>

ከቴዲ አፍሮ እና ከኢሕአዴግ የፌደራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ የገባው ማን ነው? (ውብሸት ሙላት)

የቴዲ አፍሮን “ኢትዮጵያ” የሚለውን አልበም ብቻ በምሳሌነት እንውሰድ፡፡  የአልበሙ መጠሪያ “ኢትዮጵያ” ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚል ዜማም አለው፡፡ በእዚህም፣ ስለ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት ዘፈነ፡፡  አስቀድሞም የተለቀቀውም ይሄው ዜማ ነው፡፡ የፌደራሊዝም ግብና ዓላማ አንድነትን ማምጣት ነው፡፡

በዚሁ አልበሙ ላይ “አና ኛቱ”  (anna nyaatu) ኦሮምኛ፣”ኦላን ይዞ” (ሲዳማ)፣”አደይ” (ኩናማና ትግርኛ)፣”ዐጼ ቴዎድሮስ” (በተወሰነ መልኩ አፋርን እንደሚያነሳ ልብ ይሏል)፣”ናት ባሮ” (ጋምቤላ) የተሰኙ ዜማዎች አሉት፡፡

እንግዲህ፣ በአንድ አልበም ላይ ብቻ ይሄን ያህል የተለያዩ ብሔሮችን ዕሴት እና መነሻ ሐሳብ በመውሰድ አዚሟል፡፡ ሁሉም ስለፍቅር፣አንድነት፣አብሮነት እና አገራዊነት የሚሰብኩ ናቸው፡፡

ፌደራሊዝም ለልዩነት ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ልዩነትን አይክድም፡፡ ብዙኃነትን አይክድም፡፡ ይሁን እንጂ፣ልዩነትን እና ብዙኃነትን ሁልጊዜ በማጉላት ለአንድነት፣አብሮነት፣አገራዊ ፍቅር ተጻራሪ እና ተገዳዳሪ እንደሆኑ ማድረግ የፌደራሊዝም ግብም ዓላማም አይደለም፡፡

ቴዲ አፎሮም ያደረገው ይሄንኑ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ አግላይ የሆነ አንድነትን ከዘፈኖቹ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ፣እነዚህን ከአንድ አልበሙ ብቻ የተጠቀሱ እንጂ ሌሎች ሥራዎቹን በዝርዝር ብንመለከታቸው  የተለያየ ሃይማኖትና ብሔር ቢኖረንም በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ ያሉንን የአንድነት ዕሴቶች ያጎላቸዋል እንጂ አይክዳቸውም፡፡

በመሆኑም፣ኢሕአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት ልዩነትን ብቻ በማጉላት በርካታ የአንድነት ዕሴቶቻችንን ሲያቀጭጭ መኖሩ ከፌራሊዝም ጽንሰ-ሐሳብና ግብ በተቃራኒው ሲጓዝ ኖሯል፡፡ በተቃራኒው፣ቴዲ አፍሮ ልዩነቶቻችን እንዴት እንደማይነጣጥሉን ለአንድነታችን ሳንካ እንደማይሆኑ በዜማው ሲፋለም ኖሯል፡፡ ታዲያ፣ከኢሕአዴግና ከቴዲ አፍሮ ፌደራሊዝም የገባው ማን ነው?

Filed in: Amharic