>

ተካክሎ መበደል (ከይኄይስ እውነቱ)

ተካክሎ መበደል

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያ ከዘመነ ሕገ ልቡና አንስቶ እስከ ዘመነ ሐዲስ በአምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበረችና እንዳለች በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የክርስትና እምነትን በ1ኛው ክ/ዘመን ተቀብላ፣ ሥርዓተ ቤ/ክርስቲያንን አበጅታ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለምእመኗ መስጠትን ደግሞ በ4ኛው ክ/ዘመን እንደጀመረች አሁንም በቤተክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ይኽች ጥንታዊትና ብሔራዊት ቤ/ክ ላለፉት ከ06) በላይ ለሚሆኑ ዘመናት ፊደልን ቀርፃ÷ ብራና ፍቃና ደምጣ÷ ብርዕ ቀርፃ÷ ቀለም በጥብጣ÷ መጻሕፍትን ጽፋ÷ ዜማን ቀምራ÷ ሀገር በቀል ጥንታዊ መደበኛ ትምህርትን፣ ሕግን፣ ሥነ ጥበብን፣ ኪነ ጥበብን፣ የአገር ሀብት የሆኑ መንፈሳዊ ቅርሶችን ወዘተ ከማበርከቷ በተጨማሪ፤ ብሔራዊ ሥነ ልቦናን (የጋራ አስተሳሰብ፣ የጋራዕሤቶች፣ የጋራ ስሜቶች፣ የጋራ ጠባይ መገለጫዎች ወዘተ) በመቅረፅ ረገድ ታላቅ ሚና ያላት በመሆኑ ባብዛኛው  ዘንድ የኢትዮጵያ ዋልታና ማገር ተደርጋ ትታያለች፡፡

በዘመናት ሂደት ውስጥም ህልውናዋን በእጅጉ የሚፈታተኑ ከውስጥም ከውጭም ብዙ አደጋዎች ተጋፍጣ (ከቅዱሳን አባቶችና እናቶች እልቂት እስከ የአድባራትና ገዳማት ውድመት፣ የመጻሕፍትና የቅርስ ዘረፋና ቃጠሎ ወዘተ) በእግዚአብሔር ቸርነት በመንፈሳውያን አባቶች፣ እናቶችና ምእመናን ተጋድሎ (ሊቃውንተ ቤ/ክ ‹ስንዱ እመቤት››) የሚሏትን ‹እናት› እስከነ ሙሉ ክብሯ አስረክበውናል፡፡ ይሁን እንጂ እኛ የ!ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና የ!1ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ የምንገኝ ልጆቿ ይህን ታላቅ ኃላፊነትና አደራ መወጣት አቅቶን ከአገልጋይ እስከ ምእመን ተካክሎ በመበደል አገሪቱ በመንፈሳዊ ድርቅ እንድትመታ አድርገናል፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ባወቀ በየገዳማቱ ወድቀው በትህርምት፣ በጽሞና፣ በፆም በጸሎት ተጠምደው ከሚኖሩትና ከዝጉኀን አባቶችና እናቶች እንዲሁም ‹ስውር የከተማ ባሕታውያን› ውጭ መንፈሳዊነት በእጅጉ ርቆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታታይ ትውልዶች ከፍተኛ የሆነ የሞራል ድቀት ውስጥ እንገኛለን፡፡ በፖለቲካውም በሃይማኖቱም ሥልጣንና ገንዘብ÷ ሐሰትና ንቅዘት ሠልጥነው÷ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ይሉኝታ ጠፍተው ይህች የተቀደሰች ምድር አገር ለማጥፋት የቆረጡ ጃርቶች እስከማፍራት ደርሳለች፡፡

ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ ስለ ኢኦተቤ/ክ ቸር ወሬ ተሰምቷል፡፡ ዕርቁ ዘገየ ከሚባል በቀር ተፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም ይህን ‹‹ዕርቅ›› የተቀበልኩት በተዐቅቦ ነው፡፡ ምክንያቶቼን ከዚህ በታች ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

