞክር ሁልጊዜም ስራቸው እንድ ቦታ ላይ ተደራርቦ ይታየኛል የፖለቲካ ባህላችን ላይ፡፡ በተለይ የዘመነ መሳፍንቷ ሀገራችን ኢትዮጵያ የቆመችበት የባህል ንጣፍ የተደራረበና በቀላሉ ከፖለቲካ ገፀ ምድራችን ፈንቅለን ለመጣል የሚቻል አልሆነም፡፡
ከዘመነ መሳፍንት እስካሁን የተደረጉ የለውጥ አውዶችን በቅርብ እርቀት ላይ ለመመልት ስንሞክር ስኬት አልባ የመሆናችን አንኳር ሚስጥር በዚሁ የዘመነ መሳፍንት የፖለቲካ ባህል ቅኝት ለውጥ ለማምጣት መሞከራችን ይመስለኛል፡፡ ባልተቀየረ ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ባህል ሀገር የመቀየር ትግል በማድረጋችን ይመስለኛል፡፡ ምን አልባት በእንቅርት ላይ እንዲሉ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በኋላ መሀል ሰፋሪ የተሰኘው ሃይል ያመጣው የተዛባ የፖለቲካ ባህልም በእኔ እይታ በይዘቱ ከዘመነ መሳፍንት ፖለቲካ በተወሰነ መልኩ የሚለይና የፖለቲካ ባህላችን ጤና ያወከ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ባህል የስነ ልቦናችን አዕማዶች የሚቆሙበት ንጣፍ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የፖለቲካ መስተጋብሮቻችን ውጥንቅጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መነሻው ይኸው የስነ ልቦናችን ውቅር ነው፡፡ በእርግጥ ካፈው ስህተታችን እንማራለን ስንል ያለፈውን ስህተት የማድረግ አዝማሚያ ይስተዋላልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ዘመናዊ የተሰኘው ሁሉም ዘመናዊና ለእኛ የሚጠቅም ላይሆን ይችላልና ሚዛኑን የጠበቀ ምልከታ ሊኖረን ይገባል፡፡ ይኸን ያክል ስለቀደመው ዘመን ካወሳው ከዚህ በኋላ ሊኖረን የሚገባ የፖለቲካ ባህላችን ድሮች ቢሆኑ ያልኳቸውን ጥቂት ነጥቦች እንዳነሳ ፍቀዱልኝ፡፡
፩- ከሌሎች ምን እንደጎደለ ከመጠየቃችን በፊት ከእኛ ምን እንደጎደለ መጠየቅ፡-
ለአያሌ ዘመናት የፖለቲካችንን ሰማይ በሸፈነው የፖለቲካ መስተጋብራችን በቅርብ የሚገኘና የሚታይ ማንነታችን ለመፈተሸ አቅም አግኝተን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ እራስን የመተቸት ጀግንነትም እምብዛም የምናውቀው አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ላይ አሻግረን ሁሉንም በመምረግ እራሳችን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እናስቀምጣለን፡፡ በሌላ ወገን ያለውም እንዲሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ተቀራርቦ መወያየት ከአድማስ ማዶ ይርቃል፡፡ በቃላት ከመወያየት ይልቅ በአፈ ሙዝ መወያየት ብቸኛው አማራጭ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ምን ያህል ለስልጣኔ እሩቅ መሆናችንን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሰው ሲሰለጥን የሚሰለጥነው በራሱ ላይ ነውና፡፡ በራሱ ላይ የሰለጠነ ሰው ወደ ውስጡ ያያል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ እየተወች ቢኖሩንም ቀድመን እራሳችን ከፈተሸን ያለ ብዙ ድካም ችግሮቻችንን ለመፍታት ብሎም ለመቀራረብና ለመወያየት እድል እናገኛለን፡፡ የስልጣኔ የመጨረሻው ጥግ ደግሞ በጉዳዮች ላይ በጥሞና መወያየት ይመስለኛል፡፡
