>

"አቶ ለማ መገርሣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ላይ ስማቸው ከፍ ብሎ ተሰቅሏል! (ጥሩነህ ይርጋ)

በዚህ ሰው ዙሪያ ደጋግሜ ስለሞጫጨርኩ ምን ነካው እንዳትሉኝ እንጂ፥ ሰሞኑን የእኝህ ወጣት ፖለቲከኛ ንግግር እኔንም ቀልቤን ገዝቶታል። መከራ ለጠናበት ህዝቤ ሰላምና ነጻነት ከመመኘት የተለየ ሌላ ፍላጎት የለኝም። የማይዋሽ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከወትሮው የተለየ ከመከራዋ የሚታደጋት አንድ ሰው ለማግኘት ምጥ ላይ እንዳለች መረዳት ችያለሁ።

ሰሞነኛው የአቶ ለማ መገርሣ ክስተት ለብዙዎች እንዳልተመቸ በእያቅጣጫው ከሚሰነዝሩ ባይተዋር አስተያየቶች መረዳት ይቻላል፥ ከአውራምባው ታይምስ አዘጋጅ ዳዊት ከበደ እስከ ትግራዩ ገዥ አቶ አባይ ወልዱ፥ ከኢታማዦር ሹም ሳሞራ እስከ ተራው የወያኔ ወታደር፥ ከሆዳም የክልል ሹማምንት እስከ አቃጣሪ ካድሬ ድረስ የለማ መገርሣ ነገር ትኩሳት ለቆባቸዋል።

ኦሮሞውን ወጣት በአማራ አድርባይ፥ አማራውን ወጣት በኦሮሞ ገራፊ፥ ቆመው በወፌላላ ሲያስደበድቡ የሰነበቱ የወያኔ ስልጣን ጠባቂዎችና የእስር ቤት ዘበኞች ልባቸው መሸበር ጀምሯል፥ ባይገርማችሁ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ያዙኝ ልቀቁኝ ይሉ የነበሩ የተከዜ ማዶ ተወላጆች፥ ትግርኛ ሁለተኛ ቋንቋየ ነው የማለት ያክል እየተሸማቀቁ ነው የሚል ጥቆማ ደርሶኝ አስቆኛል።

የእኝህ ለማ የሚባሉ ሰው በአንድ ነን መንፈስ ተጠምቆ ከፋፋዩን ስርዓት ረጋግጦ ከተደፋባቸው የዘረኝነት መርገም ድንገት ተመንጥቆ መውጣት ያስደነገጣቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ከዚያና ከዚህ ሲረግጡና ፍርግጥ ፍርግጥ ሲሉ እየታዩ ነው። በዚህም በዚያም እኛ ያላመጣነው ለውጥ አይረባም አይነት ሃሳቦች ሲሰነዘሩ እየሰማን ነው፥ የዚህ ግን ትርፉ ትዝብት ነው።

እንደ እኔ ሃሳብ እሄ ደርሶ ቄስነት ቢቆምና በአዲስ ራዕይ የተከሰተውን የኦሮሞ ፊታውራሪ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጅ አረጋግቶ ከእነ ሰራዊቱ ወደ መሃል ማስገባት ጥበብ ነው እላለሁ፥ መጭው የኢትዮጵያ መሪ ከእነዚህ ሁለት ወጣቶች ውስጥ እንዳይሆንም ጥርጣሬ አድሮብኛል። የዶክተር አብይ እና የአቶ ለማን ንግግር በጥሞና አዳምጫለሁ፥ ቢቻል በሚስጥርም ሆነ በገሃድ መተባበር ካልሆነ በዝምታ ማየት ማስተዋል ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን ለማ ካድሬ ነበር፣ ትላንት እሄን ብሏል እና ነገ ያን ሊያደርግ ይችላል የሚሉት ከንቱ ትችት ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት አደገኛ ሁኔታ የሚያባብስ እንጅ፥ ምንም የፖለቲካ ትርፍ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም።
አቶ ለማ መገርሣ የኢትዮጵያ ማንዴላ ለመባል ገና ብዙ መጓዝ ቢኖርበትም፥ ትላንት ባህርዳር ላይ በተናገረው ትልቅ የኢትዮጵያዊነት ቃልኪዳን መሰል ስብከትና፥ በታዋቂ የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኝ የኦሮሞ ሙዚቀኞች የተዘመረው የዓንድነት ዝማሬ አእላፍ ጽንፈኛ ወጣቶችን እንዳለዘበ፥ ብዙ በቂም የቆሰሉ ልቦችን መጠገን እንደጀመረና፥ ከሁሉ በላይ ለዘመናት በወያኔ መሃንዲስነት ሲዘራ በኖረው የዘረኝነት መርዝ ላይ ውሃ እንደቸለሰበት ለመገመት የፖለቲካ ሊቅ መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም።

እውነቱ ግን ከምስራቅም ይምጣ ከምዕራብ፥ ከሰሜንም ይምጣ ከደቡብ፥ ኦሮሞውም ይሁን አማራው ሕዝባችን የፈለገው እውነተኛ ለውጥ ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቡ ያረገዘው ከሙሉ ነጻነት ያነሰ ሽርፍራፊ መብት የማያስታግሰው የዲሞክራሲ ጥማት ነው።
ስለዚህ እሄን ሰው በጥርጣሬ ማየት ለሃበሻ ፖለቲካ እንደብልጥነት ቢቆጠርም መቃወም ጅልነት ነው ለማለት እፈልጋለሁ። ለመሆኑ እናንተስ እነማናችሁ፥ እስከ ዛሬ ምን ሰርታችኋል? አሁንስ የያዛችሁልን የተሻለ ነገር ምንድነው ለሚል ጥያቄ መልስ ይዛችሁ መሆን ዓለበት ለማለት ነው።

በሌላ በኩል ግን አቶ ለማ መገርሣ የተመኘነላቸው ታላቅነት ቀርቶ፥ የበሰበሰ ስርዓት ለማስቀጠል በማሰብ ደብረጽዮን የተባለውን የወያኔ ወጠጤ በተሃድሶ ካባ ሸፍነው ቤተመንግስት ለማስገባት ከሆነ የሚንሳፈፉት፥ ውርደቱ ለራሳቸው፥ መከራው ለህዝባቸው መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል እንጅ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገው ለውጥ ይመጣል፥ በውድ ቢቀር በግድ፥ በክብር ቢቀር በውርደት ስልጣን ለህዝብ ያስረክባሉ።

ለወያኔ መሽቶበታል፥ ድል የሕዝብ ነው
ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል።”

Filed in: Amharic