>

ዳግማዊ ኦሮማይ (በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

‹‹ስለ ልዑላኑ ማውራት ከአንገት ያሳጥራል››

ኒኮሎ ማኪያቬሊ

ለበዓሉ ግርማ ሞት ምክንያት የኾነው፣ ‹‹ኦሮማይ››በሚል ርእስ የጻፈው መጽሐፍ እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡እንደ እርሱ አተረጓጎም፣ ኦሮማይ ማለት አለቀ፣ ተፈጸመ፣ ሰዓቱ ደረሰ የሚል አንድምታያለው ቃል ነው፡፡የበዓሉ ትረካ የደርግን ሥርዓተ መንግሥትማብቂያ የሚጠቁም ሲኾን፣ኒኮሎ ማኪያቬሊየዛሬአምስትመቶ ዓመት፣ ‹‹ስለ ልዑላኑ ማውራት ከአንገት ያሳጥራል››እንዳለው የበዓሉምመጨረሻ በዚኹ መንገድ ተጠናቋል፡፡

የዚህ መጣጥፍ ዋና ዓላማ፣ በዓሉ፣ ‹‹ኦሮማይ›› በሚለው መጽሐፉ የደርግ ሥርዓት እያበቃለት መኾኑንእንደጠቆመው፣ እኔም በአኹኑ ወቅትበአገራችን እየተከሠተያለውቀውስ፣ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ማብቂያው እየተጓዘ መኾኑን እንደሚያመለክትለማሳየትነው፡፡ለመጣጥፌ ‹‹ኦሮማይ››የሚለውን የበዓሉን ቃል በመዋስና የእርሱን ትረካ እንደ ‹‹ቀዳማዊ ኦሮማይ››በመውሰድ፣ አኹን ኢሕአዴግ ያለበትን የፖለቲካና የሥርዓትቀውስ ‹‹ዳግማዊ ኦሮማይ›› ብዬዋለኹ፡፡ እዚኽ ላይ ቀዳማዊም ኾነ ዳግማዊ ኦሮማይ የአንድን ሥርዓት የፍጻሜ ደውል የሚያስተጋቡ መኾናቸውን ልብ ይሏል፡፡

ኢሕአዴግየሚመራውን ሥርዓት ከኦሮማይ ኹኔታጋር አዛምዶ ለማየት የሚያስችሉ በርካታ መገለጫዎችቢኖሩም፣ ለዚኽ ጽሑፌየሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች እንደማሳያ አቀርባለኹ፡፡

I. አገር በጄ

በዚኽ ነጥብ የማነሣውዋነኛ ርእሰጉዳይ፣ ከኢሕአዴግ በፊት የነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች የነበረባቸውን ግድፈቶችበማስወገድ፣ ለሕዝቦች ነጻነት እናለጠንካራ አገራዊ አንድነትዋስትና በሚል መርሕ የተመሠረተውፌዴራላዊ የፖለቲካ ሥርዓት መከተል የሚገባውን ፈር ለቆ፤ከዚኽ በፊት‹‹አገር በጄ›› ብለው እንደተነሡት ነገሥታት ኢሕአዴግም፣ ያንኑ የጠቅላይነት ሥርዓት በፓርቲ የበላይነት እንደተካው ለማሳየት ነው፡፡

ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ አሰባስበው በአሰናዱትና፣‹‹Kasa and Kasa›› በሚል ርእስ በታተመው መጽሐፋቸው፣ስለ ዘመነ መሳፍንት አስደናቂ እና ፈር ቀዳጅ የታሪክ እይታ ያላቸው ነጥቦች አቅርበዋል፡፡እንደ ፕሮፌሰሩ አቀራረብ፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ቀደም ሲል ከነበረው የአገዛዝ ሥርዓት የተለየና አዲስ ሥርዓትመሥርተዋል፡፡ይህንኑም አዲስ ሥርዓት፣‹‹አገር በጄ›› የሚል ስያሜ ሰጥተው ካብራሩት ሦስት ምሁራን(ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እና ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል) መነሻ ሐሳብበመውሰድ የራሳቸውን ትንተና አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በዚኹ ትንታኔአቸው፣ ዐፄ ቴዎድሮስ‹‹አገር በጄ›› ብለው መሳፍንቱንና መኳንንቱን እንዲኹምከፍተኛ ማዕርግ ያላቸውን ባላባቶችወደ ጎንበመገፍተር በምትካቸው ራሳቸው በመረጧቸውና ዝቅተኛ የሹመት ደረጃ ባላቸው ምስለኔዎች ማስተዳደር እንደ ጀመሩ አብራርተዋል፡፡
እንግዲኽ ይህ በዐፄ ቴዎድሮስ የተወጠነው የ‹‹አገር በጄ››መርሕ ነው፣ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ ድረስ ተጠናክሮ የቀጠለው፡፡ይህ መርሕበዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ይበልጥ ተጠናክሮ፣ ‹‹ጠቅል››የሚል ስያሜ በመያዝ ሙሉ ለሙሉጠቅላይ አሐዳዊ ሥርዓት ኾነ፤ ደርግም ቢኾን ይህን አሐዳዊ ሥርዓትበሶሻሊስት ሥርዓት መርሕ አስቀጠለው፡፡

