>

“ሱሪ የሰፋቸው” ብአዴኖች ! (መስከረም አበራ)

የኢህአዴግ ዕምብርት የሆነው ህወሃት መስራች አባላትን አንድ አሮጌ ሽጉጥ እና አንድ የሽንኩርት መክተፊያ ቢለዋ አስይዞ ደደቢት በረሃ ያስገባቸው ሆን ብሎ የትግራይን ህዝብ የሚበድል አማራ የሚባል “ባለ ሰባት ቀንድ” ጠላት አለን ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ ለእነዚህ የነፃነት ታጋይ ነን ባዮች የዘር ጥላቻ (በተለይ የአማራ ጥላቻ) ምትክ የሌለው ሁነኛ የትግል ማፋፋሚያ መንገድ ነበር፡፡የትግል ጥንስሳቸውን በጥላቻ ፖለቲካ መርዝ ለጀመሩት ህወሃታዊያን የትግራይን ሁለንተናዊ ጉስቁልና ያቀነባበረው አማራ የተባለው ባለሰባት ቀንድ ጭራቅ ነው፡፡ለትግራይ ክልል ዝናብ አጠርነት፣ለተራሮቿ ወጣ ገባነት፣ለግራ ካሱ ዳገት ጠመዝማዛነት ሳይቀር አማራን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚዳዳው ማኒፌስቶ በቁም ፅሁፍ አዘጋጅተው ሊገድላቸው የማለውን የአማራ ጥላቻ በክታብ አፀኑ፡፡ የሚገርመው ዛሬ ከተሜ ሆነው፣ ኩሽሽ አውልቀው ከረቫት አስረው ሳይቀር ይህንኑ ሊያፍሩበት የሚገባውን በጥላቻ የነተበ አካሄዳቸውን ማሞካሻታቸውን አለመተዋቸው ነው፡፡ የዛሬ ሁለት አመት አቶ አባይ ፀሃይየ “እኛ የተሳካልን ለማታገል ቀላል የሆነውን የብሄር ጥያቄ ይዘን መነሳታችን ነው” ማለታቸው የዚህ አንድ አስረጅ ነው::

የያዙትን ነገር ዳር በማድረስ የማይታሙት ህወሃቶች ጠላታችን ከሚሉት አማራ ህዝብ ቤት እየበሉ እየጠጡ ታግለው አዲስ አበባ መግባታቸው በልጅነታቸው የተላከፋቸውን የአማራ ጥላቻ አላደበዘዘውም፡፡በአይናቸው ያዩት የአማራ ህዝብ ድህነት የአማራን ህዝብ አሻቅቦ የማየት የዝቅተኝነት ስሜታቸውን አላረገበውም፡፡ጭራሽ ባሰባቸው! በመሰረቱት መንግስታቸው እጣ ፋንታ እንዳይኖረው አግልለው መንግስታቸውን አፀኑ፤ ከጠመንጃቸው እኩል አንግበውት አዲስ አበባ የደረሱትን የአማራ ጥላቻ ለሰሚ ሁሉ አደሉት፡፡ አማራን ማንቋሸሽ የአጋር እና አባል ድርጅቶች ካድሬ አፍ ማፍታቻ እና  የፖለቲካ እውቀት መለኪያ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ አማራን ከኖረበት ሃገሩ ማፈናቀል ጎፈሬ የሚያስበጥር ጀግንነት ሆነ፤ የአማራ ክልልን መሬት እንደ ሰንበቴ ፃዲቅ ቦድሶ መውሰድ የአማራ ሞቶ መቀበር ማረጋገጫ ተደረገ፤ የአማራ ህዝብ ግንዛቤ ልህቀት ነፀብራቅ የሆነው ተረቱ እና ባህሉ መሳቂያ መሳለቂያ ሆነ፤ አንገት መድፋት የማያውቀው ህዝብ አንገቱን ደፋ!

