>

«እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይያዝም!» (ክፍል ፪) [አቻምየለህ ታምሩ]

የትግራይ ወታደሮች የሚያንገላቱት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የዘመቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች ሁሉ የተዋደቁለት ሰንደቅ አላማ ነው። ይህ ሰንደቅ አላማ የረጅም ጊዜው ይቅርና በቅርቡ ከ20 ዓመት በፊት ፋሽስት ወያኔና የመንፈስ አባቱ ሻዕብያ የበላይነትና የበታችነት ጦርነት ባደረጉ ጊዜም የተውለበለበ ብቸኛ ሰንደቅ አላማ ነው። ልብ በሉ! በዚህ የሁለቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጦርነት ወቅት ከ80 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አልቀዋል። ይህ ከታች የትግራይ ወታደሮች ሲያንገላቱት የሚታየው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ባድመ ላይ ሳይቀር የረገፉት 80ሺህ ወጣቶች እያውለበለቡት የተዋደቀለትን ሰንደቅ አላማ ነው።

ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ለመግባት 60 ሺህ ወጣት እንደገበረ ደጋግሞ ነግሮናል። በፋሽስት ወያኔዋ ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያ በማፍረስ የታላቋን ትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት የታገለው ወያኔ ከራሺያና ከቻይና የኮምኒስት ምልክቶች አውጣጥቶ የደረተው የባዕድ ባንዲራ ሕጋዊ ሆኖ ባድመ ላይ ወያኔ ስልጣን ለመያዝ ገበርሁት ከሚለው ወጣት በላይ በላይ የሚሆን 80 ሺህ ወጣት ዳር ድንበር ለማስከበር የተዋደቀበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ማውለብለብ ወንጀል ነው። ሌላው ቢቀር እነሱ የትግራይ ዳር ድንበር ተደፍሯል ብለው የኢትዮጵያን ወጣት ቀስቅሰው 80 ሺህ ወጣት ባድመ ላይ በማገዱበት የጦርነት አውድማ ላይ እንኳ የተውለበለበውን ሰንደቅ አላማ በኢትዮጵያ ምድር ማውለብለብን ወንጀል ያደረጉ ምን አይነት ጉዶች ናቸው?

ፋሽስት ወያኔ መቼም ቢሆን ተፈጥሮ የሆነውን ሰው ማጥቃቱን አይተውም። በትናንትናው እለት በፋሽስት ወያኔ ማሰቃያ ቤት ስድስት አመታት ታጉሮ ሲሰቃይ የኖረውን ወንድሙን አንዷለም አራጌን ለመቀበል የወጣውን ታናሽ ወንድሙን ያብባል አራጌንና ሌሎች 21 ሰዎችን በግፍ አስረው ልደታ አጉረዋቸዋል። አረመኔዎቹ ወያኔዎች ስድስት አመታት ሙሉ በማሰቃያ ጣቢያቸው በግፍ አስረውት የበቀል ጥማታቸውን ሲወጡበት የቆዩት አንዷለም አራጌና መላ ቤተሰቡ በአንዷለም መፈታት እንኳ ደስታ እንዳይሰማቸው በስስት ሲናፍቀ የባጀውን ወንድሙንና በጉጉት ሊቀበሉት የወጡትን ንጹሐን ወጣቶች አጉረው የጭካኔያቸው ማርኪያ እያደረጓቸው ይገኛሉ።

አንድ «ፈታን» አሉንና ሀያ ሁለት ሰዎችን በግፍ እግር ብረት አስረው ጥልቅ ተሃድሶ እያደረግን ነው ይሉናል። ስለዚህ በቃላት ከሚገለጸው በላይ ጨካኝ ወንጀለኛ የሆነው ፋሽስት ወያኔ ከነ ሕገ አራዊቱና የአፓርታይድ ድንጋጌው ተወግዶ ግፈኞች እኛን ያሰቃዩበት ያለው ግፈኛ እጃቸው የኋሊት በመጫኛ ታስሮ እውነተኛ ችሎት ፊት ቀርበው ለፈጸሙት ጭካኔ ፍርዳቸውን እስካላገኙ ድረስ ለትንፋሽ ማግኛና ለጊዜ መግዣ «የፖለቲካ እሥረኞች ተፈቱ» እየተባለ በጣት የሚቆጠሩ «እየተለቀቁ» ከሃያ እጥፍ በላይ አዳዲስ ንጹሐን በየእለቱ እየተጋዙ ባለበት ሁኔታ በፋሽስት ወያኔ ግፍ የጨቀየችዋ ኢትዮጵያ ስርየት ሊኖራት አይችልም።

 

Filed in: Amharic