በደርግ ውድቀት ዋዜማ የኢሕአዴግ አዲስ ሕገ መንግሥት ተረቆ አገሪቷ፣ ወደ አገር በጃችን (ፌደራላዊ) ሥርዓት መሸጋገሯን ይደነግጋል፡፡ ይህንንም የፌደራል ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አገሪቱ በተለያዩ የክልል መንግሥታት ተዋቀረች፡፡ ይኸው፣ ሕዝቦችን የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የሚያደርግ ነው በሚል መርሕ የተመሠረተው አዲሱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጥቂት መንገድ ከተጓዘ በኋላ በሒደት፣ አገር በጃችን ቀርቶ አገር በፓርቲዬ መኾን ጀመረ፡፡

በዚኽ የ‹‹አገር በጄ›› መርሕ፣አንድገዢ ፓርቲ ፍጹም የበላይነት ከተቀናጀ በኋላየፈለገውንና የተመቸውን የክልሎች ግዛት እና ሀብት፣ ‘የፓርቲዬና እኔ ወክዬዋለኹ የሚለው ሕዝብ ንብረት ነው’ ብሎ በተስፋፊነትቢራመድየሚያስገርም አይኾንም፡፡የገዢው ፓርቲ የበላይነት ሥርከሰደደ በኋላ የሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በእጅጉ እየተገደበ ሔዷል፡፡
በየክልሉ የሚነሡየማንነት ጥያቄዎች፣በኢንቨስትመንት ስም የሚካሔደው የመሬት ወረራ፣ ‘ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም የላቸውም’ በሚል ሰበብ የሕዝቦችን ሉዓላዊነትና የራሳቸውን ክልልበራሳቸው የማስተዳደር መብት የመጣስ ችግሮች፤ በአኹኑ ወቅት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

አገርበጄበሚለው ፅንሰ ሐሳብ፣ ነገሥታቱበተበታተነ መልኩ በተለያዩ መሳፍንት ይተዳደሩ የነበሩ ግዛቶችን አዋሕደው አገራዊ አንድነትንአጠናክረዋል፡፡ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ግን፣ ለአገር አንድነትየነበራቸውን ትልቅ ግምትና ቦታ ያኽል፤ለሕዝቦች ነጻነት፣ማንነትናመብትመጠበቅም ተገቢው ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ሕገ መንግሥት ቀርፆ ፌዴራላዊ ሥርዓትሲመሠርት፣ የግዛት አንድነት ብቻ ሳይኾንየሕዝቦች ነጻነትም ለአንድ አገር ህልውና አስፈላጊ ነው፤ በሚል መርሕ ከአሐዳዊ አገዛዝ ወደ ፌዴራላዊ አገዛዝ ማለትም ከ‹‹አገር በጄ›› ወደ ‹‹አገር በጃችን›› ለማሸጋገር በማለም ነበር፡፡

የዚኽምሽግግር ዓላማ፣ የአገሪቱን አንድነት አስጠብቆ ለዜጎች መብትንና ነጻነትን የሚያጎናጽፍ የፌደራል ሥርዓትን በሕገ መንግሥት ለመመሥረትና ሕገ መንግሥታዊነትንለማስፈንነበር፡፡ይህ ዓላማምኢትዮጵያ፣ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አገር መኾኗን በመገንዘብ የአገሪቷን አንድነት ለማስጠበቅና የሕዝቦችን መብት ለማስከበርነበር፡፡

ነገር ግን፣ የኢሕአዴግንአገዛዝ ስንመለከት፣ አገር በጄ ወይም አገር በፓርቲዬ የሚለው አካሔድ፣ የአገሪቱን የአንድነት ጉዞም ኾነየሕዝቦችን የነጻነት እና የመብት ፈለግ አልተከተለም፡፡ ይልቁንም የተወሰኑ ወገኖችን ጥቅምና የበላይነትማእከልበማድረግ፣ ነገሥታቱ ያስጠበቁትን የአገር አንድነት በማፋለስና በፌዴራሊዝሙ አስከብረዋለው ያለውን የአገር አንድነትም ኾነየሕዝቦች መብት እናነጻነት በመጋፋትና በመፈታተን አዝማሪው እንዳለው‹‹…ኹለተኛ ጥፋት››ኾኗል፡፡

II. ኢ-ዴሞክራሲያዊነት

የኢሕአዴግየፖለቲካ ሥርዓት ሲጀምር፣ ሕገ መንግሥት በወረቀት ላይ አርቅቆ በአንድ በኩል፣ ከአሐዳዊ ወደ ፌደራላዊ ሥርዓት ሽግግር ሲደነግግ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ከግለሰባዊ አገዛዝ፤ የሥልጣን ክፍፍልን መሠረት ወደ አደረገ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ለመግባት የሚያስችል መንገድ ከፍቶ ነበር፡፡ እዚኽ ላይ ቁልፍ ጉዳይ የሚኾነው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ ሠናይትልሞች አኹንባለንበት የፖለቲካ ምዕራፍ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ስንጠይቅ ነው፡፡

