>

በየቀኑ ስለሚገደሉ፣ሥለሚታሰሩ፣ሥለሚፈናቀሉ ወገኖቻችን...(አቤነዜር ይስሃቅ)

የበፊቱን ለጊዜው ተትን ባለፉት 2 ዓመታት ወይም በ730 ቀናት ውስጥ ብቻ ኢትዮዽያ ውስጥ ከፖለቲካ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በየቀኑ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ። ቁጥሮችም የሚናገሩት ይሄንን ነው። ትንሽ ምሳሌ እንመልከት።

=> ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ5,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ይሄ ማለት በቀን በአማካይ 7 ሰዎች ከፖለቲካ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተገድለዋል ማለት ነው። እነዚህ ወገኖቻችን የተገደሉት ደግሞ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በሐይማኖት በዓላት ጊዜ፣ በትምህርት ተቋማት ውስጥ በኢህ አዴግ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ፣ በብሔራቸው የተነሳ ኢላማ ተደርገው. . . ነው።

=> ባለፉት 2 ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በዋናነት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ከ150,000 በላይ ሰዎች ታስረዋል። ይሄ ማለት በአማካይ በቀን 205 ሰዎች ይታሰሩ ነበር ማለት ነው። እነዚህ ወገኖቻችን የታሰሩት በተናጠልና በጅምላ ነው። በእስር የቆዩባቸው ጊዜያት የተለያዩ ነው። በርካቶች torture ተደርገው፣ ለሥነ ልቦናና ለአካል ጉዳት ተዳርገው የተፈቱ፣ በዚያው የተገደሉም አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሥልጠና ተሰጥቷቸው “አይደገምም” የሚል ካኔተራ በግድ ለብሰው የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ድረስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በየማጎሪያው ይገኛሉ።

=> ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ800,000 በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ይሄ ማለት በቀን በአማካይ በቀን 1,095 ሰዎች ይፈናቀሉ ነበር ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ ከ500,000 የማያንሱት የኦሮሞ ብሔር አባላት ናቸው።

=> በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች የተመደቡበትን ዩኒቨርስቲ በተመተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰዋል።

=> በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት 2 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮዽያውያን ሀገር ለቀው ተሰደዋል።

እየኖርን ያለነው ከዚህ ዕውነታ ጋር ነው። የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ነው። እናም ይሄ አምባገነን መንግስት በወንበሩ ላይ እስካለና ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር እስካልተካሄደ ድረስ ወደፊትም ከዚህ በላይ ሰዎች በየቀኑ መገደላቸው፣ መታሰራቸው፣ መፈናቀላቸውና መሰደዳቸው. . . አይቀርም።

ማስታወሻ:- ቁጥሮቹን ያሰባሰብኩት ራሱ ኢህአዴግ በተለያዩ ሀላፊዎቹና ተቋማቱ በኩል በተለያዩ ጊዜያት የሰጣቸው መግለጫዎችና ሪፖርቶች፣ የክልል መንግስታት የሰጧቸው መግለጫዎች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያቀረቧቸው ሪፖርቶች፣ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች የዘገቧቸው ነገሮች፣ ታስረው የተፈቱና ታስረው ያሉ የፖለቲካ እስረኞች የተናገሯቸው ነገሮችን በማየት ወዘተ ነው ።

Filed in: Amharic