>

በህወሓቶች የሚመራው ሜቴክ በማን አለብኝነት የማጭበርበር ወንጀሎችን እየፈጸመ ነው! (BBN)

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ-ህወሓት ባለስልጣናት የሚመሩት ሜቴክ የተባለው ድርጅት፤ የማጭበርበር ወንጀሎችን እየፈጸመ እንደሚገኝ ተጠቆመ፡፡ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን-ሜቴክ በመባል የሚታወቅ ይኸው ድርጅት፤ በአብዛኛው ማለትም ከፍተኛው የአመራር ቦታው የተያዘው፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን በተቆጣጠሩ የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖች እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፣ ትልልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ያለ ጨረታ ነጥቆ በመውሰድ የግንባታውን ዘርፍ ተቆጣጥሮት ይገኛል፡፡
ሜቴክ እየገነባቸው ከሚገኙ የመንግስት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ይገኝበታል፡፡ ድርጅቱ ፋብሪካውን ገንብቶ ለመጨረስ ዓመታት የወሰዱበት ቢሆንም፤ ግንባታው ግን ዛሬም ሊጠናቀቅ አለመቻሉን የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደሜ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 1 ቀን 2010 የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በተመለከተ፤ ለገዥው ፓርቲ ፓርላማ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ ሪፖርቱ በሚቀርብበት ወቅትም፤ ሁሉም አመራሮች ሜቴክን በአቅም ውስንነት ሲወነጅሉ እንደነበር መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ጨምሮ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በቀረበው የፋብሪካው ግንባታ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ሜቴክ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ግንባታ በገባው የጊዜ ገደብ ካለማጠናቀቁም በላይ፤ የገንዘብ ማጭበርበር ውስጥ መዘፈቁን የሚያመላክቱ ገለጻዎች ተደምጠዋል፡፡
በዋነኝነት የህወሓት ጄኔራሎች የሚመሩት የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን-ሜቴክ፣ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ያጠናቀቀው 44 በመቶ ቢሆንም፤ የወሰደው ገንዘብ ግን 60 በመቶ መሆኑን የገለጹት የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ‹‹ይሄ ተገቢ አልነበረም፡፡›› ሲሉ ሜቴክ ከደንብ ውጭ የወሰደው ገንዘብ ህገ-ወጥ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ በጊዜ አለመጠናቀቅ ወይም መንጓተት ዋነኛ ችግሩ የሜቴክ አቅመ-ቢስነት መሆኑን የገለጹት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደሜ በበኩላቸው፤ ሜቴክ ፋብሪካውን ገንብቶ ለመጨረስ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በድጋሚ በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የማዳበሪያ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የታቀደው በሚቀጥለው ዓመት ነሐሴ ወር 2011 ቢሆንም፤ እንደ ሜቴክ አያያዝ ከሆነ ግን ፋብሪካው በተጠቀሰው ጊዜም ተገንብቶ ሊያልቅ እንደማይችል አቶ ፍቃዱ ደሜ ተናግረዋል፡፡
የፓርላማው የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሪት ወይንሸት በበኩላቸው፤ ሜቴክ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በሚያካሂድበት የኦሮሚያ ክልል፤ ህገ ወጥ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባልተፈቀደና በባህላዊ ዘዴ የድንጋይ ከሰል በስራ ተቋራጩ እየወጣ እየተሸጠ ይገኛል፡፡›› ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ይህ ህገ-ወጥ ድርጊት ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉ የሜቴክን ማጭበርበር ኮንነዋል፡፡ ለፋብሪካ ግንባታው መዘግየት እጃቸው ያለበት አካለት ሁሉ በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡ በዋነኛነት በሜቴክ አቅመ-ቢስነት ለዓመታት ሲንጓተት በቆየው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጉዳይ፤ መንግስት ውሳኔ እንዲሰጥበት በዚሁ የካቲት ወር 2010 ቀጠሮ መያዙ ተገልጿል፡፡

Filed in: Amharic