ይህንጥያቄ ይዘን፣ የኢሕአዴግንየ21 ዓመት የሕገ መንግሥት ጉዞ ስንገመግመው፣ ሥርዓቱ ሕገመንግሥትአርቅቆ ቢነሣም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓተወግን ሊጎናጸፍ ግንአልቻለም፡፡ ይኸውም ኢሕአዴግ፣ ሕዝቦችንለሉዓላዊ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ከማብቃት ይልቅ በጥቂት ሰዎች እንዲከማች ያደረገ፤ ሕገ መንግሥትን ማጽደቅ እንጂ ሕገመንግሥታዊነትን ያላሰፈነና በኹሉም መልኩ የበላይነት የተጎናጸፈ ሥርዓት መኾኑ ነው፡፡ ለዚኽም እውነታ የሚከተሉትን ነጥቦችበማሳያነት ማቅረብይቻላል፡፡

አንደኛ፣ማንኛውም ዴሞክራሲ በመሠረቱ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስገድዳል፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር በምናይበት ጊዜ፣ ሥርዓቱ፣‹‹የፖለቲካ ሥልጣንን ለሕግ አውጭው፣ ለሕግ አስፈጻሚውና ለሕግ ተርጓሚው ያከፋፈለና የመንግሥት ሥልጣንን የገደበ ነው፤›› ቢባልም፤ የሕግ አስፈጻሚው ክፍል በአንድ በኩል ፌዴራሊዝሙን በሌላ በኩል ደግሞ፣በሕግ አውጪው እና በሕግተርጓሚው ላይ ትልቅ ጫና በማሳረፍ ሥልጣናቸውንበእጅጉ ገድቦታል፡፡ በመኾኑም የሕግ አስፈጻሚው ተቋምራሱን እያፋፋና እያጠናከረ በአንፃሩሌሎቹን የመንግሥትተቋማት እያሽመደመደ ሔዷል፡፡

ኹለተኛ፣ ከአገራችንም ኾነ ከሌላው አገር ታሪክ እንደምንረዳው፣ ሕግ ለነጻነት ትልቅ ዋልታ ነው፡፡ በመኾኑም የአንድን አገር ፍትሕም ኾነ ነጻነት ለማስከበር የፍትሕ ተቋማትበነጻነትና በገለልተኛነት መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው፡፡ ኾኖም በአገራችንየፍትሕ ተቋማት የራሳቸው ልዕልና ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፡፡የራሳቸውን ልዕልና ያላስከበሩ ተቋማት ደግሞ የዜጎችን ነጻነት ያስከብራሉ ለማለት አይቻልም፡፡ በዚኽም የተነሳ የሕግ የበላይነት ሳይኾን የፖለቲካ ፍላጎት የበላይነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሕግ ባለሥልጣናትን መቆጣጠር ሲገባው በተቃራኒው ባለሥልጣናት ሕግን እንዳሻቸው ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡ በመኾኑም አገሪቱን የሚያስተዳድሩመሪዎች የሕግ ማህቀፍ ሳይጣልባቸው በዘፈቀደ ሕግ እያወጡ ለፖለቲካ መሣርያነት እንዲጠቀሙበት ኾኗል፡፡

ሦስተኛ፣ማንኛውም ሕገ መንግሥት በዜጎች እናበመንግሥትመካከል የሚገኝ የውልሰነድ ነው፡፡ ይኹንና የውል ፍጥጥሙን፣በብሔር እና በመንግሥት መካከል ያደረገው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን፣ለዜግነት ተገቢውን ቦታና ዋጋ አልሰጠም፡፡መኾኑም ብሔር የሚለው እሳቤ ጎልቶ ሲቀርብ፣ ዜጋ የሚለውን እሳቤ አኮስሶታል፡፡ይህን የዜጋ እሳቤ ማኮሰሱ ሦስት ዐበይት ችግሮችን ፈጥሯል፡፡

አንደኛው፣ ዜጎች በብሔራቸው ከተመደበላቸው ክልል ውጭ ተንቀሳቅሰው መኖር እንዳይችሉአድርጓቸዋል፡፡ኹለተኛው፣ከተለያዩ ብሔሮች የሚወለዱትንና ራሳቸውን ከብሔር ማህቀፍ ያወጡ ዜጎችን ብሔር አልባ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል፡፡ ሦስተኛው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤሎችን፣ ‹‹የተመረጡ ሕዝቦች›› እንደሚላቸው ኹሉ፣ በእኛ አገር የፖለቲካ ሒደትም በአገሪቷ ውስጥ ካሉ ብሔሮች መካከል‘የተመረጠ ብሔርና ሕዝብ’በሚል መድልዎ ይካሔዳል፡፡