፪ኛ – የተጠቂነት ስነ ልቦናን ማሸነፍ፡- እርስ በርስ የምንባላባቸው ጉዳዮች በዋናነት የተጠቂነት ስነ ልቦና ተመርኩዘው የሚነሱ ናቸው፡፡ ቀማሪዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ሲሆኑ በተጠቂነትና እራስን በመከላከል ስልት አዙሪት እንዲወድቅ ሙሾ የሚወርድለት ደግሞ ህዝቡ ነው፡፡ አገዛዝ ሁልጊዜም በእውነት ላይ አይቆምም፡፡ ያልተሰጠውን እንደተሰጠው ተጠልቶ ሳለ ብዙሃን በፍቅር እንደወደቁለት ግቡም የህዝብ ነፃነት እንደሆነ ይሰብካል፡፡ ይኸንን አስተምሮውን ተቀብሎ የማያደገድገው ሁሉ ይወገራል፤ ይገደላል፡፡ ከየትኛውም ወገን ቢሆን፡፡ ሁሉም የብሔር ነፃ አውጭ መች ግን የእኛ ከሚሉት ብሔር ይልቅ (የእነርሱ ብቻ ከሆነ) የሌላውን ወገን ሰብዓዊ ክብር መውደቅ እንዳያዩ አይናቸው ተጋርዷል፡፡ የጣር ድምፁን እንዳይሰሙ እዝነ ልቦናቸው ደንቁሯል፡፡ የሚፈላው የዘረኝነት ጥንስስሰ የእኛ ከሚኩት ዘር በላይ ሰው ላሳር ይላቸዋል፡፡ ዘረኝነት ልክፍት ሳር የሰደደ ደዌ ነው፡፡ ከበታችነት ጥልቅ ጉድጓድ የሚቀዳ ነቀርሳ ነው፣ ማንም ቢያቀነቅነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ደዌ የተፈወሰ የፖለቲካ መስተጋብር ለሁላችም መድህን ይመስለኛል፡፡
፫ኛ- ፍርሃታችን ከመኖር ህልማችንን እንኑር፡- በፖለቲካችን ውስጥ ፍርሃት ሞልቶ ተርፏል፡፡ በአገዛዝና በሕዝብ መካከል የነበረውን የነፃነት ግርዶሽ ሆኖ ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት የዘለቀው የፍርሃት ከል እየተገፈፈ ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካ ልሂቃን መሀል ያለው የፍርሃትና ያለ መተማመን ጥቁር ደመና ግን ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ይሰማኛል፡፡ ስለሌሎቹ በጎ ማሰብና እንደሚያሰቡም መገመት ሰብዓዊ እድገታችንን የሚያቀጭጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፤ እንዲያውም ጤናንም ሆነ ሰብዓዊ ልዕልናን የሚያበለጽግ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ከፍርሃት ይልቅ መተማመን ላይ ለመጀመር ዘመን እንደመጣ ይሰማኛል፡፡ መተማመን ላይ ስንሰራ የጋራ ህልሞቻችንን መኖር እንጀምራለን፡፡ ለጋራ ህልሞቻችን በጋራ ስንሰራ የማይናድ ገደል አይኖርም፡፡ ፍርሃትና አለመተማመን ላይ ቆመን አንድ አይነት ህልም አይኖረንም፡፡ ‹‹የሚጋጩ ህልሞቻችንን›› ለመፍታት የማያበራ ግጭት ውስጥ በመዝፈቅ እንቀጥላለን፡፡
