>

የአንዲት አገር ልጆች በሁለት ባንዲራ?!... (እንግዳሸት ታደሰ )

ትላንት ኦስሎ ላይ በተካሄደው የበጋ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ፣ በየአመቱ ሁልጊዜ እንደሚደርገው አልተገኘሁም ነበር ፡፡ ምክንያቱም አልተመቸኝም ፡፡ ባሳለፍነው ሰኞ የጰራቅሊጦስ በዓልን ለማክበር ፣ ኖርዌይ መሥርያ ቤቷን ሁላ ለበዓሉ ሲባል ዘግታ ነበር ፡፡ የነበረውን የዕረፍት ቀን አስታኮ ለታዋቂው የባህል ዘፋኛችን ጋሽ ዳምጠው በከፍተኛ ሁኔታ በመታመሙ ፣ የኢትዮጵያ ማህበራችን ጋሽ ዳምጠው አየለን ወደ ሃገሩ ለመመለስ ታላቅ የርዳታ ዝግጅት ፣ በአጭር ቀናት ውስጥ በኦስሎ ዙርያና አካባቢዋ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያኖች አዘጋጅቶ ነበር ፡፡
በዚያ ልብ ቅልጥ በሚያደርግ ሙቀት ሁሉም ዜጋ ሳይሸነፍ በተጠራው ሰዓት ላይም ሳይዘገይ በአዳራሹ ከአፍ እስከ አፍጢሙ ግጥም ብሎ በመገኘት ፣ በሙያ አጋሮቹ የያሬድ ሙዚቃ የባህል ባንድ የተዘጋጀውን ድግስ በመቋደስ የተዘጋጀውን የርዳታ ማሰባሰብ ዝግጅት ታድሞ ነበር ፡፡ ታላቅም የተሳካ የገንዘብ አሰባሰብ አድርጓል ፡፡
የድርጊቶች መገጣጠም ሆነና ዘወትር በየዓመቱ በሚደረገው የበጋ ዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድር ድምቀት ይኖረው ዘንድ ድባቡን የሚያሞቀው ጋሽ ዳምጠው ነበር ፡፡ ግን ዘንድሮ አልቻለም ፡፡ በአልጋ ላይ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ማህበራችን ዘውትር እንደሚያደርገው በየአመቱ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ቢሽሌት ስታዲዮም ሄዶ ለወገኖቻችን የኢትዮጵያ ሯጮች ድጋፍ እንዲሰጡ ትኬቶችን በቅናሽ አከፋፍሏል ፡፡
የተቻለው ኢትዮጵያዊ በስቴድዮሙ ተገኝቶም ድጋፉን ለአገራችን ሯጮች አበርክቷል ፡፡ በርግጥ ለኢትዮጵያ ማህበራችን ተደራራቢ ታላቅ ሥራ ነበር ፡፡ ምክንያቱም የጋሽ ዳምጠው አየለን ከፍተኛ ውጣ ውረድ ሥራ አልጨረሰምና፡፡ እንደገና ከሶስት ቀናት በኋላ ደግሞ እዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊው እንዲታደም ሌላ ሥራ ቢታከልበትም ፣ በተቻለው መጠን ኢትዮጵያዊው ስታዲዮም በመገኘት ድጋፉን ለአገራችን ሯጮች እንዲለግስ አድርጓል፡፡
ዘንድሮ ግን አኪርና ክሜራ ፊቷን ወደሌላ አዙራ ፣ የኦነግ ደጋፊዎች በብዛት ባንዲራቸውን ይዘው በመውጣታቸው ፣ ካሜራውም ከፊት ለፊት ስላገኛቸው ፣ በተደጋጋሚ የኦነግ ባንዲራ ፣ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በላይ ይታይ ነበር ፡፡ የአምስት ሺህ ሜትር ሩጫው ሲቀጥል ፣ ከአንድ ወገን የኦነግ ባንዲራ ፥ በሌላው ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሁለቱም የአንድ አገር ልጆች እየተቀዘፈ ድጋፋቸውን ላገራቸው ልጆች ይቸሩ ነበር ፡፡
ሩጫው ቀጥሎ ከመሃል አላምረው የኔነው የሚባል ኢትዮጵያዊ ግን ከመሃል አፈትልኮ ሲወጣና ሲያሸንፍ ግን ስሙን አይተው የኦነግ ደጋፊዎች እንዲያ የሚያውለበልቡትን ባንዲራ አሳርፍ አሉት ፡፡ በቴሌቭዥን መስኮት ማየትና በስቴድዮም ተገኝቶ ማየትን ፣ ልዩነቱን ያየሁት ዘንድሮ ነው ፡፡
እኔ አላምረው ኦሮሞ ይሁን አማራ ፥ ትግራዋይ ይሁን ወይም በዘመኑ አጠራር የደቡብ ሰው ጉዳዬም አይደለም ፡፡ ለኔ መስፈርቱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ብቻ ነው ፡፡ ቢያንስ በዘሩ እንኳ ቢጠሉት ፣ በአፍሪቃዊነቱ ድጋፋቸውን ቢሰጡት ፣ ስልጡን ፖለቲካ ማለት ያ’ ነው ፡፡ ፖለቲካው እጅግ ፈረንጅ አገር እያበደ ነው ፡፡ በአገር ቤት በግፍ ለሚሰቃየው የኦሮሞ ብሄረሰብ ግፉን ለአለም ህዝብ ለማሳየት ድጋፍን ማሳየት ተገቢ ነው ፡፡ በዘረኝነት ግፍ በአገራችን የኦሮሞ ህብረተሰብ ላይ የሚደረገውን ግፍ ግን እየተቃወሙ በሌላ በኩል ደግሞ ያሸነፈው ሰው ስም የአማራ ስለሆነ ድጋፍ አንሰጥም ማለት ግን ወያኔ ከሚሰራው የዘር መድልዎ ያልተናነሰ ሌላ በደል ነው፡ይሄኔም ነው ፖለቲካችን ኣብዷል የምንለው።ለማንኛውም ! በዕለቱ በስቴድዮም ተገኝታችሁ ፣ ጀግናችንን  የኔነህ አላምረውን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላጀባችሁትና ላከበራችሁት ፣ የኢትዮጵያ አምላክ ያክብራችሁ፡፡
ፎቶ የኔነህ ኣላምረው በቢስሌት የዳይመንድ ሊግ ሲያሸንፍ የለበሰው ትክክለኛው ባንዲራ
Yenenew Alamrew

Filed in: Amharic