ሥርዓቱ ፍጹም የበላይነትን ያሰፈነ ለመኾኑ አራተኛው ማሳያ፣በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የዴሞክራሲግብ የሚሠምረው፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚተገበሩ ፖሊሲዎችን ከማርቀቅ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ያለው ሒደት፣ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሲከናወን ነው፡፡ በዚኽ ረገድኢሕአዴግየሚያወጣቸውፖሊሲዎች፥ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ፣ የሕዝቡን አስተያየት ያካተቱና የሕዝቡን ይኹንታ አግኝተው የሚተገበሩ አይደሉም፡፡ይልቁንም የምናወጣቸው ፖሊሲዎች እና የምናስፈጽማቸው ተግባራት፣ትክክለኛውን አቅጣጫ የተከተሉ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ የተለያዩ ሐሳቦች እና አመለካከቶች በግልጽ እና በሐቅ እንዲንሸራሸሩ ቦታ አይሰጡም፡፡ይህ ፍጹም ርግጠኝነት ለዴሞክራሲማበብ ትልቅ መሰናክል እንደሚኾንመረዳትተስኗቸዋል፡፡ ይህም ሕዝቦች በነጻነት ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ እናየሚደመጡበትተቋም (የብዙኃን መገናኛ) በአገሪቷ ውስጥ እንዳይኖር ምክንያት ኾኗል፡፡

III. ሙሰኝነት

በአማርኛ፣‹‹ሙስና›› በእንግሊዝኛ፣‹‹Corruption›› የሚባለው ስያሜ በጣም ሰፊ እና በተለያዩ የታሪክ ዘመናት የራሱ የኾነ ይዘት፣ ቅርፅ እና ትርጉም እየያዘ የመጣ ፅንሰ ሐሳብነው፡፡
‹‹ሙስና›› ለሚለው ቃል አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ የሚከተለውን ፍች ሰጥተዋል፡፡ሙስና ማለት ‹ጥፉነት›፣ ‹ጥፋት›፣ ‹መፍረስ›፣ ‹መበስበስ›፣ ‹መከራ›፣ ‹መቅሠፍት›… ወዘተማለት ነው፡፡ እንዲኹም ‹‹ሙሱን (Agent)›› ‹የማሰነ›፣ ‹ጥፉ›፣ ‹መጥፎ›፣ ‹ብልሹ›፣ ‹ግም›፣ ‹ድፍር› …ወዘተ. ማለት ነው፡፡
እንደእንግሊዝኛው ኦክስፎርድ መዝገበቃላት ፍች ደግሞ፣ ‹‹Corruption›› ማለት በዋናነት ‹መበስበስ›፣ ‹መቆርቆዝ›፣ ‹መበታትን›፣ ‹መዝቀጥ›… ወዘተ ሲኾን፣ ከእነዚህ ገለጻዎች የምናገኘው ምስል፥‹‹መበከል›› እና‹‹ከተፈጥሯዊ ማንነት መውጣትን›› ነው፡፡

ልብብለን መገንዘብ የሚኖርብን ነገር ቢኖር፣ የአማርኛውም ኾነ የእንግሊዝኛው ትርጓሜበሐሳብ ደረጃ ተቀራራቢነትና ተያያዥነት እንዳላቸው መረዳት እንችላለን፡፡በተጨማሪም የአማርኛውም ኾነ የእንግሊዝኛው ፍቺ፣ አኹን በዘመናችን ካለው እሳቤ ጥልቀት እናስፋት ያለው ኾኖእናገኘዋለን፡፡ይህንንም የምንልበት ዐቢይ ምክንያት፣ዘመናዊው አተያይ ሙስናን፣ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችውጭየማያይ፤ በግለሰብ እና በማኅበረሰብ ጥቅም መካከል የሚገኝ ሽኩቻ ብቻ አድርጎ ስለሚያቀርብ ነው፡፡

በአገራችን ያለውን የሙስና ደረጃ እና ኹኔታ በሚገባ ለማየት ግን የጥንቱንና ዘመናዊውን አተረጓጎምና አተያይ በድምር መውሰድ ይኖርብናል፡፡ እኔም ከፈላስፎች ጥቂት ብሂላትን በመውሰድ፣ ኹለቱንም አተያዮችና አተረጓጎሞች በጥቂቱም ቢኾን ማየቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ እላለኹ፡፡ የአራት ፈላስፎችን ሐሳብ አጠር አድርገን እንመልከት፡-

አርስቶትል፡- 
እንደ ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል አስተምህሮ፣የአንድን የፖለቲካ ማኅበር እንደ ሰንሰለት የሚያያይዘው ተቀዳሚ ዕሴትፍትሕ ነው፡፡ያለፍትሕ ማንኛውም ማኅበረሰብ በሰላም እና በጸጋ ሊኖር አይችልም፡፡ሙስና፣ ይህን ወሳኝየሞራል እና የሕግ ዕሴት እና አውታር ስለሚያበትከው እና ስለሚያመክነው ለማኅበረሰቡህልውና ትልቅ አደጋ ነው፡፡

ሲሰሮ፡- 
ለሲሰሮ፣ የሙስና ተቀዳሚ መሠረቱ፣ ማኅበረሰቡን ለማስተዳደር ሓላፊነት የተቀበሉ ሰዎች በፍቅረ ንዋይ እየተነዱ ከዋናው ተግባራቸው መውጣታቸው ነው፡፡ ለዚኽፈላስፋ፣ ሙስና፣ ሰፋ ያለ የሞራል፣ የሕግ እናየፖለቲካ ብልሹነትን የሚጠቁም ጉዳይ ነው፡፡