፬ኛ – በተግባር ተፈትኖ የሚያልፍ የፖለቲካ እምነት ማራመድ፡- እስከዚህ ዘመን ድረስ በፖለቲካ ቤተ ሙከራዎችን የታዩ ግኝቶች ሁሉ አገዛዝ ህዝብንም ሆነ ጎሳን መሰረት ቢያደርግ እራሱን አውሎ ከማሳደር የዘለለ ርዕይ እንደሌለው ይመሰክራሉ፡፡ የአገዛዝ ልዕልና በህዝባዊ ልዕልና ሊተካ ጊዜው ደርሷል፡፡ አሁንም ግን አንድ የፖለቲካ ስንክሳር ንጋታችንን ሊያጨልም ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ በግለሰቡ ልዕልና ላይ እስካልቆመ ድረስ ምንም አይነት አማላይ ስም ብንሰጠው ዴሞክራሲ አይሆንም፡፡ ግለሰቡ ሰብዓዊ ግዴታዎችና መብቶቹ የተደራረቡበት የልዕልና ልቃቂት ነው፡፡ በትክክል የግለሰቡ መብት በሚከበርበት በየትኛውም ሁኔታ የሚጣስ ምንም አይነት መብት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ሁሉ መብቶች የሚተረተሩት ከዚሁ ከግለሰቡ የልዕልና ልቃቂት ነውና፡፡ ተፈትኖ የሚልፈው የፖለቲካ መስመርም በሀቅ የግለሰቡ መብት ላይ የሚቆም የፖለቲካ ስርዓት ስለመሆኑ ብዙ እማኞችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
፭ኛ- ከግለሰቦች በጎ ፍቃድ ይልቅ በፅኑ መሰረት ላይ በቆሙ ተቋሞች ላይ እንደገፍ፡- ኢትዮጵያ መሪዎች የማይከሰሱባት ህዝብ ደግሞ በእነርሱ አሳሩን የሚያይባት ሀገር በመሆን ትታወቃለች፡፡ በጎበዝ አለቃው የሚምል የሚገዘተው ህዝብ ከጎበዝ አለቆቹ የሚታደጉት ተቋማትን መገንባት አልቻለም፡፡ እስከአሁን እጣ ከፍሉ በገዥዎች መረገጥ ሆኖአል፡፡ ይህ ታሪካችን ወደ ኋላ ላይመለስ ይቀየር ዘንድ ሁላችንም የምናምንባቸውና የምንደገፍባቸውን ተቋማጽ ለመገንባት የሁላችንም ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ተቋማት መገንባት እስካልቻልን ድረስ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ መሆኑ ይቀጥላል፡፡
፮ኛ እስከሞት ድረስ የምንፀናላቸው መርሆዎች ባለቤት መሆን፡- ከአያሌ የፖለቲካ ችግሮቻችን በተጓዳኝ ይኸን ያህል ዘመን አገዛዝ ይሰለጥንብን ዘንድ ግድ ያሉን አያሌ ሁኔታዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አሸርጋጅነት ጎላ ብሎ የሚታይ ይመስለኛል፡፡ በየዘመኑ ግፍን የሚቃወሙ የአይበገሬነት ተምሳሌት የሆኑ ጀግኖች ሀገራችን አጥታ ባታውቅም የሰንበሌጥ ፖለቲካ የሚጫወቱ አያሌ ወገኖች በየዘመኑ እንደ እንጉዳይ ፈልተው ሲያድሩ ይስተዋላል፡፡ መርህ አልባነት የአድርባዮች መርህ ነው፡፡ ከግፍ ከውሸት ከህገወጥነትና ከግብረ ገብነት አፈንግጦና በፍርሃት ቆፈን ተቀይዶ ለግፈኞች ውዳሴ ማህሌት መቆም፡፡ የመከራውን ሌሊት ያስረዘመው ይኸን የግፍ ቋት የሆነ አካሄድ በግል በማህበረሰባችንም ሆነ በሀገር ደረጃ ከስሩ ተመንግሎ ሊጣል ይገባዋል፡፡ እውነት፣ ነፃነትና ሰብዓዊ ልዕልና አቋራጭ መንገድ የላቸውም በመርህ በእውነትና በፍቅር ላይ ቆመን ህልማችን ለመጨበጥ መትጋት ይገባናል፡፡
