>

መረራ ጉዲና ሆይ ፤ ሸክምህ ከበደኝ (በፈቃዱ ሞረዳ)

(የጋዜጣ ድስኩር)
ከየት መጀመር እንዳለብኝ እንጃ፡፡ ከአምስት ኪሎ የሳይንስ ፋኩልቲ ክበብ ልጀምር? በእነዚያ ነፋሻማ ምሽቶች በክበቡ አናት ላይ ተቀምጠን ፅዋ ካነሳንባቸዉ አይረሴ ቀኖች፡፡
ሰዎች ‹‹ኢዲዩ›› እያሉ ከሚጠሩት የእንጦጦ መናፈሻ ? ከዚያ ብሶትና ጥብስን በፋርሶ ካወራረድንበት፣ ያረረ አንጀታችንን ይበልጥ ካሳረርንበት ልጀምር? ወይስ ከሞኒክ ካፌ? ማኪያቶ እየጠጣን የጋዜጣ ወሬ ከሰለቀጥንበት፡፡
ከእነዚያ አብረን ካሳለፍናቸዉ ቀኖች ዉስጥ በአንዱ፣ ከእኔ ተለይተህ ወደቤትህ ስትሄድ በዚያ በሬንጀር ቅብ ቶዮታ ላይ መትርየስ ጠምደዉ ከስድስት ኪሎ ጀምሮ አጅበዉ ቤትህ ደጃፍ ካደረሱህ የሕወሓት ሚሊሺያዎች ጉዳይ ልጀምር?
ከሲፒኤ በስተጀርባ በነበረዉ መኖሪያህ ዉስጥ ስለቆረጠምነዉ የአምቦ ቆሎ ፣ስለአነሳናቸዉ የግልና የሀገር ጉዳይ በማዉሳት ልጅምር?
በተለይም ከምርጫ 97 በፊት በሀገር ዉስጥ በነበሩት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መሐከል ያለዉን ልዩነት ለማጥበብና በምርጫዉ ሂደት ዉስጥ ዕጩዎችን ባለማደራረብ ጉዳይ ላይ (በተለይ በኦብኮና ኦፌዴን)፣ እንዲሁም ዉህደትን በመፍጠር ሃሳብ ላይ በዶክተር ነጋሶ ቤት ዉስጥ ካደረግናቸዉ ዉይይቶች ልጀምር? ዶክተር ነጋሶ ቤት የተመሰረተዉ Gumii nagaa በዚያዉ ፈርሶ ቀረ አይደል?
በምክክር ሂደቱ ላይ ኦሕዴድም እንዲሳተፍ ተጠይቆ አንዱ የኦሕዴድ የወቅቱ ቱባ ሹም ‹‹ በምክክሩ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኞች ነን፤ መረራ ካለበት ግን አንሳተፍም›› ካለበት ነገር ልጀምር? ከሰዉ ሁሉ ለምን አንተን እንደፈሩ ባላዉቅም፡፡
አፋን ኦሮሞ የሚናገር የብሮድካስትና የኅትመት ሚዲያ ለማቋቋም ሩጫ ላይ በነበርንበት ጊዜ ሁሌም በምናከብራቸዉ ወዳጃችን በአቶ ቡልቻ ቤት እናደርገዉ ከነበርነዉ ስብሰባ ልጀምር? እርሱ ጥረታችን ፈቃድ ካወጣን በኋላ፣ በዉስጥና በዉጭ ችግር ምክንያት ሳይሳካ ስለቀረበት ጉዳይ ለመነጋገር ጊዜ እስኪናጣ ድረስ ተበታትነን እንቅር? ከእርሱ ልጀምር እንዴ? ምክንያቱን አላዉቅም፡፡በስደትም ዓለም አልተለያየንም፡፡ አሜሪካ ደርሰህ እቤቴ ሳትመጣ የቀረህበት ጊዜ ስንት እንደሆነ አላዉቅም፡፡ ከሂዩስተን ዳላስ ስንሄድ፣ በሂዩስተንም ጎዳናዎች ላይ ስንነዳ ከተነጋገርናቸዉ ቁምነገሮች ልጀምር?
በተለይ ተስፋህ ስለካከመበት፣ ጥንካሬህ ስለተፈተነበት፣ ‹‹ እኔ ምን የተለየ ዕዳ አለብኝ? ይህን ሕዝብ ላደራጅ ብዬ ነዉ፡፡ ካልተደራጀን እንጠፋለን ብዬ ነዉ…›› ካልከኝ ልጀምር? ትግሉን መጠቀሚያ በማድረግ ለገንዘብ ያሰፈሰፉ ሆዳሞች ያበሳጩህ መስሎኝ ነበር፡፡
እነዚያ ‹‹ መረራ ለምን አልታሰረም›› እያሉ ሲያጉተመትሙ የነበሩ ‹‹ የኦዳ ሥር ቁማርተኛ›› ዲያስፖራዎችና ሚሊሺያዎቻቸዉ ከእነማን ቤት ማደር እንዳለብህ፣ ከእነማን ጋር መጠጣትና መብላት እንደሚኖርብህ ሊስተምሩህ ከቃጡት እዉነት ልጀምር? ፓርቲ ሲያፈርሱ፤መሪ ሲያነግሱ ዉለዉ የሚያድሩ እነዚያ የሶሻል ሚዲያ ላይ ነብሮች ዛሬ ሲያጨበጭቡልህ( ዉሸታቸዉንም ቢሆንም) ሳይ ደስ ይለኛል፡፡ እነርሱ ይፈሩ እንጂ እኔ ምንተዳዬ?