ይሄኔ ህወሃት ወለድ የጎሳ ፖለቲከኞች “አማራ ሳይዘጋጅ ደረስንበት” በማለት ፅዋቸውን ከፈጣሪያቸው ህወሃት ጋር አጋጩ!የጥቁር አማሮቹ ብአዴንም በፅዋ ማጋጨቱ ውስጥ አለበት፡፡

በበረከት ስምኦን ይመራ የነበረው የጥቁር አማሮች ቡድን ለአማራ ህዝብ ቆሜለሁ እያለ የአማራን ህዝብ በግልፅ የሚሳደብ፣ጀርባ ገልጦ ለህወሃት ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ለበቅ የሚያመቻች ይዞ አስገራፊ ሆኖ ብዙ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡አቃፊ መሳይ ገፍታሪው በረከት ስምዖን ህወሃቶች እንደወትሮው ጆሮ አልሰጥ ሲሉት አኩርፎ ከሄደበት አፍታም ሳይቆይ ተመልሻለሁ ያለው አንድም እሱ በሚያደርገው መጠን የአማራን ህዝብ ይዞ ማስገረፉ ለሌሎች ባለመሳካቱ፤ ሁለትም እንደሱ ያሉት “ፎርጅድ” አማሮች ከብአዴን ደጄሰላም መራቃቸው እውነተኛ የአማራ ልጆችን ወደፊት አምጥቶ ለህወሃት ክፉ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አደጋ እንዳለው ታስቦ ነው፡፡

በብአዴን የቤት ደንብ በአማራ ህዝብ ጥላቻ የሰከሩት ጥቁር አማሮች ያልባረኩት የክልሉ ተወላጅ ወደ ስልጣን ይመጣ ዘንድ አይታሰብም፡፡ የስልጣን ጥም ያክለፈለፈው የክልሉ ተወላጅ ሁሉ የቋመጠለትን ወንበር ያገኝ ዘንድ በጥቁር አማሮች ጫማ ስር መንከባለል አሽከራዊ ግዴታው ነው! ከኦህዴድ በባሰ በብአዴን ቤት አሽከርነት የበረታው ለዚሁ ነው፡፡ በአመዛኙ ትውልደ ህወሃት የሆኑት ካልሆነም የአማራን ህዝብ የመጥላቱን ጠበል በደደቢት በረሃ፣ በዋልዋ ተራራ ላይ የተጠመቁት ጥቁር አማሮች ደግሞ እግራቸው ስር የሚንከባለለውን የስልጣን ጥመኛ እነሱን የተጣባቸውን የአማራ ህዝብ ጥላቻ ሳያወርዱበት ከእግራቸው አንስተው ወደ ቋመጠለት ወንበር አይነዱትም፡፡ወንበር ላይ እስካለ ድረስም “ህዝበኝነት” እንዳይጎበኘው ሳያስጠነቅቁ ለወንበር አያበቁትም:: ይህንኑ ዘነፍ ሳያደርግ መከወኑን የሚቆጣጠሩበት ልጓም እንደፈረስ በመንጋጋው ሳያስገቡ የስልጣን ፍርፋሪን ያጣጥም ዘንድ አፉን አያቦዝኑለትም!

እንዲህ በጥቁር አማሮችን እግር ስር ተንከባለው ስልጣን የጨበጡት አማሮች የባህር ዳሩ ወንበር ላይ ተቀምጠው አዲስ አበባ የተቀመጠውን ሿሚ ሸላሚ ጌታቸውን ፈቃድ ይፈፀማሉ:: እንጅ የእነሱ እግርስር ወድቆ የእኩልነት ያለህ፣ የፍትህ ያለህ ፣በልቶ የማደር ያለህ ሚለውን ህዝብ ጩኽት የሚሰሙበት ጆሮ የላቸውም፡፡ አእምሯቸውን፣አፋቸውን እና ጆሯቸውን የተከራየው የአዲስ አበባው መንግስት የሚሰማውን ሰምተው የሚናገረውን እንዲናገሩ የአሽከር-ጌትነቱ ውል የታሰረበት ክር ያስገድዳል! ሚገርመው ነገር ግን የብአዴን የላይኛውን አመራር  ነፍሰ-ስጋ ተከራይቶ የፈለገውን የሚያናግራቸው ህወሃት ቁልቁል ቢሰቀሉለት እንኳን የማያምናቸው መሆኑ ነው፡፡