፯ኛ – ዘመኑን የሚመጥኑ አስተሳሰቦችን መታጠቅ፡- ስለ ኢትዮጵያን ጥንታዊ ገናና ስልጣኔ ብዙ እናወሳለን፡፡ የሚጎድለው እንዳች አገር የሌለ እስኪመስል ድረስ አብዝተን እናንቆለጳጵሰዋለን፡፡ የሚጎድለው ኖረም አልኖረ በሩቁ ዘመን አባቶቻችን የሰሯቸውን ነገሮች የሚጠጋ ነገር በዚህ ዘመናዊ ዓለም መስራት አልቻልንም፡፡ ሁኔታው በምን ዓይነት የአስተሳሰብ ድርቅ እንደተመታን ያሳያል፡፡ ከቆዩ ክፉ አስተሳሰቦች መላቀቅ ደግሞ የሞት ያህል ያስጨንቃል፡፡ ሰዎችን የሃሳብ መስመራቸውን ተከትሎ ከመከራከር ይልቅ በዘር ወይንም በጥቅም መነፅር ብቻ የማየት ሀሳብ ተፀናውቶናል፡፡ ይህን መሰሉ የፖለቲካ እይታ ደግሞ እጅግ ኋላቀርና በማኅበረሰብ እድገትም በስረኛውና በመጨረሻው ንጣፍ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ወደ ኋላ እያየን ወደ ፊት እንሮጣለን፡፡ ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ ባለቤቶች መሆን ይገባናል፡፡ የመፍታት ችግር በስፋት ይታይብናል፡፡ ተግባቦታችን እርስ በእርሳችንም ሆነ ከሌሎች ጋር ደካማ ነው፡፡ በአመዛኙ ዝግ ነን ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዜግነታችን ላይ አለመተማመን ሊተከል ደግሞ ዳፋው ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም ለአዲስና ከእኛ ለተለዩ አስተሳሰቦች መዘጋጀት ያሻናል፡፡ በሰብዓዊና ስነ ልቦናዊ ብቃታችንም ሙሉ መተማመን ሊኖረን ይገባል፡፡
፰ኛ – ቁርጠኝነት፡- የምንቆምለትን ዓላማ ካልተገባ ጥቅም ከከንቱ ውዳሴም ሆነ ከአቋራጭ መንገድ በፀዳ መልኩ በእውነትና በምንሰራው ነገር ትክክለኛነት በፍፁም በማመን መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ለተሰጠንለት ዓላማ ለውጤት መብቃት የምንችለውን ሁሉ ለመክፈል ቁርጠኝነቱ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ የኋላ ታሪካችን መለስ ብለን ስናይ ወይንም በትውልድ የኋልዮሽ ስንታይ ከሚያኮሩ ነገሮች መካከል በጉዳዮች ላይ የያዝነው አቋም ብቻ ሳይሆን አቋማችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በወሳኝ ወቅት የምናሳየው ቁርጠኝነት ትልቁ መገለጫችን ይመስለኛል፡፡ ይህን የመሰለውን ሰብዓዊ ጥራት ማዳበር ለግላዊ እድገትም ሆነ ለማኅበረሰብ እድገት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው፡፡
፱ኛ- የታዛቢነት ፖለቲካ ይምከን፡- በተለይ ከ1960ዎቹ መሰረት ያደረገ እልቂት በኋላ ምሁራን ወደ ትግሉ መመለስ ቀጥ ያለ ተራራን የመቧጠጥ ያህል ከብዶን ቆይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ትልቅ ስራ የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖአል፡፡ የኢትዮጵያችን ምሁራን መናኸሪያ የውጭ ሀገር diaspora ከሆኑ ከራርሟል፡፡ በእርግጥ ከእነርሱ ውስጥ ጥቂቶቹም በተለያዩ መንገዶች ታግለዋል፡፡ አብዛኛው ግን