እነዚያስ ደግሞ፤ እነዚያ የዛሬ አርባ ምናምን ዓመት ከሀገር ሲወጡ ራሳቸዉን በከተቱበት ማሰሮ ዉስጥ ዛሬም ያሉ፡፡ ወይ ሳይበስሉ፣ ወይ ሳይከስሉ፡፡ እነዚያ ‹‹ የአንድነት ሥር ቁማርተኞች›› ፡፡ ለመፅሐፍህ የፊርማ ሥነስርዓት ጠርተናቸዉ ቀሩ፡፡ የቀሩበትም ምክንያት ‹‹ መረራ ወያኔ ነዉ፤ እንዴት የወያኔ መፅሐፍ እንገዛለን?›› ብለዉ እንደሆነ ያኔ ያልነገርኩህ በሳቅ እንዳትሞት ብዬ ነዉ፡፡
የመጡትስ ‹‹ ለምን በኦሮሞ ስም ፓርቲ ትመሰርታለህ? ኢትዮጵያዊ ሁን›› አሉህና በጎጣቸዉ ስም የተከሉትን ቤተክርስቲያን ሊሳለሙ ሹልክ ብለዉ ሄዱ አይደል? ‹‹ መረራ ስለኢትዮጵያ እንጂ ስለኦሮሞ አይሟገትም›› የሚሉትን የአንዳንድ ኦሮሞ ወገኖችህን ወቀሳ እንኳ ልብ ሳይሉ፡፡ ምስኪኖች ከዚያችዉ ማሰሮ ሳይወጡ ተንነዉ ሊያልቁ ነዉ፡፡
በዚህ አጋጣሚ አለቱን ወዳጃችንን ኃይሌ ተፈራንና ጓደኞቹን ሳላመሰግን ባልፍ የአባትህ Ayyaanaa ይጣላኛል፡፡
( ‹‹የእንትን ሥር ቁማርተኞች›› የሚለዉን ነገር ከዳንኤል ክብረት ነዉ የተዋስኩት፡፡ ‹‹ የመስቀል ሥር ቁማርተኞች››)
እና ከየት ልጀምር? እነሆ አንተም ታሰርክ፡፡ ተፈታህም፡፡ በወገኞችህ ተጋድሎ፡፡ ቁማርተኞቹም ዝም አሉ፡፡ የሚያዩት አስደንግጧቸዉ እንጂ የሚያወሩት ጠፍቷቸዉ ግን አይምሰልህ፡፡
ለመሆኑ ስኳሩ እንዴት አደረገህ? መድኃኒትህን እንዳትከታተል አድርገዉ እስር ቤት ዉስጥ የሚገድሉህ መስሎኝ ነበር፡፡ ዶክተር ጥላሁን ጅፋር እንኳ እዚያ የለ ከራሱ መድኃኒት ቀንሶ እንዳያበድርህ፡፡
ትዝ ይልህ እንደሁ ከሕመሙ ጋር በተያያዘ እጅህን የምታስርበትን (hand cast) እቤታችን ረስተህ ሄድክ፡፡እጃቸዉን አጣምረዉ ፎቶ ከአንተ ጋር የተነሱት ልጆቼ መታሰርህን ሲሰሙ ካሉኝ ነገር አንዱ ፣‹‹ እባክህን እስር ቤት ያስፈልገዉ ይሆናልና በቻልከዉ መንገድ ላክለት›› ብለዉ የተማፀኑኝ ነዉ፡፡ ማድረግ ግን አልቻልኩም፡፡ዕቃውን ግን ከልጆቼ ደበቅኩት፡፡ ጭቅጭቃቸዉ…
ልጆቼ በተለያየ ጊዜያት አስቀዉኝ ያዉቃሉ፡፡አስለቅሰዉኛልም፡፡ አንዱ ለቅሶዬ በአንተ የተነሳ ነዉ፡፡ ከአዉሮፓ ስብሰባህ በኋላ ወደሀገር ቤት ስትመለስ እንደሚያስሩህ አንተም ታዉቅ ነበር፤ የእኛም ስጋት ነበር፡፡ ይህንኑ ስጋቴን ለልጆቼ ሳጋራ ፣ ‹‹ ለምን መጥቶ ከእኛ ጋር አይኖርም? ንገረዉ›› አሉኝ፡፡አልነገርኩህም፡፡ የመታሰርህን ዜና ስነግራቸዉም ተወቀስኩ፡፡ ‹‹ ባትነግረዉ ነዉ›› አሉኝ፡፡
አንድ ወቅት እቤትህ ዉስጥ (አራት ኪሎ) ቁጭ ብለን ስለቤተሰብ ምስረታ አስፈላጊነት ስናወራ ፣ ‹‹ ትግሉን አንድ ደረጃ ላይ ሳናደርስ…›› ያልከኝ ትዝ አለኝና አለቀስኩ፡፡ ከሰዉ ዓይን ተከልዬ፡፡ ነገሬን ከዚህ ልጀምር?