የጎሰኝነት አባት የሆኑት ህወሃቶች ራሳቸው የማያደርጉት ስለሆነ ሰው ከሌላ ጋር አብሮ የራሱን ጎሳ ሳያሰልስ ይበድላል ብለው ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አቶ መለስ እያሉ ጭምር ለህዝባቸው ተቆርቋሪነት በማሳየት የሚታወቁትን ኦህዴዶችን ቀርቶ ለአሽከርነታቸው እንከን የማይወጣላቸውን ብአዴኖች(ትውልዳቸው ከአማራ ብሄር የሆኑቱን) አያምኗቸውም፡፡  በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል ኮሽታ መብዛቱ የብአዴኖች ድጋፍ እንዳለበት  አጥብቀው ይጠረጥራሉ፡፡ግፋ ሲልም የድርጅቱን መስመር ለመሳት ዳርዳር በማለት ከዳተኝነት አፍ አውጥተው ይከሷቸዋል፡፡

ኮሎሌል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ከብአዴን እውቅና ውጭ ከትግራይ ገስግሶ በሌሊት በኮሎኔሉ ቤት የተገኘውን ገዳይ ቡድን ለመተባበር አቶ ገዱ ቸል ማለታቸው የአሽከር ማንጓጠጥ የመጀመሪያ ምልክት ተደርጎ ጥርስ ሳይነከስበት አልቀረም፡፡ አቶ ገዱ የተለመደውን ‘አቤት ወዴት!’ ያጓደሉት እውን ለህዝብ አስበው፣ ወይም የወንበራቸውን ሽራፊ ሉአላዊነት አስበው ሳይሆን ጀግናው ኮሎኔል እንደጥጃ አልነዳም ካለ በኋላ የተፈጠረው ቀውጢ ከጌታ ቁጣ የበለጠ አስፈሪ ሆኖ አግኝተውት ይመስለኛል፡፡ሁለትም ተመካክረን ብናደርገው ኖሮ እዚህ ሳይደረስ ሰውየውን ለመያዝ ሌላ ቀላል መንገድ ይገኝ ይሆናል በሚል “የተሻለው ለምን አመለጠን?” ከማለት ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ አጋጣሚ የአቶ ገዱን እና የካቢኔያቸውን ታማኝ ሎሌነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ አጋጣሚ ነው፡፡በበኩሌ የብአዴን የላይኛው አመራር ማንነት ከዚህ የተለየ መስሎ አይታየኝም፡፡

ኢህአዴግ በሚባለው መጋረጃ ውስጥ ህወሃት በሚዘውረው መንግስት/ፓርቲ ውስጥ አጋርም ሆነ አባል ተብለው የተኮለኮሉ ካድሬዎች ሁሉ ሎሌነታቸውን ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ የካድሬ ማጉረምረምም ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያመጣል ብየ አስቤም አላውቅም፡፡ ለዚህ ምክንያቴ ለማመንም ለመክዳትም የአንድ ቀን ተከርቼም ግምገማ የሚበቃው የካድሬ ፖለቲካዊ ግንዛቤ ለውጥን ለማምጣት ቀርቶ ለማሰብም ብቁ መስሎ ስለማይታየኝ ነው፡፡ ካድሬ ቢያልም ብሄሩን፣አበሉን፣ፎቁን እንጅ ዲሞክራሲን እንደማይሆን ስለሚገባኝ በየትኛውም የኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ ያለ ካድሬ ንግግርም ድርጊትም ቀልቤን አይገዛውም፡፡ የሆነ ሆኖ አበሉን፣ፎቁን፣ዘረፋውን ቸላ ብሎ ወይም ጎን ለጎን እያስኬደም ቢሆን ከዕለታት አንድቀንም ቢሆን ለስልጣን ያበቃውን ጎሳውን ጉዳይ አንስቶ ፈራ ተባ እያለም ቢሆን በጌቶች ፊት ኩርፊያውን እንኳን የሚገልፀው የኦህዴድ  ካድሬ እና በአሽከርነቱ ላይ ብቻ በሚበረታው የብአዴን ካድሬ መሃል ልዩነት የለም ማለት አይቻልም፡፡