ከዚህ ቀደም ባቀረብኋቸው አስተያየቶች እንደገለጽኹት የወያኔ ትግሬ አገዛዝ እንደ መርግ ኢትዮጵያ ላይ ሲጫን ከጫካ ይዞ ከመጣው ተልእኮ አንዱ ይህቺን የኢትዮጵያ ባለውለታ ቤተክርስቲያን ድምጥማጧን ማጥፋት ነበር፡፡ ጨርሶ ባትጠፋም በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ በመግባትና ተልእኮውን ለማስፈጸም በመለመላቸው ሁለት ‹‹ፓትርያርኮችና›› እስከ አጥቢያ ቤ/ክ (ቆብ አስጠልቆና ጥምጣም አስደርጎ) ባሠማራቸው ካድሬዎች አማካይነት ወረራ በማድረግ ቤ/ክርስቲያኒቱን የዝርፊያ ዓውድማ አድርጓታል፡፡ ሕዝባችንን በዘር እንደከፋፈለው ኹሉ ቤ/ክርስቲያኒቷንም ለሁለት ሰንጥቆ መንፈሳውያን አባቶችን በመግደል፣ በማሠርና በመሠወር፤ውድ መንፈሳዊ ቅርሶችን በመዝረፍና በማጥፋት፤ ዋልድባን ያህል ታላቅ ገዳም በመድፈርና አባቶች በኪደተ እግራቸውን የባረኩትን የተቀደሰ መሬት በመንጠቅ፤ የቤ/ክ አባቶችና ምእመናን እርስ በርሳቸው ተናቁረው ምእመናን እንዲባዝኑ በማድረግ፤ አገር መካሪ፣ አስተማሪ፣ ገሣጭ፣ ሸምጋይና አረጋጊ አባቶች እንዳይኖራት፤ ግብረ ገብ የሌለው (ነውሩን ኹሉ እንደ ክብር የሚቀበል ትውልድ እንዲፈጠር) ወይም ሞራሉ የላሸቀ ማኅበረሰብ እንዲበዛ ወዘተ አድርጓል፡፡ የወያኔ ይቅር የማይባል ጥፋት እንዳለ ሆኖ፤ በዚህ ጥፋት ውስጥ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ በስደት የሚገኙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን አቅልለን የምናየው አይደለም፡፡ ለተጨማሪ ንባብ ከዚህ ቀደም ያቀርብኳቸውን አስተያየቶች ከሚከተሉት አድራሻ መመልከት ይቻላል፡፡

(https://www.ethioreference.com/archives/6190; https://www.satenaw.com/amharic/archives/54532)

አገር ውስጥ የሚገኘው የቤተክህነቱ አመራር፣

  • ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በጠላትነት ከሚያይ ከሀዲ ወይም አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ሠርቷል፤ ባጭሩ መለካውያን – የገዢዎች ፈቃድ ፈጻሚ ነበሩ፤
  • በሕይወት ያለን ፓትርያርክ ቦታ ቀምቶ ሳይገባው በወያኔ አለቆች የተሰየመ፤ ካንዴም ሁለቴ ከስደት ዘር ቆጥረው በመጡ ኢ-መንፈሳውያን ‹አባቶች› የተያዘ መንበር ነበር፤
  • ቤ/ክርስቲያኒቱን አዋርዶ ለአዋራጆች አሳልፎ ሰጥቷል፤
  • ከዲቁና እስከ ጵጵስና ያሉ የአገልግሎት ማዕርጋትን በገንዘብ የሚገዙ የሚለወጡ ሸቀጦች አድርጓል፤
  • ቤ/ክርስቲያኒቱ ምስካየ ኅዙናን (የችግረኞቸ መጠጊያ) መሆኗ ቀርቶ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ በሚል አስተሳብ በተጠመዱ ‹አገልጋዮች› እንድትሞላ አድርጓል፤
  • እውነተኛ መንፈሳውያን አገልጋዮችን ገፍቷል፤
  • ዘርፎ አዘርፏል፤
  • ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤ/ክ ያሉ ቊልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ካንድ አካባቢ በመጡ ተወላጆች (‹ጨዋ› ደናቁርት) እንዲያዝ በማድረግ በታሪኳ ከመቼውም ጊዜ በከፋ (የኢኦተቤ/ክ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ፀድታ ባታውቅም) ዘረኝነትን አስፋፍቷል፡፡ በዚህም ተግባሩ በርካታ ምእምናን ከቤ/ክ እንዲርቁ አድርጓል፡፡

በስደት የሚገኘው የቤተክህነቱ አመራር፣

  • ሲቻል ከአገር ሳይወጣ በገዳም መወሰን ነበረበት፤ ለሕይወት የሚያደርስ አደጋ ከነበረም (ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን በጠራራ ፀሐይ ለአገር መሥዋዕትነት በከፈሉበት አገር) በክብር ሰማዕትነት በመቀበል ምሳሌ መሆን ይገባ ነበር፤
  • ከአገር ቤቱ ‹ቤተክህነት› አመራር በከፋ ምእናንን እስከ መንደር ድረስ ወርዶ በዘር በመከፋፈል የክርስቶስ መንጋ ያለጠባቂ እንዲባዝንና ያለፍላጎቱ ለነጣቂ ተኩላዎች አሳልፈው ሰጥተውታል፤
  • ጥቂት የማይባሉ ‹‹አገልጋዮች›› የሀገር ፍቅር የሌላቸው፤ በምንፍቅና እንደሚታሙና በ‹ተሐድሶ› ስም እናት ቤ/ክርስቲያንን እየቦረቦሩ እንደሆነ የእውነተኛ አገልጋዮችና ምእመናን ምስክርነት አለ፤
  • በስደት የሚገኙትን ፓትርያርክ መሣሪያ በማድረግ የሰየሟቸው ‹‹ኤጲስ ቆጶሳትና ጳጳሳት›› ገሚሱ በዘር ቆጠራ፣ ገሚሱ ለቦታው የሚያበቃ ትምህርትም ሆነ መንፈሳዊ ዝግጁነት የሌላቸው፣ ገሚሱ በእምነታቸው ሕፀፅ የሚጠረጠሩ መሆናቸው፤
  • አንዳንዶችም ከፖለቲከኞች ጋር እጅና ጓንት በመሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ለሥልጣንና በሥልጣን የሚገኘውን ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት የቋመጡ መሆናቸው፤