ቅዱስ ኦገስቲን፡-
እንደ ቅዱስ ኦገስቲን አባባል፣ የሰውነት ክፍሎቻችን የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸው ኹሉ፤ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ተቋማትም የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ እንደ እርሳቸውም እሳቤ፣ የሰው ልጅ አንድ አካሉ ሲታመም መላው ሰውነቱ እንደሚታወክ ኹሉ፤ ሙስናም፣ በአንደኛው የማኅበረሰብ አካል ከታየ ሌሎቹንም ክፍሎች እንደሚበክል ይናገራሉ፡፡

ኒኮሎ ማኪያቬሊ፡-

እንደማኪያቬሊ አገላለጽ፣ የጥንት ሮማውያን ወታደራዊ ድል ከተጎናጸፉ በኋላግዙፍግዛተ ዐፄ/ኢምፓየር/ ገነቡ፡፡ በዚኽም ብዙ ሀብት እና ትልቅ የፖለቲካ ኃይልማግኘት ቻሉ፡፡ ኾኖም ግን ያገኙት ሀብት እና ምቾትየተንደላቀቀ አኗኗር እንዲያገኙ ቢያስችላቸውም፣ ከንዋይ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው የሞራል ዝቅጠት ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ማኪያቬሊ፣ይህን የታሪክ እውነታ ዋቢ በማድረግ ስለ ሙስና የጻፈውን በኹለት ነጥቦች አሳጥሬ ላቅርብ፡፡
ሀ/ ሙስና፣ከምቾት እና ከቅምጥል ኑሮ የሚነሣየሥነምግባር እና የዲስፕሊን ጉድለት ነው፡፡
ለ/ የግል ጥቅም ከማኅበረሰብ ጥቅም የበላይነት ይዞ ሲገኝ፣ ‹‹የእኔ…›› የሚለው የራስ ወዳድነት መንፈስ ከሪፐብሊኩ ፍላጎት እና መንፈስ ጋር ሲጋጭ ነው፡፡

በአገራችን ያለው የኢሕአዴግ ሥርዓት በሙስና የተዘፈቀ በመኾኑሳቢያ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከተሟሉ መገለጫዎቻቸው ጋር ተሸክሞ እንደሚገኝ አምናለኹ፡፡ የኢሕአዴግ ሥርዓት በአስከፊ ሙስና ውስጥ እንዲዘፈቅ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

አንደኛው ምክንያት፣ መንግሥቱም ኾነዜጎች፣በአገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መዋቅሮች የየራሳቸው ሓላፊነትና ድርሻሊኖራቸው ሲገባ፣ ይህ ካለመኾኑ የመነጨ ነው፡፡ ሥርዓቱ፣እኒኽ ዜጎች በመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮች ተገቢውሓላፊነትና ድርሻ እንዳይኖራቸው በማድረግ ራሱ የፖሊሲ አውጪ፣ ራሱ አስፈጻሚ እናራሱ ዋነኛ የኢኮኖሚው ተዋናይ ኾኗል፡፡

ከዚኽ ጎን ለጎን ሳይጠየቅ የማይታለፈው ደግሞ፣ሥርዓቱ በሕዝብና በግለሰብ መብት መካከል ያለውን ልዩነት ማየት የተሳነው መኾኑ ነው፡፡አንድ ግለሰብ፣ፍትሕ ላይ የተመሠረተ፣ የማይሻርና የማይገሰስ መብት አለው፡፡ በመኾኑም ብዙኃኑን ይጠቅማል በሚል እሳቤ የግለሰቡን የማይገሰስ መብት መጣስ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በዚኽሥርዓት ግን የማኅበረሰቡን ወይም የብዙኃኑን ጥቅም ለማስከበር በሚል ሰበብ የግለሰቡ መብት እና ህልውና ሲጨፈልቅ ይታያል፡፡ ይህም በዋነኛነት የግለሰቡ ጉዳት ፖለቲካዊ ኪሳራ አያመጣብኝም ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፡፡
ይህም መንግሥት ለግለሰቡ እና ለሲቪል ማኅበረሰቡ መላወሻ የማይሰጥ፣ አንድ ወጥ መንግሥታዊሥርዓት እንዲኾን አድርጎታል፡፡

እነዚኽየሥርዓቱ ባሕርያትም፣ መንግሥት በኹሉም የአገሪቱ ሀብት እና ንብረት ላይ እጁን እንዲዘረጋ፣ የመንግሥት የአስተዳደር ሕጎች በትክክል እንዳይተገበሩ፣ የአሠራር ብልሹነት እንዲስፋፋ፤ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት በማባከን ሥርዓቱ የሙስና መናኸሪያ እንዲኾንአድርጎታል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸውን ፈላስፎችሐሳብ አጠቃለን ስናየው፣ ሙስና የሚከተሉትን አሉታዊ ተጽዕኖዎች እና ውጤቶች ያስከትላል፡፡እነርሱም፡- ኢፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ሥርዓተ ብልሹነት፣ አድልዎ እና የሞራል ዝቅጠት ናቸው፡፡
በአገራችንም ያለው የኢሕአዴግ ሥርዓት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከተሟሉ መገለጫዎቻቸው ጋር የተሸከመ እንደኾነ ስለምናምን፣ ሥርዓቱ ደግሞ እንዴት ወደ እነዚኽ አስከፊ የሙስና ኹኔታዎች እንደገባ በሚከተሉት ነጥቦች ማሳየት ይቻላል፡፡