ብአዴን የአማራ ህዝብ መታረድ፣ መፈናቀል፣ መሰደብ ታጋይ የህዝብ ልጅ በደሙ በላቡ የፃፈው ደማቅ ታሪክ አንድ ገፅ ይመስለዋል፡፡ ኦህዴድ ደግሞ የህዝቡ ሞት መፈናቀል ያሳስበዋል፤ በቀጥታ ተኩሶ ካፈናቀለው ጋርም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚያስተኩሰው አካል ጋር ቢያንስ በማህበራዊ ድህረገ-ገፅ ሲነታረክ ይታያል፡፡ የተፈናቃዮቹን ፍዳ ቶሎ ማቅለል ባይችልም፣ ሃብት ንብረት አፍርተው ለሰው ይተርፉ የነበሩት ተፈናቃዮች በአንድ ጀንበር ምፅዋት ጠያቂ ሆነው ስንት ወር ሙሉ ፀሃይ ቁር ሃሩር ቢፈራረቅባቸውም የኋላ ኋላ በኦሮሚያ ክፍት ቦታዎች እንዲሰፍሩ ለማድረግ እየጣረ ነው፡፡ በዚህ መከፋቱን ቢያንስ በኩሪፊያው ይገልፃል፣ የሚያስተዳድረውን ህዝብ በመትረይስ የሚቆሉ ባለጊዜዎችን አፉን ሞልቶ “ወንጀለኞች ናቸውና ለፍርድ ይቅረቡ” ይላል፡፡ በተግባር ለፍርድ እስከ ማቅረብ መጋፋቱ የሎሌነቱ ደረጃ ባይፈቅድም ማጉረምረሙም አንድ ነገር ነው፡፡ ብአዴን ደግሞ ገዳይ በሌለበት ሟች የሚኖር ይመስል ስለገዳዮች ትንፍሽ ሳይል “ለሞቱት አዝኛለሁ” ይላል፤ ጭራሽ ለቅሶ መድረስም ጀምሯል፤ “ለዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያቱ እኔ ነኝ” እያለ ማንም ጌቶቹን እንዳይጠይቅበት መጋረጃ ይሆናል::

ጥልቅ ተሃድሶው የብአዴንን ሱሪ ያሰፋውን ያህል ኦህዴድን አላደረገውም፡፡ ከጥልቅ ግምገማው ወዲህ በረከት ተመለስኩ ካለ በኋላ ብአዴን ሱሪው ሰፍቶት ሰፍቶት ሊወልቅበት እንደ ደረሰ ወልዲያ ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ የፓርቲው አመራሮች በሚሰጡት የተውሸከሸከ መግለጫ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ሰው ስለሞተ አዝነናል እያለ ስለሞተ ሰው የአዞ እንባ የሚያነባ ሰው ስለገዳዮች ጭጭ ካለ ከቡከንነት ሌላ ትርጉሙ ምንድን ነው? ሰዎቹን በታቦት ፊት በጥይት እየቆላ በደም የሚነክረው መቼም የአማራ ክልል ፓሊስ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ጦር ሜዳ እንዳሉ ሁሉ ያገኙት ላይ የጠመንጃ ላንቃ የሚከፍቱ ነፍሰ-ገዳዮች እነማን ናቸው? ከበዓሉ ቀደም ብለው ወልዲያ ከተማ ገብተው ሲሰፍሩ ገዱ ያውቅም ነበር? ካወቀ የወንጀሉ ግብረ-አበር ነውና ከተጠያቂነት አይመልጥም፡፡ አላውቅም ካለም አስተዳድረዋለሁ ባለው  ክልል ነፍሰ-ገዳይ ገብቶ ሲከትም ማወቅ ካልቻለ ስልጣን ላይ ምን ይሰራል? ወይስ ለምን ስልጣኑን በግልፅ ለእውነተኞቹ መሪዎች አስረክቦ ህዝቡም እውነተኛ ጠላቱን እንዲያውቅ አይሆንም? የምን መጋረጃነት ነው! ሲገቡ ያላወቀውን ወይም ተነጋግሮ ያስገባቸው ነፍሰገዳዮች ይወጣሉ ሲል ለህዝብ ቃል ከገባ  በኋላ ስንት ሰውነው የገደሉት? ይህን ሁሉ ያደረጉ ነፍሰ-በላዎችን ሳያወግዙ “የአማራ ህዝብ ሰዎችን በማንነታቸው ማጥቃቱ ትክክል አይደለም” ሲል ለገዳይ ሞሻሪዎች ማልቀስ ከአሽከርነት ሌላ ትርጉሙ ምንድን ነው?