ብዙ ደጋፊዎችህ እጅህን በካቴና ታስረህ ፍርድ ቤት ስትቀርብ አልቅሰዋል፡፡ እኔ አላለቀስኩም፡፡ አልተገረምኩምም፡፡ አንደኛ፣ ካቴናዉን አዉቀዋለሁ፡፡ ሁለተኛ፣ በጠላቱ እጅ ያለሰዉ ወደፍርድ ቤት ሲመላለስ በወርቅ ሠረገላ ላይ ተቀምጦ ሊሆን እንደማይችል ስለማምን ነዉ፡፡ እስረኛ ነህ፤ትታሰራለህ፡፡ በካቴናም፣ በቀበቶም፣ በገመድም…
ይልቁንስ ከእስር ተፈትተህ አምቦ ሄደህ ስታለቅስ ሳይህ አለቀስኩ፡፡ የእኔ ሕዝብ የሚገርም ሕዝብ ነዉ፡፡ በስቃዩ ያስለቅሰሃል፤ በደስታዉም ያስለቅሰሃል፡፡ ለዚህ ሕዝብ ምን ብታረግለት፣ ምን ብትሆንለት ነዉ ነፍስህ የሚረካዉ? ፈተና ነዉ አይደል?
አይተናል በፎቶና በቪዲዮ፡፡ የአጀቡን፣ የጠያቂህን ብዛት፡፡ የሰንጋዉን ፣ የበግ ሙክቱን መዓት፡፡እነአጫሉና ሙስሊም ወገኖችህ ሱፍ ሲያለብሱህ፤ አባትና እናቶች ፣ፎሌና ቄሮዎች ሲያነግሱህ አይተናል፡፡
ያ ሁሉ አክብሮት፣ ያ ሁሉ… የሆነዉ አሳሪዎችህን ለማናደድ አይደለም፡፡ ለከፈልከዉ ዋጋ የምስጋና ሽልማትም አይደለም፡፡ እንደገና ስለመወለድህ አዲስ ብስራት ነዉ፡፡ አደራ ነዉ፡፡ ሸክም ነዉ ወንድሜ፡፡
ያ ሕዝብ ሕልም አለዉ፤ ግብ አለዉ፡፡ ሕልሙ እዉን ወደሚሆንበት የሚያደርሰዉን መሪ ይፈልጋል፡፡ አንድ የሚደርገዉን መስኢ ይሻል፡፡ ‹‹እኛ ከኋላህ እንተማለን፤አንተ ምራን›› ነዉ መልዕክቱ፡፡ ሰምተኸዋል?
ወዳጄ ሆይ፤ያንን ሰንጋ፣ ያንን ሙክት አሁን እንዳትበላዉ፡፡ የትግል ጓደኞችህ እነበቀለ፣ ደጀኔ፣ አዲሱ፣ አልባናና ሌሎችም በሺህ የሚቆጠሩ ወገኞችህ ዛሬም እጃቸዉ በካቴና ዉስጥ ነዉ፡፡ አንተን ነፃ ያወጣህ ሕዝብ የእነርሱንም ነፃነት በአንተ መሪነት ለማየት ይፈልጋል፡፡በሬዉና ሙክቱ ከእነርሱም ነፃነት በኋላ ቢበላ አይመርም፡፡ አለበለዚያ ግን…
ወዳጄ፤ እንደገና መወለድህ፣እንደገና ቄሮ መሆንህ፣ እንደገናም አዲስ ኃይል ማግኘትህ ቢያስደስተኝም ይህ ሕዝብ የጣለብህ ሸክም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሳስበዉ ስለአንተ ደከመኝ፡፡ሸክምህ ከበደኝ፡፡ ፈራሁ፡፡
አንተ ግን አትፍራ፡፡ ወደኋላህ ዞረህ ተመልከት፡፡ ከማይደርቅ ምንጭ የሚፈልቅ የትውልድ እሳተ-ገሞራ ከበስተኋላህ ተከትሎህ እየፈሰሰ ነዉ፡፡ ‹‹ እሳተ- ገሞራ›› ያልኩበትን ምክንያት አታጣዉም አይደል? ካቅማማህ አንተንኑ…
ወደፊትህም ተመልከት፡፡ነፃነት፣ሠላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ አንድነት…የሰፈነበት የተስፋችን ምድር ብሩህ ሆኖ ይታያል፡፡ እንሂድ! ከዚህ ልጀምር ወጌን?

Filed in: Amharic