በአርምሞ መታዘብን መርጠዋል፡፡ አርምሞው ምን ዓይነት መንፈሳዊ ልዕልና እንዳጎናፀፋቸው የሚያቁት እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በተለያየ መልኩ ሲደመጡ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች አያሌ ህፀፆችን ያነሳሉ፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲከኛ ፖለቲከኞች ችግሮች ማውሳት ምንም ዓይነት ምሁራዊ ትንታኔ የሚያሻው አይደለም፡፡ ፖለቲከኞች እውቀትም ሞራልም ሆነ ተሞክሮው ላይኖረን ይችላል፣ በአመዛኙም እንደዚህ ነው፡፡ መፍትሔው ግን ፖለቲከኞች ሞራል ስለሌላቸው ሞራል ያላቸው ምሁራን መሳተፍ ወይንም ሌሎች ብቃቱና እውቀቱ እንዲሁም ሞራሉ ያላቸው ወገኖች እንዲታገሉ መታገል ነው፡፡
፲ኛ -ፀረ ዘረኝነት ዘመቻ ማወጅ፡- ሁላችንም አንድ የሚያደርገን አንድ ነገር ካለ የመጀመሪያው ፀረ ዘረኝነት ዘመቻ ይመስለኛል፡፡ በዘረኝነት የሚያንስ፣ የሚከሰስና የሚጎዳ እንጂ እነዚህ እውነቶች ተቃራኒው የገጠመው ግሰብም ሆኖ ማህበረሰብ ማቅረብ አንችልም፡፡ “Groups are more immoral than individuals” (ቡድኖች ከግለሰቦች ይልቅ ኢሞራላዊ ናቸው) እንዳሉት ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገሮች የምንመሰክረው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ዘረኝነት የአንድን ዘመን ትውልድ ብቻ ሳይሆን ያልተወሰዱ ልጆቻችን ሀፍረት ስለ መሆኑ ብዙ ማጣቀሺያዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሀገራችን እያየን ያለነው የዘረኞችና ዘረኝነት የይዋጣልን ጥሪ በጊዜ እልባት ካልፈለግንለት ልንነቃ ወደ ማንፈለግበት ክፉ ህልም ይዞን ይወርዳል፡፡ እንደ ሀገር እንደ ትውልድም ሆነ እንደ ህዝብ ከዘረኝነት በላይ የሚያከስረን የሚያረክሰንና የሚያሳንሰን የክፋ ደዌ ሊኖር ሊኖረን አይችልም፡፡
11ኛ በራሳችሁ ላይ እንዲደረግ የማትሹትን በሌሎች ላይ አትድርጉ፡- ይህ ሃይለ ቃል የሃይማኖቶቻችን ሁሉ ወርቃማ መርህ ነው፡፡ ምን አልባት ስንክሳ ለበዛበት የፖለቲካ ችግራችን ትልቁ መፍትሔ ይመስለኛል፡፡ ለራሱ ሰብዓዊ ክብር ጥቅምና ነፃነት ቀናኢ የሆኑ ሁሉ ከልብ ሊታጠቁት የሚገባ እውነት ይመስለኛል፡፡ ሞራላዊ ግባችንን ኢሞራላዊ በሆነ መንገድ ማሳካት ፈፅሞ ተገቢነት አይኖረውም፡፡ የሰው ልጅ ትልቁን ሽልማትም ሆነ ቅጣት ከህሊናው ይቀበላል፡፡ ለእኔ ሁልጊዜ ወደ ሞት አፋፍ ሲወርድ በሰዎች ላይ ስላደረኩት ክፋት ማድረግ ሲገባኝ ስላልፈፀምኩት ተግባር መጸጸት የሞት ሞት ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ለሁላችንም በጎ በሆኑና በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መቆም ብሎም መታገል ተገቢ ነው፡፡
12ኛ ፍቅር እንዲያሸን እንፍቀድለት፡- ዶ/ር ኪንግ ኒቼ ፍቅርን አቅመቢስ እንደሆነና የቆጠረው ፍቅር ውስጥ ያለውን ሀይል ስለማያውቅ ነው ይላሉ፡፡ በግሌ የሰላማዊ ትግል ላይ የሙጥኝ ስል የፍቅር መንገድ ፍፁም የሆነ የግፍና የአንባገነንነት ማርከሻ መሆኑን በማመኔ ነው፡፡ ከሃይል ሁሉ የበረታው ሃይል ፍቅር ውስጥ ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል መንገድና ውጤት ከቁብ የሚፅፈው ያለ ባይመስልም በፍቅር ዘመን ጠገቡን የአገዛዝ ተራራ ለመናድ ሳይገድሉ ለመሞት የቆረጡ ወጣቶቻችን የፈፀሙት ገድል ከሁሉ ለከበረው እውነት የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ ማናችንም በፍቅር ማሸነፍ እንደምንችል አሁን ያለንበት ዘመን እማኝነቱን ይሰጣል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በፍቅር ብዙዎችን ትጥቅ አስፈትተዋል፡፡ የጓድ መንግስቱም ሆነ የአቶ መለስ አፈ ሙዝ መማረክ ያልቻለውን የኢትዮጵያውያንን ልብ ዝቅ ብለው በፍቅር እየማረኩ ይገኛሉ፡፡ ትልቅ ማስተዋል ነው፡፡ አሁንም ለፍቅር ተጨማሪ እድል አብዝተን ልንሰጠው ይገባል፡፡ የምናጭደው ስኬት ዛላም እንዲሁ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡
13ኛ የተስፋ ፅናት ይኑረን፡- ኢትዮጵያችን ሁሉም ነገር በጅምር የሚገኝባት ሀገር ነች፡፡ የመጣነው መንገድ ቀላል ባይሆንም እራሳችንን ለእረፍት ለማዘጋጀት የሚበቃ ውጤት ላይ በአንዳንችንም ዘርፍ ላይ አልደረሰንም፡፡ ይህ ሁኔታ ልብ ያዝላል፡፤ በመከራ ውስጥ ውጤት እንደሚገኝ ማመን የሰው ልጅ የትኛውንም የአገዛዝም ሆነ የችጋር ድቅድ የሚገፍ ሀይል የተሞላ መሆኑን ማመን ወሳኝ ነው፡፡ በተስፋ ሙላትና በአይበገሬነት የተሞሉ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የሰሩን ማስታወስ በዚህ ዘመን ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል፡፡ በሰዎች ላይ በግፍ እስካልተሳ ድረስ የሚጨነግፍ ተስፋ አይኖርም አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተስፋ እጦትን በተስፋ ሙላት የምንተካበት ዘመን ነው፡፡
ለዘመናት በጥይት ባሩድ የጠቆረው ሰማያችን የዴሞክራሲ ጠል እስኪያንጠባጥብ ድረስ በተስፋ ሙላት ልንታገል ይገባል፡፡ ጥላቻና ዘረኝነት ያነፈራቸው የወገኖቻችን ልቦች ፍቅርና ወንድማማችነት እስኪያብቡባቸው ድረስ በተስፋ እንፀናለን፡፡ በአሉታዊ ገፅታዋ የምትታወቀው ሀገራችን የአለም ሀፍረት ሳይሆን የአለም ጌጥ እስክትባል ድረስ በተስፋ እንፀናለን፡፡ አሁን የቆምንበት የነፃነት ብልጭታ ወደ ደማቅ የሕዝባዊ ልዕልና ንጋት እስኪለወጥ ተስፋን ተሞልተን ርዕያችን ለመጨበጥ እንተጋለን፡፡
ፍትህ እንደቀትር ፀሐይ ፍቅር እንደ ሃይለኛ ጅረት ወንድማማችነት እንደ አበባ ጉንጉን በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ይንገስ! 
 
ግዮን መጽሔት ቁጥር 43 የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም
Filed in: Amharic