ወልቃይት፤ ሰማያዊትiii

ከሰማይ በታች ባለ ችግር ላይ ሁሉ ከፓርቲየ ሥራ አስፈፃሚ ጋር ተነጋግሬበታለሁ ያለው ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ በእጅጉ እያሳሰበው ያለውን የወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ፣ ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ክልል የተዳበሉ ግጨውን የመሰሉ ለም መሬቶችን ጉዳይ በተመለከ ምንን ሳይባል ሲቀር አስጠቂው ብአዴን ነሁልሎ ከመቀመጥያለፈ ነገር አልሰራም፡፡ ከሰማይ በታች ባለ ነገር ላይ ሁሉ የተነጋገረ ስራ አስፈፃሚ በአንገብጋቢው የወልቃይት ጉዳይ ላይ ያልተነጋገረው ወይ የወልቃይት ነገር ከሰማይ በላይ ያለ ጉዳይ ነው አለያም ብአዴን ከምድር በታች ያረፈ አስከሬን ነው ማለት ነው፡፡

እስትንፋስ ያለው ሁሉ እንደሚረዳው የወልቃይት ነገር የአማራን ህዝብ ፀጉር የሚያቆም ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ የወልቃይት ነገር በወሳጁ የትግራይ ክልል ምክርቤት ይፈታ የሚለውን የቀደመ አቅጣጫ ለማስፈፀም መሰለኝ የብአዴን ዝምታ! ጌቶቹን ላለማስቀየም ሲል ዝም ይበል እንጅ የወልቃይት ነገር ለራሱም ለጌቶቹም ወንበር እጅግ ክፉ ውጋት ሊሆን እንደሚችል ለብአዴን  አይጠፋውም፡፡ አማራ ነኝ ያለ ወልቃይቴ ከገብሩ አስራት የስልጣን ዘመን ጀምሮም ሆነ ገና ህወሃት ጫካ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ባዶ ስድስት እስርቤት አይሆኑ ሲሆን እንደኖረ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለብአዴን ምኑም አይደለም! እያለባበሰው መኖርን መርጧል፡፡ አለባብሶ ማረሱ በአረም ለመመለስ እንኳን ፋታ የማይሰጥ መከራ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡

ብአዴን ምን ማድረግ አለበት?

ከአቶ አያሌው ጎበዜ ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ ያለው ብአዴን ከጥቁር አማሮቹ ብአዴን በተሻለ ለህዝብ የመቆም ነገር አለው፣ ነገር ግን ፓርቲው በህወሃት ጠንካራ እጅ እና ለህዝብ በማሰብ አጣቢቂኝ ውስጥ ገብቶ የሚንገላታ ነው፡፡ብዙ ትችት ባይበዛበት፤ ይልቅስ በአማራ ልሂቃን አይዞህ ቢባል እንደ ኦህዴድ ለህዝቡ በመቆም ረገድ የተሻለ ስራ ሊሰራ ይችላል የሚሉ ሃሳቦችን የያዙ መልዕክቶች ይደርሱኛል፡፡ አንድ ወዳጄ እንደውም “ብአዴን እኮ በማዕከላዊ የእስረኛ ጥፍር እንደሚነቀል አያውቅም፤ አለማወቅ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርጋቸው! እባክሽ ተረጃቸው” ብሎ ከሳቄ ጋር አታግሎኛል፡፡ አያውቁም የሚለውን ቀልድ እንተወውና እኔም ያልገባኝ እውነት ያላየሁት አቅጣጫ  ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ የሚባለውን ለማመን ለብአዴን ድንዛዜ ከስልጣን ጥም፣ ከአሽከርነት ልማድ እና የመስዕዋትነት ፍርሃት (የሱሪ መስፋት) የተለየ አጥጋቢ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ“ተያቸው”የሚለው ነገር ግን ቆምኩልህ የሚሉትን ህዝብ እያስፈጁ ላሉ ሰዎች በርቱ እንደማለት ያለ ነገር ስለሆነ የሚስኬድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ብአዴኖች መሰረታዊውን የቤቱን አመል ሳይስቱ፣ ደርሰው አሽከርነታቸውን እናሽቀንጥር ሳይሉ (ቢሉም የሚሆን አይደለምና!) አንዳንድ መሻሻሎችን ካላደረጉ የሚወዱትን የስልጣን ቱርፋት ለማጣጣም እንኳን የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የወሎ ህዝብ ከሰሞኑ በብአዴን ባለስልጣናት እና በቢሮዎቻቸው ላይ የወሰደውን እርምጃ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከትችት ባሻገር ብአዴኖች ሊያደርጉ የሚገባቸውን እርምጃዎችም ማሳየት ያስፈልጋል የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ስለደረሱኝ በኔእይታ ብአዴን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን እርምጃዎች ልጠቁም፡፡

