>

ኦቦ በቀለ ገርባ በአዳማ ስታዲየም ያደረገው ድንቅ ንግግር (ትርጉም: ጥላሁን ግርማ)

ዛሬ እኛ ከእስር የተፈቱ ሰዎችን ለመቀበል እና ድሉን ለማክበር ከላይ ታች እያልን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ትግላችን ጠንክሮ እዚህ በመድረሱ ራስ ምታት የያዛቸው ሰዎች ምን እየዶለቱብን እንደሆነ ለማወቅ አንችልም።

ስለሆነም ብልጥ ከሆናችሁ በመካከላችሁ ንፋስ ሳታስገቡ በፖለቲካ ድርጅት ሳትከፋፈሉ ፣ በሃይማኖት ሳትከፋፈሉ በሌላ በሌላ ነገር ሳትከፈፈሉ አንድ ሆናችሁ ሃገራችንን ወደፊት ማራመድ ይጠበቅብናል።

አሁን የተገኘው ነፃነት በምን አይነት ትግል እንደተገኘ ሁላችሁም ታውቃላችሁ። ስለሆነም ይህንን በስንት ትግል የመጣ ነፃነት መጠበቅ ይኖርብናል።

“… የሰዎችን ንብረት ፣ የግለሰብ ንብረትን ፣ የህዝብ ንብረትን እንዲሁም የመንግስት ንብረትን ሳንነካ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው በሰላማዊ እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንታገላለን!

“እንታገላለን!”

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን ወዳጅነት ማጥበቅ ይኖርበታል። በክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች እንደ ኦሮሞ የመታየት መብት እና ኦሮሞ የሚያገኛቸውን መብቶች በሙሉ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
በክልላችን ውሥጥ እስከኖሩ ድረስ እነሱም የኛ ናቸው። እነሱም ወገኖቻችን ናቸው።

ኦሮሞን የሚወድ ሰው ፤ የኦሮሞን ልማት የሚወድ ሰው ፤ ኦሮሚያ ነፃ እንድትሆን የሚፈልግ ሰው በኦሮሞ ትግል ላይ ጠላትን አይገዛም። እኛ የምንፈልገው ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ጋር በመዛመድ ዝምድናችንን ማብዛት ነው።

በሰላም በልጣችሁ ተገኙ! እሺ በሉኝ?

“እሺ!”

በፍቅር ልቃችሁ ተገኙ!

“እሺ!”

በልማት በልጣችሁ ተገኙ!

“እሺ!”

በመልካም ባህሪ ልቃችሁ ተገኙ!

“እሺ!”

በመደማመጥ ልቃችሁ ተገኙ!

“እሺ!”

ሰውን በመጥላት ሳይሆን ሰውን በመውደድ በልጣችሁ ተገኙ!

“እሺ!”

ይህንን ማድረግ ከቻልን በምድር ላይ ስማችን በጥሩ ይታወሳል። ስማችን በጥሩ እንዲነሳ ባላችሁበት ቦታ ሁሉ የህዝባችሁ ተወካይ ሆናችሁ ተገኙ። እያንዳንዳችሁ የህዝባችሁ ተወካይ ናችሁ ሰው እናንተን በሚያይበት አይን እና እኔን በሚያይበት አይን ኦሮሞን ያያል። እኔ ደግ ከሆንኩ ኦሮሞ ደግ እንደሆነ ይታወቃልና።

Filed in: Amharic