አንደኛ፡- የኢሕአዴግን የፖለቲካ ሥርዓት ስንመለከት፣ በይዘቱ በጣም ሰፊና ትልቅ መንግሥት ነው፡፡ይህም አንዱ፣በመንግሥት እና በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ልዩነት እና ወሰን መኖሩን የማይቀበል ሲኾን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሕዝብ እና በግለሰብ መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት በመናድ አንድ ወጥ የኾነ የጠቅላይአገዛዝመንግሥትየዘረጋ ኃይል ነው፡፡ ይህደግሞ፣ በኹሉም የአገሪቷ ንብረት ላይ በበላይነት እጁን የከተተ መንግሥት የአስተዳደር እና የብክነት እክሎችና የትግበራ እንከኖች ብሎም የሙስና መናኸሪያ መኾኑ አይቀሬ ነው፡፡

ለሥርዓቱ በሙስና መዘፈቅ ኹለተኛው ምክንያት፣ ከፍትሐዊየሀብት ክፍፍል፣በብቃት ላይ የተመሠረተ ውድድር፣ ከጤናማ የኢኮኖሚ ፉክክር፣ ከሕጋዊ የሀብት ምንጭ… ወዘተ አኳያ ትልቅ ክፍተት ያለበት ሥርዓት መኾኑነው፡፡በእኔ ግምት ይህ ክፍተት ካለማወቅየመነጨ ሳይኾን፣ኾነተብሎ የፖለቲካ ሥልጣን ከጨበጡት ሹመኞች ጋር የብሔር ትስስር ያላቸውንና የእኛ የሚሏቸውን ወገኖች ለመጥቀም በማሰብ የተደረገ ነው፡፡

በዚኽ መልኩ ፍትሐዊነት በጎደለውበአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ፣ እነዚህ ዕሴቶች በሚጓደሉበት ወቅት ደግሞ፣አኹን በአገራችን እንደምናስተውለው፣ የአገሪቷ ሀብት የጥቂት ቡድኖች መጠቀሚያ እናችሎታን መሠረት ያላደረገ ኢፍትሐዊ ውድድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ አስችሏቸዋል፡፡

በአጠቃላይ በኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የሙስና ደረጃ ስናየው፣ ሌቪ የተባለው የጥንታዊሮማ የታሪክ ምሁር ስለሙስና ያለውን ያስታውሰናል፡፡ ሌቪ እንደሚለው፣ ‹‹ሙስና የተንሰራፋበት ሥርዓት ዝም ብለው ቢተዉት ሥርዓቱን ማፍረሱ አይቀርም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ፣ የተስፋፋውን ሙስና ለመግታት ሙከራ ቢደረግም እንኳ ሥርዓቱ መፍረሱ አይቀርም፡፡››

ከላይ ያነሣናቸው የአገር በጄ፣ የኢዴሞክራሲ እና የሙስና መንሰራፋት ችግሮች፣አኹን ሥርዓቱ ለአጋጠመው ሕዝባዊ ተቃውሞ እና ዐመፅመንሥኤዎች ናቸው፡፡

ወደ ኦሮማይ ጎዳና

ሌኒን፣ በ1920 (እ.ኤ.አ)፣አንድ አገር ዐብዮታዊ ኹኔታ ውስጥ ስትገባ የሚከተሉትን አራት ክሥተቶች እንደ ምልክት እናያለን ብሎ ነበር፡፡እኔም ሥርዓቱ ወደ ዳግማዊ ኦሮማይ ድባብ እየገባ ነው፣ብዬስለማምን የሌኒንን አራት መገለጫዎችአንሥቼየራሴን አተያይ ለማቅረብ እሞክራለኹ፡፡

1ኛ/ ለዐብዮቱ ጠላት የኾኑመደቦች በመካከላቸው ባለው ውስጣዊ ትግል ምክንያት ወደ ውዥምብር እና ክፍፍል ያመራሉ፡፡ይህ ውስጣዊ ውዥምብር ደግሞ ለድክመት ይዳርጋቸዋል፡፡ በመኾኑም ድሮ በሚተገብሩት መንገድ ሥርዓታቸውን ማስቀጠል አይችሉም፡፡

2ኛ/ ከሥርዓቱ ተጠቃሚነት አልፎ ተቀባይነትና አመኔታ ያለው የንኡስ ከበርቴ መደብ፣ በሕዝቡ ዘንድ ማንነቱ በሚገባ ታውቆና በሕዝቡ ፊት ተጋልጦ፣ በጥቂቱም ቢኾን የነበረውን ሕዝባዊ ቅቡልነትሙሉ ለሙሉ ያጣል፡፡