  1. ራሱን ከጥቁር አማሮች ተፅዕኖ ማላቀቅ ነገ ዛሬ የማይለው የመጀመሪያ እርምጃው መሆን አለበት፡፡በረከት ስምኦንን፣ ህላዊ ዮሴፍን፣ታደሰ ካሳን፣አዲሱ ለገሰን የመሰሉ ጥቁር አማሮች ዓላማቸው የ1968ቱ የህወሃት ማኒፌስቶ ላይ የተቀመጠውን አማራን አርቆ የመቅበር ስራ ማስፈፀም ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ይህን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እነሱን ባየ ቁጥር የሚታወሰው የበደኖው ጭፍጨፋ፣ የጉራፈርዳው መፈናቀል፣ የአለምነው መኮንን ስድብ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚያሽከረክሩት ድርጅት እና አማራ ነኝ ባይ ካድሬ ለአማራ ህዝብ ይቆማል ማለት ዘበት ነው፡፡ እነሱን እንደአምላክ እያመለኩ የአማራ ህዝብ ወኪል ነኝ ማለት ቀልድ ነው! የነዚህ ሰዎች ሎሌ የሆኑ አማሮች ብቻ ወደ ብአዴን የስልጣን ማማ እንደሚመጡ ግልፅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በረከት ስምኦን የሚባል ሰው መለስ ቀለስ እያለ ለአማራ ህዝብ ጉድጓድ እንዲቆፍር መተው የለበትም፡፡

ህዝብ አንቅሮ የተፋቸውን ጥቁር አማሮች ጌታ አድርጎ እንደወደዳችሁ አድርጉን ማለት፣በረከት ስምኦንን የመሰለ ሰው እንደሚወደድ ሰው የበአዴንን ሁነኛ ስራዎች እንዲሰራ ማድረግ፤ ይህንኑ በቴሌቭዥን ማሳየት ብአዴንን የህወሃት “ዝነኛ” ማኒፌስቶ አስፈፃሚ አድርጎ ከማቅረብ አያልፍም፡፡ከሁለት አመት በፊት በብአዴን ስብሰባ ላይ የተገኘች አንድ እህት ያለችውን እዚህ ጋ መጥቀስ የነገሩን ሙሉ ትርጉም ያሳያል፡፡ “በአዴኖች ሱሪ መሰለኝ የለበሳችሁት፣ እናንት ሴት ህወሃቶች ወንድ ሆነው እንዲህ የሚያደርጓችሁ እንዴት ነው? እንዲህ ሆናችሁ ሆናችሁ ክፉቀን ሲመጣ መቼም መቀሌ ይዘዋችሁ አይሄዱ፤ እዚሁ ህዝቡ መሃል እንደምትቀሩ እወቁ፤ያኔ እናንተን አያድርገኝ” ልጅቷ ህወሃቶች የምትለው በነበረከት አድሮ ብአዴኖችን የሚያሽከረክረውን ህወሃታዊ ክንድ ማለቷ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

