>

ከድሉ ባሻገር! (ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን  ማስታወሻ ትሆን ዘንድ የተፃፈች)

ዘውድአለም ታደሰ

አላጋጩ አይኔ፥
ከታሪክ ገፅ ላይ ስላቅ እያሰሰ
ፌዘኛው መዳፌ፥
ከትናንት ድርሳን ላይ አሽሙር እያፈሰ
ባባቱ ሲቀልድ፥
ባያቶቹ ሲያሾፍ፥
ተጉዞ …. ተጉዞ «አድዋ» ደረሰ!

አድዋ!

ፊደላቱ ሁሉ ስእል እየሆኑ
ያሳዩኝ ጀመረ ታሪኬን አጉልተው
“ሎሬቱ” በብእር
ትናንቴን አምጥቶ ፥ ዛሬ ላይ ጎለተው!

አድዋ!

ባባቶቹ ሩጫ፥
መሳቅ የለመደው ፥ ዘመንኛው ጥርሴ
በከንፈሮቼ ስር ፥ መሸሸግን ሲሻ ፥ ገረመኝ ለራሴ!
ሳቅ ይፈጥራል ያልኩት ፥ ያያቶቼ ጀብዱ
ለፌዘኛ አይሆንም፣
በደም ተቀብቷል ፣ ተጋርዷል መንገዱ!

አድዋ!

ሎሬቱ ይፅፋል ፣
ይፅፋል ፣ ይፅፋል
ያባቶቹን ወኔ ፥
በጥበብ ለማስፈር ፥ ብቻውን ይለፋል
ከፊደል ሲታገል ፥
ግዜም እንደነፋስ ፥ በፍጥነት ይከንፋል!

ሱሌኦ ያ ሱሉ ሱሌኦ

«እምቢ አለ ፥ ምኒሊክ እምቢ አለ
ብረት እያማታ
ብረት እያጋጨ ጦሩን በሳት ሳለ!
እምቢ አለ!
ምኒሊክ አልታለል አለ
ዳኘው አባ ጎራ
የደጀን ተራራ
አፍሪካን ፣
ኢትዮጲያን ፣ እስከሰሜን ጣራ
በአለም ሊያኮራ
እምቢ አለ ምኒሊክ
ሱሌኦ ያ ሱሉ ሱሌኦ!»

ከነጭም የነጣ
ብራና ጨብጦ ፥ ሎሬቱ ተቆጣ
በላዩም ደርቧል ፥ ያባቶቹን እልህ ፣ ያያቶቹን ቁጣ!

ለሳቅ አይመችም የገለጥኩት ዶሴ
እንደመሸገ ነው አልስቅ አለኝ ጥርሴ!
ያዝናናኛል ያልኩት ያያቶቼ ጀብዱ
ፌዘኛ አያስኬድም፥
በአጥንት ታጥሯል ተጋርዷል መንገዱ!

«በቃ!»
አለች ጣይቱ
አንቶሎኒን አይታ
ብርቅ አይደለም ለኛ
መውጣት ቀራኒዮ መውረድ ጎለጎታ
በቃ!
የነጩን ድንፋታ ፥ በወኔዋ ካደች
የነጩን ከፍታ ፥ በኩራቷ ናደች
እንደእሳት ነድዳ ፥ ጣይቱ ፎከረች
«እግሩን ለሹል እሾህ ፣ ደረቱንም ለጦር
ለሀገሩ ማይይሰጥ፣
አንድም ኢትዮጲያዊ ፣ እዚህ እንደማይኖር
እወቅ አንቶሎኒ
ስማችሁ ራሱ ፥ ውል የለሽ ፥ ውል አልባ
ምኒ ምኒ ምኒ!»

ለካስ እቺ ሐገር
በተረት ላይ ብቻ ፥ ፀንታ አልቆመችም
ጎበዝ ምን ይሻላል?
የአድዋ ታሪክ ፥ ለሳቅ አይመችም!
ሳቅ ይፈጥራል ፥ ያልኩት ያያቶቼ ጀብዱ
ፌዘኛ አያስኬድም፥
በአጥንት ታጥሯል ፥ ተጋርዷል መንገዱ!

አድዋ!

ያለእግር ጠፈር
ነጠላ አጣፍቶ ፥ ሊሞት ቤቱን ለቅቆ
የሐበሻ ሬሳ ፥ ይታያል ፈራርሶ ፥ እዚያም-እዚም ወድቆ
አዋራው ይቦንናል ፥ በደም ተቀይጦ ፥ ከደም ተደባልቆ!

ያስፈራል አድዋ!
የፈረሱ ኮቴ ፥ የብረቱ ፍጭት ፥ የቁስለኛው ዋይታ
ሐበሻ ባንድ ላይ፥
ተሰቅሏል ላገሩ ፥ ይኸው ቀራኒዮ ፥ ይኸው ጎለጎታ!
ይኸው የሾህ አክሊል ፥ እነሆ ሚስማሩ
እልፍ ጀግና ወድቋል ፥ ተሰቅሏል፣ ለክብሩ!

እየተፃፈ ነው ፥ በኢትዮጲያ ሰማይ ፥ የሐበሻ ጀብዱ
ለፌዘኛ አይሆንም ፥ በደም ተለቅልቋል ተጋርዷል መንገዱ!

እዚም-እዚያም ፥ ወድቋል የሀበሻ ገላ
ወደፊት ነው እንጂ፣
ማፈግፈግ ነውር ነው ፣ መሸሽ ወደኋላ!

ገበየሁ ወደቀ ፥ ጀግናው ክንዱ ዛለ
ደሙን ሚመልሰው፥ ያ ባልቻ የታለ?
«ባልቻ ሳፎ ኢርጋና
አባ ነፍሶ ያባ ጤና
አካና ታሲፍ ቲካ አካና
ገበየሁ ወድቋል ቶሎ ና!»

«እንዲህ ነች ሐገርህ»
ብሎ ተረከልኝ ፥ሎሬቱ በመንፈስ
ቀለም ደፍቶ አሳየኝ ፥
ሐበሻ ሲታረድ ፥ ላ’ገር ደሙን ሲያፈስ!
ለክብሩ ሲዋደቅ፥
እንደበግ ሲሸለት ፥ ለነፍሱ ሳይሳሳ
ይህ ሁሉ ለኔ ነው ፥
ይህ ሁሉ ግብ-ግብ ፥ ይህ ሁሉ አበሳ
ደልቶኝ እንድራመድ ፥ እርጥብ አፈር ሆኗል ፥ ያያቶቼ ሬሳ!

ይፅፋል ሎሬቱ ያባቶቹን ወኔ
ታሪክን ያትማል ፣ ያስቀምጣል ለኔ!
ለሳቅ አይመችም ፥ የገለጥሁት ዶሴ
እንደመሸገ ነው ፥ አልስቅ አለኝ ጥርሴ!

ወደኋላ ዞሬ ፥
አንድ ሁለት እያልኩኝ ፥ ጀግኖቹን ስቆጥር
ከሩቅ አይሃለሁ!
ፊደላትን ቀርፀህ ፥ ልቤ ላይ ለመትከል ፥ ብቻህን ስትጥር!

እልፍ ህይወት ተከፍሎ
ሐበሻም ድል አርጎ ፥ ጦርነቱ አልቋል
ከድል ባሻገር ግን
ከፊደል ሲታገል ፥ አንድ ጀግና ወድቋል!

Filed in: Amharic