3ኛ/ ዐብዮተኞቹ ከቡርዣው መደብ ጋር የሚያደርጉትን ቁርጠኛ ትንቅንቅ ሰፊው የሠራተኛው መደብ መደገፍ ይጀምራል፡፡

4ኛ/ የገዢው መደብ ሠራዊት እርስ በርስ መከፋፈል፣ መፈረካከስ እና ማመፅ ይጀምራል፡፡

እንደሚታወቀው እነዚህ ነጥቦች፣ የሩስያ ዐብዮት መሪ የዛሬ መቶ ዓመት ለዐብዮት መፈጠር አመልካች ክሥተቶች ናቸው በሚልየጠቀሳቸው ናቸው፡፡ በመኾኑምሌኒን ያለውን በንባቡ(ቃል በቃል)በመውሰድ፣ ዛሬ አገሪቷ ያለችበትን ኹኔታለመግለጽ ሳይኾን፣ከእነዚህ ነጥቦች መካከል የተወሰኑትአኹን ባለው የአገራችንየፖለቲካ ኹኔታ ላይ እንዴት እንደሚስተዋሉቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ሀ/ ‹‹በድሮው መንገድሥርዓቱ መቀጠል ሲሳነው››
በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ እና በመብት ዙሪያ የተነሡ ጥያቄዎች፣ ሥርዓቱ እስከ ዛሬ በሚያስተዳደረው መንገድ ሊፈቱ እንደማይችሉ ሕዝቡርግጠኛ ኾኗል፡፡ በመኾኑም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚቻለው የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ እንደ ኾነ ሕዝቡ ተገንዝቧል፡፡ ሌኒንም፣ እንደድሮው ሥርዓቱ መቀጠል አይችልም፤ በሚልበት ጊዜ፣ በሕዝቡ ለተነሡት ኹለተናዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው፣ በድሮው መንገድ ሳይኾን አዲስ የሥርዓት መንገድመከተል እንደሚያስፈልግ ሕዝቡ ሲያምን እንደኾነ መናገሩ ነው፡፡

ለ/ ‹‹የሕዝብ ቅቡልነት ማጣት››
ለአንድ ሥርዓት የቅቡልነት ጥያቄ ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ቅቡልነቱም በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል፤መንገዶቹም፡- ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ… ወዘተ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ የአንድሥርዓት ዕድሜ፣ቀጣይነት ወይም ዘላቂነት የሚወሰነው፣ከሕዝብ ከሚያገኘው ቅቡልነትየተነሣነው፡፡
አገዛዙ የሕዝብ ቅቡልነትን ሲያጣ በመሣሪያ ኃይል ሥርዓቱን ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ አኹንም በአገራችን እያየን ያለነው የሕዝብን ጥያቄ በመሣሪያ ለመግታት የሚደረግን ጥረት ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የኃይል አካሔድ እንደማያዛልቅ የታወቀ ነው፡፡ በዚኽ ረገድ ፈረንሳዮች አንድ ትምህርታዊ አባባል አላቸው፡፡ ይህም ‹‹መሣሪያን ብዙ ነገር ያደርጉበታል፤ኾኖምለብዙ ጊዜ አይቀመጡበትም››የሚል ነው፡፡

ሐ/ ‹‹የሕዝብ ቁርጠኝነት››
የሕዝብ ብሶት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰ ጊዜሽንገላ እናጊዜያዊ መፍትሔዎች ቀልቡን አይስቡትም፡፡ቀደም ሲል፣ ሕዝቡ፣መንግሥት ወይም የአስፈጻሚ አካላት ሕገ መንግሥቱን ቢያስከብሩ ችግራችን በሒደት ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ አኹን ግን ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የሕዝቡን ጥያቄ ለማስተናገድም ኾነ መፍትሔ ለመስጠት ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ከመረዳት አልፎ፣ሥርዓቱ ሕገመንግሥቱን ለመተግበር የሚያስችል ባሕርይና ፈቃድ እንደሌለው ተገንዝቧል፡፡ በዚኽ ምክንያት በተነሣሣው ሕዝባዊ ዐመፅ፣ መንግሥት በብቸኛነት በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ የተለያየ ምክንያት ቢያቀርብምሕዝቡ ልቡንም ጆሮውንም ሳይሰጠው የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡

ማጠቃለያ 
እንደኢትዮጵያየተለያዩ ማኅበረሰቦች ባሉበት አገር፣ የሚዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት ቢያንስ የሚከተሉትን ኹለት ወሳኝጉዳዮች ማሟላት እንደሚገባቸው በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ጥናት እና ምርምር ያደረገው አረንድ ሊፕሐርት ይገልጻል፡፡ እነርሱም፡-

አንደኛ፡– በአገሪቷ ውስጥ ባሉት ማኅበረሰቦች መካከል ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ፡- በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ማኅበረሰቦች፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት መጎናጸፍ ይኖርባቸዋል፡፡
ሊፕሐርት፣ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያስፈልጋል፣ ሲል ኹሉም ማኅበረሰቦች ውሳኔ በመስጠት ሒደት ላይ ቀጥተኛ እና ተገቢውን የተሳትፎ ሚና ሊኖራቸው ይገባል ማለቱ ነው፡፡

