>
5:13 pm - Tuesday April 20, 2573

እኛ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስንል... (ሳምሶን አስፋው-ቋጠሮ)

ከቀናት በፊት  “በኢትዮጵያ ህዝብ ለመከበር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ብቻ በቂ ነው! ” በሚል ርዕስ ለንባብ ያቀረብነው ጽሁፍ ግልጽ ካልሆነላቸው አንባቢያን ጥያቄ አዘል መልዕክቶች ደርሰውናል። በቅድሚያ ለሁሉም ምስጋናችንን እያቀረብን ለእያንዳንዱ ጠያቂና ጥያቄ የነፍስ ወከፍ መልስ ከመስጠት ይልቅ ይህን ጽሁፍ ማዘጋጀት መርጠናል። 

አዎ! እኛ ኢትዮጵያ ስንል፡ ልዩነቶችን የማታስተናግድ፤ ከአንድ ቦታ ከተቆፈረ አፈር ፤ ከአንድ ወንዝ ከተቀዳ ውሃ ፤ ከአንድ ክምር ከተሰበሰበ ጭድ ተቦክታና ተዋህዶ የተገነባች ኢትዮጵያ ማለታችን አይደለም፡፡ሊሆንም አይችልም። ይልቁኑም እኛ ኢትዮጵያ የምንለው ብዝሃነትን መለያዋ ፤ አብሮነትን መርኋ አድርጋ ፤ በርካታና ዘርፈ ብዙ ልዩነቶች ላሏቸው ህዝቦች ማዕቀፍ ሆና የኖረቺውን ኢትዮጵያን ነው።

እኛ ኢትዮጵያ የምንለው፤ የዛሬውን አያድርገውና፤ የስልጣኔ ቀንዲል፤ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት-ምኩራብ…. በሚል አለም አቀፋዊና አህጉራዊ ክብር የምትታወቀውን ኢትዮጵያን ነው። አያት ቅድማያቶቻችን ዘርና ቋንቋ ሳይለያቸው ክፉዋን ላለማየት ክፏቸውን ያስቀደሙላትን ኢትዮጵያን ነው።

 ትልቅ ነበርንና ትልቅ እንሆናለን የሚለውን ቁርጠኝነትን የታጠቀ፤ ተስፋን የሰነቀ መርህ መሰረት አድርገን … ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለስ ዘንድ የአብዛኛው ዜጋ ፍላጎት እንደሚሆን የራሳችንን እምነት ያስቀመጥነውም ለዚህችው ኢትዮጵያ ነው።

ይህን እምነት ለመያዝ የበቃነውም ነባራዊውን የህዝባችንን ስሜት ከአኩሪው የአበው ታሪክ፤ ወቅታዊውን የህዝባችንን ስሜትና ፍላጎት ከወቅቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ሁነቶች በመገንዘብ ነው።

የለማ መገርሳን ወቅታዊ እንቅስቃሴና ተከትሎም ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያገኘውን አዎንታዊ ግብረ- መልስ እንደ መገለጫ ያቀረብነውም የህዝባችን ስሜት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል ቅርብ መሆኑን በጨረፍታም ቢሆን ያሳይልናል ብለን እንጂ የግለሰቡን የትናትና የዛሬ ማንነት መርምረንና ሚዛን ላይ አስቀምጠን ድጋፍ ወይም ነቀፌታ ለመሰንዘር አይደለም።  ይህን የማድረግ ፍላጎቱም ፤ ሃላፊነቱም የለንም።

ቴዲ አፍሮ ስለ ኢትዮጵያ ሲያዘምር፤ ታማኝ በየነ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲደክም፤ ፓስተር ቶሎሳ ጉዲና ቅዱስ ቃሉ ኢትዮጵያን እንጂ አንድም ዘር እንደማይጠቅስ ሲያስተምሩ፤ ደስ የሚለው ኢትዮጵያዊ ለማ መገርሳም “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ሲል ደስ እንዳለው ነው የገለጽነው ። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድስና የሚያደምቅ ንግግርም ሆነ ተግባር ኢትዮጵያዊውን ያስደስታል ነው ያልነው።

አዎ! ኢትዮጵያዊነት ስንልም፡ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱ ልዩነቶች ያላቸውን ህዝቦች አቅፋ የያዘቺው ሃገር ተወላጅ የሆነ ዜጋ ሁሉ የጋራ ማንነት ማለታችን ነው።

ማንነታቸውን በጎሳቸው ጣራና ግድግዳ ስር አውለው ኢትዮጵያዊነትን እንደማንነት ላለመቀበል የሚሹ ወገኖች ይህን የኛን የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትርጉም ባይቀበሉ ወይም ከስህተት ቢጥፉት አይገርመንም። ለ27 አመታት የዘለቀው ዋናው የሃገራችን ችግርም ይኽው ነውና።

