>

በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ውጥረት መንገሱ ተጠቆመ (BBN)

በኢትዮጵያው አገዛዝ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ውጥረት መንገሱን ምንጮች አመለከቱ፡፡ የውጥረቱ ምልክቶች መታየት የጀመሩት ቀደም ብሎ ቢሆንም፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ውጥረቱ ስጋ ለብሶ መታየቱን ነው የመረጃ ምንጮች የጠቆሙት፡፡ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ትግል በሰራዊቱ ውስጥ ለተፈጠረው ውጥረት መነሻ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮቹ፤ ህዝባዊ ትግሉ በህወሓት ጄኔራሎች ቁጥጥር ስር የሚገኘውን መከላከያ ሰራዊት ውጥረት ውስጥ እንዲገባ እንዳስገደደውም ያክላሉ-የመረጃ ምንጮቹ፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለማቋረጥ እየተካሄደ የሚገኘው ህዝባዊ ትግል፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን ይዘው ለሚገኙት የህወሓት ጄኔራሎች እና ሲቪል ባለስልጣናት አስፈሪ መሆን ከጀመረ ቆየት ማለቱን የሚገልጹት መረጃዎቹ፤ በዚህም የተነሳ ህወሓቶች፣ በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጅ ወታደራዊ መኮንኖች መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉብን ይችላሉ የሚል ስጋት ውስጥ እስከመግባት መድረሳቸውንም መረጃዎቹ ያክላሉ፡፡ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ እና ሌሎች ባለስልጣናት ወደ አመራርነት ከመጡ በኋላ መነቃቃት እንደሚታይበት የሚነገርለት ኦህዴድ፣ ከዚህ ቀደም በፓርቲው ታሪክ ባልነበረ ሁኔታ ብቅ ብቅ ማለቱ፣ በህወሓት ዘንድ የራሱ የሆነ የስነ ልቦና ጫና ሊፈጥር እንደሚችል የሚገምቱ ታዛቢዎች አሉ፡፡
ከኦህዴድ አዲስ የፖለቲካ መነቃቃት ጀርባ የህወሓት እጅ ሊኖርበት እንደሚችል የሚጠረጥሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ፓርቲው ከዚህ ቀደም ያልፈጠረበትን ፖለቲካዊ መነቃቃት እያሳየ የሚገኘው፣ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ የልብ ልብ ሰጥቶት ነው ሲሉ የሚገልጹ ወገኖችም አሉ፡፡ እንደነዚህ ወገኖች ገለጻ ከሆነ፤ በኦህዴድ ባለስልጣናት ዘንድ የተፈጠረው መነቃቃት፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በሚገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ወታደራዊ መኮንኖች ውስጥ ሰርጾ ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለህወሓት አደገኛ ሁኔታ መሆኑንም እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡
ቅዳሜ ጥር 26 ቀን 2010 ለ61 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ ሹመት መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በድጋሚ ትላንት አሁድ ጥር 27 ቀን 2010 ደግሞ፤ ወታደራዊ ሹመት ከተሰጣቸው 61 የሠራዊቱ አባላት መካከል ለሶስቱ፣ የምክትል ጠቅላይ ኤታማዦርነት ሹመት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዳሜ ዕለት ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እጅ የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ እንደተሰጣቸው የተነገረላቸው ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ይመር፣ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ገለልቻ እና ጀነራል አደም መሐመድ ሟህመድ፣ ትላንት እሁድ ዕለት ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ‹‹የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦርነት›› ሹመት እንደተቀበሉ ተገልጿል፡፡ ከሶስቱ ጄኔራሎች አንዱ ማለትም ጄነራል ሰዓረ መኮንን ይመር የትግራይ ተወላጅ እና የህወሓት አገዛዝ አስጠባቂ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጅ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከዚህ ቀደም ‹‹የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር›› የሚባል የስልጣን እርከን ያልነበረ ቢሆንም፤ ይህ የስልጣን እርከን በሰራዊቱ ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የመጣ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የሰራዊቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሆኑት የትግራይ ተወላጅ ሳሞራ የኑስ ቢሆኑም፤ ፖለቲካዊ ውጥረቱን ተከትሎ ደግሞ ከእሳቸው በታች ሶስት ጄኔራሎች ‹‹ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር›› ሆነው እንዲሾሙ ተደርጓል፡፡ መከላከያ ሠራወቱ ውስጥ ባልነበረ ሁኔታ፣ በምክትል ጠቅላይ ኤታማዦርነት ከተሾሙት ሶስት ጄኔራሎች አንዱ እና የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ሰዓረ መኮንን፣ በቀጣይ የሳሞራ የኑስን ቦታ በመረከብ የጦር ኃይሎች ዋና ጠቅላይ ኤታማዦር ሆነው ሊሾሙ እንደሚችሉ የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

Filed in: Amharic