‹‹ዕርቁ›› በ‹‹ሲኖዶሶች›› ወይስ በስደትና ባገር ቤት በሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱን አመራር እንወክላለን በሚሉ ግለሰብ ‹‹አገልጋዮች››?

ሲኖዶስን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ጉባኤ/ማኅበረ ጳጳሳት፤ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ሕግ÷ ሥርዓት፣ ቀኖናሃይማኖት ለመወሰን የመጨረሻ ሥልጣን ያለው አካል በሚለው ትርጕም ከተስማማን፣ በዘመነ ወያኔ የኢኦተቤ/ክ እንኳን 2 አንድ ሲኖዶስ አልነበራትም፡፡ አንዲት ሐዋርያዊት ቤ/ክ ሊኖራት የሚችለው አንድ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም አባቶቻችን ሐዋርያት የሠሩት ቀኖና ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ‹እናንተ በሰማይ ያሠራችሁት በምድርም የታሠረ ይሁን› የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር መሠረት አድርጎ መንፈሳውያን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ በሚመራ ጉባኤ የደነገጉት ሕግ በሰማይም የታሠረ (የተደነገገ) ነው፡፡ በስደት የሚገኙ ፓትርያርክ ግን ነበራት፣ አሁንም አላት፡፡ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ ሳለሁ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ፓትርያርክ አለ ማለት ግን የግድ ሲኖዶሰ አለ ወደሚለው ድምዳሜ አያደርሰንም፡፡ ሲኖዶስን ሲኖዶስ የሚያሰኘው እንደ አንድ ልብ መካሪ÷እንደ አንድ ቃል ተናገሪ÷ እንደ አንድ ሕይወት ኗሪ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቤ/ክርስቲያንን ማስተዳደር ነው፡፡ ይህ በተጓደለበት እንዴት ሲኖዶስ አለ ለማለት ይቻላል? ሲኖዶስ በሌለበት ደግሞ እንዴት የ‹ጨዋ› አነጋገር ተወስዶ ሁለቱ ‹ሲኖዶሶች› ታረቁ በሚል አገር ኹሉ ይቀባበለዋል?

አባቶች ‹ዕርቅ› መፈጸማቸው በበጎነት የሚታይ ቢሆንም ‹ዕርቁ› እና ‹የዕርቁ› ውጤት ዕውነትን መሠረት አድርጓል ወይ? ቀኖና ቤ/ክርስቲያንን የጠበቀ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ለማግኘት እንቸገራለን፡፡

ቤተክህነቱም ዕውነትን ፍርጥርጥ አድርጎ በመነጋገር የቤ/ክርስቲያንን ህልውና÷ የምእመናንን አንድነት ከማፅናት ይልቅ ልክ እንደ ‹ቤተመንግሥቱ› ወይም እንደ ዓለማዊው ፖለቲካ የማድበስበስ ድርድር ውስጥ ከገባ ውሎ አድሮ መዘዙ ቀላል አይሆንም፡፡

የሃይማኖት ዕውነት አንዲትና ደረቅ ናት፡፡ እንደ ፖለቲካው ዓለም ‹‹አማራጭ ዕውነት›› (alternative truth) የሚባል ነገር የለም፡፡ ዕርቀ ሰላሙ ዘላቂ የሚሆነው ሕገ ቤተክርስቲያን ሲከበር ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም፣