“በኢትዮጵያ ህዝብ ለመከበር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ብቻ በቂ ነው” በሚለው ርዕስ የገለጽነውም ኢትዮጵያ የምትባለውን የጋራ አገርና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን የጋራ ማንነት የሚቀበል ዜጋ ሁሉ የኔ የሚላት አገር ስትታፈርና የማንነቴ መገለጫ የሚለው ኢትዮጵያዊነቱ ሲከበር ይደሰታል የሚለውን ጥሬ እውነት ነው።

ከተላኩን መልዕክቶች እንደተረዳነው አብዛኞቻችሁ፣ በጽሁፋችን የወቅቱን የሃገራችንን የፖለቲካ ውጥንቅጥ አድበስብሰን ለማለፍና የማይጨበጥ የአንድነት ተስፋ ለማጫር እንደሞከርን ተሰምቷችኋል።

በኛ እምነት ይህ የአረዳድ ችግር እንጂ የጽሁፋችን አብይ አላማ ችግሮችን አድበስብሶ ማለፍ ወይም የማይጨበጥ የአንድነት ተስፋ ለማጫር አልነበረም። ሊሆንም አይችልም።

ከላይ በዝርዝር እንደገለጽነው የጽሁፋችን አላማ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከምንምና ከማንም በላይ የኔ ለሚላት ሃገሩ ለኢትዮጵያ ህልውናና ለኢትዮጵያዊ ማንነቱ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ማመላከት ብቻ ነው። የሃገሩ ህልውናና የዜግነት መብቱ እስከተከበረ ድረስ ቀሪውን ችግር በሰላም ለመፍታት እንደማይቸገር፤ ቀና ልቦናና ትዕግስት እንዳለው ማሳየት ብቻ ነበር።

ከሃገሩ ህልውና በመለስ ላሉ ጥፋትና ስህተቶች የይቅርታ ልብ ያለው ህዝብ መሆኑን ማሳየት ብቻ ነው የፈለግነው። ከዚህም ተያይዞ አድምቀን የገለጽነው፤ ወያኔ መራሹ መንግስት ይህን የህዝብ ፍላጎትና መሻት ተረድቶ ሊለወጥ ያለመቻሉ የፈጠረብንን ገረሜታ ነው። ወያኔ ላለፉት 27 ዓመታት የፈጸማቸው ጥፋቶች ይቅር ባዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍጹም ይቅር በማይለው በሃገሩ ህልውናና በማንነቱ ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸው ነው ያመላከትነው ።

በጽሁፋችን “አብዛኛው ኢትዮጵያዊ” ስንልም ለዘመናት ተከባብሮና ተፈቃቅዶ የኖረውን መላውን ህዝብ እንጂ ይህን ወይም ያንን ህዝብ እወክላለሁ ብሎ በፖለቲካው መድረክ የሚሳተፈውን ወገን ብቻ አይደለም።  እንዲያውም በፖለቲከኞች ሰፈር በአብዛኛው እንደ ህዝብ ጥያቄና ችግር የሚጠቀሱና የሚነሱ አጀንዳዎች በህዝባችን ጉያ ውስጥ ያለመገኘታቸውን ስናስተውል፤ ፖለቲከኞች የህዝብን ስሜትና ፍላጎት በትክክል ካለመተርጎም አልያም ሆን ብሎ ከማዛባት የሚፈጥሩት ችግር ጎልቶ ይታየናል። ስለዚህም የህዝባችንን ትክክለኛ ስሜት፤ ፍላጎትና ጥያቄ በፖለቲከኞች አጀንዳ ውስጥ በትክክል ስለመንጸባረቁ  በጥንቃቄ መፍተሽ ይኖርበታል የሚል ዕምነት አለን።

ይህ ስንል በህዝባችን ውስጥ በአብዛኛው የጎሳ-ፖለቲካ የወለዳቸው የሚታዩ የሚዳሰሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉም እንረዳለን። ይሁንና እነኚህ ችግሮችም ቢሆኑ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሊፈቱ እንደሚችሉ እምነትታችን ጽኑ ነው። እንዴት ይፈታሉ?…ይህ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ የሚችለው፤ በችግሮቹ ዙሪያ ያሉ ወገኖችን ሁሉ ያለምንም አግላይነት በሚያሳትፍ ውይይትና ምክር ብቻ ነው።

ማጠቃለያ፡ ከደረሱን መልዕክቶች በመነሳት ከሞላ ጎደል ቀደም ባለው ጽሁፍ ውስጥ ብዥታ የፈጠሩ ሃሳቦችን ለማጥራትና የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሞከርን ተስፋ በማድረግ አስተያየት ለሰጣችሁን ሁሉ በድጋሚ ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን።

Filed in: Amharic