  1. የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ- ለህወሃት በመታዘዝ የማይታማው ብአዴን በአማራ ህዝብ እና ልሂቃን ዘንድ እንደ አስጠቂ እንደሚቆጠር ግልፅ ነው፡፡ ብአዴን ቆምኩለት የሚለው የአማራ ህዝብ ሲሞት ሲፈናቀል ይህ ነው የሚባል ድምፅ አሰምቶ የማያውቀው ህወሃትን ላለማስቀየም፣የሎሌነቱን ዳርቻም ለማሳየት ቢሆንም ህወሃት ግን አያምነውም፡፡ በአማራ ክልል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉ የብአዴን አመራሮች እጅ እንዳለበት ይጠረጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ብአዴን ከሁለት ያጣ ሆኖ ቁጭ ይላል-ወይ ጌታው ጎሽ አላላው ወይ ህዝብ እሰይ አላላለው! ስለዚህ ለህወሃት ባለው ጭልጥ ያለ ታማኝነት እና ለህዝብ ችግር ባለው ድፍን ጆሮ መሃከል የማመጣጠን ስራ መስራት አለበት፡፡ ለህወሃት ያለው ፍፁም ታማኝነት በከዳተኝነት ከመጠርጠር፣ምናልባትም አንድ ቀን ከመታረድ አያድነውም፡፡ በአንፃሩ ለህዝብ ችግር ትንሽ እንኳን ጆሮ ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ከህወሃት ለሚመጣበት መቅሰፍት ሳይቀር ህዝቡ ዋስትና የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ለዚህ ኮሎኔል ደመቀን  እንደ አርአያ መውሰድ ይቻላላል፡፡ ኮሎኔሉ ለኢህአዴግ ወግኖ ጫካ ወርዶ የተዋጋ ሰው ነበር፡፡እንደማንኛውም የብአዴን ካድሬ በህወሃት ትዕዛዝ የኖረ ነበር፡፡ ሆኖም ጭነት ሲበዛበት እንዴት ማለት ጀመረ፡፡እንዴት ማለቱ ደግሞ ጠበቃ አበዛለት እንጅ እንዲሁ ሜዳ ላይ አልተወውም፡፡ ስለዚህ ሁሌ እንደአህያ ከመኖር አንድ ቀን እንደ አንበሳ ኖሮ መሞትን ማሰብ ደግ ነው!
  2. ፈራ ተባን ማቆም፤ አቋምን ማሳወቅ- ከአማራ ህዝባዊ አመፅ በኋላ ብአዴን ያመጣው አዲስ ፀባይ አንድ ቀን ለህዝብ የቆመ መስሎ መታየት ወዲያው ደግሞ ህወሃታዊ ቃና ያለው ፍርደገምድል ንግግር እና መግለጫ ማውጣት ነው፡፡ የቅማት ህዝብን ሪፈረንደም በተመለከተ ተናገረው ሁለት ምላስ፣አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአቶ ዘርዓይ አስገዶም ጋር ያደረጉት ይበል የሚያስብል ንግግር ውሎም ሳያድር የወልድያውን ጭፍጨፋ በተመለከተ ሰለባውን ህዝብ ሊወቅሱ የሞከሩበት መውሸክሸክ በሁለት ጥይት የሚያስመታ ክፉ ወላዋይነት ብአዴንን ዘመድ አልቦ የሚያደርግ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ወይ ሎሌነቱን አጥበቆ መያዝ ወይ ከህዝብ እና ከእውነት ጋር ወግኖ አካፋን አካፋ የማለት ብርታት ያስፈልጋል፡፡
  3. ተጨባጭ እውነታዎችን መረዳት- በአሁኑ ሰዓት እንደ ብአዴን የከፋ ቀን እየመጣበት ያለ አሳዛኝ ድርጅት የለም፡፡ ህወሃት ብአዴንን ተተግኖ በአማራ ህዝብ ላይ ሲሰነዝር የኖረው ለበቅ ህዝቡን አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ገብቶ ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ጨምሮታል፡፡ አንድም ቀን የህዝብን ወገንተኝነት ለማግኘት ሰርቶ የማያውቀው ብአዴን እጣ ፋንታም የከፋ እንደሆነ የሚያመላክቱ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡የተወለዱበትን ጎጥ ህዝብ እንዲያረጋጉ የተላኩት አቶ ያለው አባተ፣ አቶ አለምነው መኮንን ህዝብ ፊት የመቆም ሞገስ አጥተው እግሬ አውጭኝ ሲሉ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራታቸው ብአዴኖች ነገ ከነገ በስቲያ ደግሞ በባህርዳር ከተማ ወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው ለማስተዳደር ስለመቻላቸው አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ የመርሳው አስተዳዳሪ መገደል ባህርዳር ላይ ላሉት ባለስልጣናት የሚያረጋጋ ዜና አይደለም! ስለዚህ ብአዴን የመጣበትን ጥቁር ቀን በውል ተረድቶ በገዛ ህዝቡ ከመበላት ለመዳን ልብ መግዛት አለበት፡፡ የህዝብ ወገንተኝነቱን በግልፅ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ቀዳሚው እርምጃ የዛሬው ብአዴን ከጥቁር አማሮች ብአዴን የተለየ እንደሆነ በተግባር ማሳየት ነው፡፡
  4. የብአዴን ጌታ ህወሃት ብቻ አለመሆኑን መረዳት- ብአዴንን ከሌሎች ቢጤዎቹ እህት ድርጅቶች የሚለየው አበይት ጉዳይ በሁለት ባለጠመንጃ አለቆች (በህወሃት እና ጠበንጃ በሚወደው የአማራ ህዝብ) መሃል መሰነጉ ነው፡፡ ብአዴን የህወሃትን ጠመንጃ እና እስር ሽሽት በአማራ ህዝብ ቁስል ላይ እንጨት ሲሰድ፣የህዝቡን ችግር ላይ አይቶ እንዳላየ ሲሆን፣ ፍርድ ሲገመድል የረሳው ነገር አመዛኙ የአማራ ህዝብም በህወሃት ቤት የፈራውን እሳት ያነገተ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህ ምስክሩ የአማራ ህዝባዊ አመፅ በተነሳ ሰሞን ጎንደር ላይ የተሰማው የጥይት በረዶ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ ህወሃት ብቻ ነው ብሎ አስቦ ለህወሃት ጠበንጃ ብቻ ማርገዱ የከፋ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ማወቅ ያስፈልጋል!
  5. በአዲስ አበባው ብአዴን እና በባህርዳሩ ብአዴን መሃከል ያለ የሚመስለውን ክፍተት መርምሮ መልክ ማስያዝ፡፡ የአዲስ አበባው ብአዴን ለአሽከርነታቸው እንከን የማይወጣላቸው እነ ደመቀ መኮንን፣ ተፈራ ደርበው፣ ይናገር ደሴን፣ ከበደ ጫኔን የመሳሰሉ ጉዳይ አስፈፃሚዎችን ያጎረ ነው፡፡ በአንፃሩ የባህርዳሩ ብአዴን በተለይ መካከለኛው እና ዝቅተኛው አመራር የህዝቡን ብሶት በተሻለ የሚረዳ፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ወገንተኝነት እየታየበት ያለ እንደሆነ ህወሃት ከሚያቀርበው የከዳተኝነት  ክስ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ብአዴን የጥቁር አማሮች ግርፍ ከሆነው የአዲስ አበባው ብአዴን ይልቅ ወገንተኝነቱን ከባህርዳሩ ዝቅተኛ እና ከመካከለኛ አመራር ጋር በማድረግ ጉልበቱን ማፈርጠም ይችላል፡፡ ለዚህ ታዲያ የጋራ አላማን ማስቀመጥ፣ በካድሬው መሃል ጠንካራ መወቅሮችን መገንባት እና በከፍተኛ ሁኔታ ተናቦ መስራትን ይጠይቃል፡፡አሽከርነታቸው ያየለባቸው የአዲስ አበባ ብአዴኖች በዚህ እንደማይስማሙ ይታወቃል፡፡ደመቀ መኮንንን የመሰለ አስጠቂ የብአዴን ሊቀመንበር መሆኑ ለባህርዳሩ ብአዴን ፈተና እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግን የዛ ሰው ካለው ለሚቀጥለው የፓርቲ ሊቀመንበር ምርጫ ብአዴን እንደ ደመቀ ያሉትን ለዘብተኞች ሽሮ የህዝብ ብሶት በሚሰማቸው እስከመተካት ድረስ ማሰብ ይኖርበታል!

መስከረም አበራ

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

Filed in: Amharic