  • 2~ቱም በኩል አላግባብ የተሾሙ ‹‹ጳጳሳት››ን መቀበሉ ተገቢ አይደለም፤
  • በእውነተኛ አገልጋዮችና ስለ ተዋሕዶ መሠረተ እምነትና ሥርዓት በቂ ዕውቀት ባላቸው ምእመናን የተመሠከረባቸው የእምነት ሕፀፅ ያለባቸው ‹ጳጳሳት› እና በሥራቸው የተኮለኮሉ ‹ሐሳዊ አገልጋዮች› ባስቸኳይ በማስረጃ የተመሠረተ ማጣራት ተደርጎ እንዲመለሱ ወይም እምቢተኛ ሆነው ከተገኙ ተወግዘው እንዲለዩ ማድረግ ይገባል፤
  • ወያኔ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤ/ክ በየትኛውም የአገልግሎት ደረጃ አሥርጎ ያስገባቸው በተለይም ካንድ አካባቢ የመጡ ዘራፊ ካድሬዎችን ‹‹በጅራፍ ገርፎ›› ቤ/ክርስቲያንን ከወንበዴዎች ዋሻነት ማፅዳት ያስፈልጋል፤
  • የወያኔን ፈቃድ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ያለ አግባብ በመንበሩ ላይ የሚገኙትን ‹ፓትርያክ› አቡነ ማትያስን ለማዳን ሲባል 2 ፓትርያርኮችን ባንድ መንበር መሰየም ሥርዓተ ቤ/ክ አይፈቅደውም፡፡ በመሆኑም አባ ማትያስ በቤ/ክ ላይ ስለፈጸሙት በደል ተጸጽተው በጵጵስና ማዕርግ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑ ተገቢ ይመስለኛል፤አሁን እየተደረገ ያለውን የምረዳው ሕወሓት ‹ኢሕአዴግ› በሚል ሽፋን በኢትዮጵያ መንበር ላይ በጉልበት እንደሠለጠነ ኹሉ፣ አባ ማትያስም አባ መርቆርዮስን በምልክትነት አስቀምጠው የፓትርያርክነቱን ዋና ሥልጣንና ተግባር ሊፈጽሙ የታቀደ ሤራ አድርጌ ነው፡፡

አባቶች አጥብቃችሁ አስቡበት፡፡ ቤ/ክ ከምእመናን ውጭ አትታሰብም፡፡ ሀብቷም ጌጦቿም ምእመናን ናቸው፡፡ በሁለቱም ጎራ የምትገኙ አባቶች ምእመናንን የምትፈልጉት ለምንድን ነው? ለገንዘባቸው ወይስ እምነትን ከምግባር አስተባብረው ይዘው ምድራዊ ሕይወታቸው ተባርኮ የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች ለማድረግ?

እውነት መንፈሳዊነቱ ካለ፤ እነዚህ ‹መነኮሳት› ቆብ የደፉት÷ በቁማቸው የተገነዙት÷ ለዓለም ምዉት ነን ያሉት÷ ለንጉሠ ሰማይ ወ ምድር ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ለመሆን/ለሰማያዊ መንግሥት ከሆነ፤ እንዲጠብቁት አደራ ለተሰጣቸው ለመንጋው ከልብ የሚጨነቁ ከሆነ፣ እንደቀደሙት አባቶች ሥልጣንን ለምንድን ነው የማይጸየፉት? ቀደምት አበው እኮ በመንፈሳዊ ብቃታቸውና በትምህርታቸው (ዕውቀታቸው) ተመርጠው ሲያበቁ አንፈልግም ብለው ይሸሹ ነበር፡፡ ይህ የአገልጋይ አባቶችና የእኛ የምእመናን ተካክሎ መበደል ካልሆነ ሌላ ምን ትርጕም ሊሰጠው ይችላል? ቅዱስ ዳዊት በመዝ. 03.3 ‹‹ኵሉ ዐረየ ወኅቡረ  ዐለወ›› (ሁሉ ተካክሎ አንድ ሆኖ በደለ ወነጀለ) እንዳለው፡፡

የቤ/ክ አባቶች በሽምግልና በማስታረቅ ተግባር አገር እንዲያረጋጉልን መንግሥትን ጨምሮ የኹላችን ፍላጎት ነው፡፡ የሽምግልናውም ሆነ የማስታረቁ ተሰሚነት መሠረቱ የለበሱት ቀሚስ፣ የደረቡት ካባ፣ ያጠለቁት ቆብ፣ ያንጠለጠሉት መስቀል ሳይሆን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ያገኙት ንጽሕናና ቅድስና (መንፈሳዊ ፀጋ) መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

በመጨረሻም አገርን ያለ ቸር/በጎ ሰው የማይተው እግዚአብሔር መጨረሻውን ያሳምረው እንጂ በትሁት ወንድሞቻችን አቶ ለማና ዶ/ር ዐቢይ አገራችን ሊታደግ ጅምሩን እንዳሳየን ኹሉ፤ለኢኦተቤ/ክርስቲያንም ፊት ዓይተው የማያዳሉ መካሪና አስተማሪ፤ ገሣጭና አስታራቂ፤ መንፈሳዊነትን ከጥብዐት (ለበጎ መጨከን መድፈር) የያዙ አባቶችን ያበርክትልን፡፡

Filed in: Amharic