ኹሉም ማኅበረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ ማለትም፣ የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሃይማኖት… ወዘተእንዲያሳድጉና በአገሪቷ ላይ የሚኖራቸውን የጋራ የባለቤትነት ስሜት እንዲያጎለብቱ እንዲያስችላቸው ነው፡፡
ከእነዚኽኹለት ነጥቦች አኳያ የኢሕአዴግንመንግሥት አመራር ስናየው፣ ፌዴራላዊ ሥርዓትን በመተግበር በባህልና በትምህርት መስኮች ማኅበረሰቦችያላቸውን ማንነት እንዲስጠብቁ ቢሞክርም፣ ጅማሮው እየዋለ ሲያድር መልሶ የማኅበረሰቦችን ማንነት ወደ መጨፍለቅ፣ እኔ የሰየምኩኽን ማንነት መላበስ አለብኽ፣ ወደሚል ዓምባገነናዊ አካሔድ ተለወጠ፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፣ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የሕዝቦችን ዴሞክራሲ መብት በጉልበት በመገደብ ፍትሐዊ የሥልጣን ውክልና እንዳይኖራቸው እስከማድረግም ደርሷል፡፡ እንደሚታወቀው ዴሞክራሲ፣ለኹሉም እኩል የኾነ መንገድ ትከፍታለች፡፡ ኾኖምበአንድ ጉዳይ ላይ ‹‹የመድልዎ›› ስሜትይታይበታል፡፡ ይህም ዴሞክራሲ በተፈጥሮዋ ግቧን ለማሳካት በዋናነት የቁጥርን መርሕ መከተሏ ነው፡፡
በኢሕአዴግ ሥርዓት ግን፣ ዴሞክራሲ፣ ይህን መርሕ ተከትላ ለሕዝቦች የሥልጣን ውክልናና ትክክለኛውን ምላሽ እንዳትሰጥ በጉልበት ተገድባለች፡፡ ለዚኽም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የመቀመጫ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ወደ ኋላ ተገፍተው፣ ከእነርሱ በእጅጉ ያነሰ የመቀመጫ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ይዘዋል፡፡ይህን ሕዝቦች ባላቸው የመቀመጫ ቁጥር ውክልና መሠረት ተገቢውን ሥልጣን አለማግኘታቸው እንደ ማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡

በእነዚህ ኹለት መሠረታዊ ችግሮች ሳቢያ፣በአኹኑ ወቅት የኢሕአዴግ ሥርዓትፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍልን ለመተግበርም ኾነ ሙሉ ለሙሉ አስጠብቄዋለኹ በሚለው የሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ለሚነሡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ተስኖታል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው፣ትላንት የነበሩት ሥርዓቶች የሕዝቦችን ማንነት አላከበሩም፤ እያለ ሲወነጅል የነበረው መንግሥት፣አኹን ካለፈው በከፋ መልኩ ለማኅበረሰቡ ባይተዋር የኾነ ማንነት እየለጠፈ ባለኽበት እርጋማለቱ ነው፡፡

አኹን የተነሣው ጥያቄ፣ በዴሞክራሲ ዕጦት አካባቢና አብረውየሚሔዱት የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ የሀብት አከፋፈል እንዲኹም፣በሰብአዊ መብት ረገጣ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን፣ከአኹን በኋላ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን ማክበር ቢጀምር ነገሮች ይስተካከላሉ፤ የሚል አቋም ይዘው እየተሟገቱ ነው፡፡ እንደ እኔ አስተሳሰብ፣ በአንድ በኩል፣ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ባለው ፍላጎትና ዴሞክራሲራሷ እንዲተገበርላት በምትፈልገው መካከል ትልቅ ቅራኔ ስላለ፣ሥርዓቱ፣ሕገ መንግሥቱን በሥራ ላይ ያውላል ብሎ መመኘቱ ትልቅ ስሕተት ነው የሚኾነው፡፡
በሌላ በኩል፣ዴሞክራሲ በሌለበት ቦታ የመናገር እና ሐሳብን በነጻነትየመግለጽ መብት ብሎም ኹሉም ወገኖች የሚደመጡበትና ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ሊኖር አይችልም፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በብዙኃን መገናኛ እየቀረቡ፣ ‹‹አኹን የተፈጠረው ችግር በውይይት ይፈታ፤ ሕዝቡም ሐሳቡን በግልጽ ተወያይቶ መፍታት ይኖርበታል›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡

የእኒኽን ምሁራን ሐሳብ ስሰማ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተነሣውን ችግር ቀርቶ፣ የሐሳብ መፈተሻና የነጻ ውይይት መዲና ሊኾን በሚገባውናዛሬየዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ በኾነው ዩኒቨርሲቲ ውስጥሐሳብን በነጻነት መግለጽ እንደማይቻል እየታወቀ፣ ምሁራኑ ራሳቸውም ሐሳባቸውን በነጻነት የማንሸራሸር መብታቸውን ተገፈው ባሉበት ወቅት፣‹‹ሕዝቡ በነጻ ውይይት ችግሩን ይፍታ››ማለታቸው ነው፡፡

በመጨረሻም ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ ሙስና ለአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ኢፍትሐዊነት ማሳያ ነው፡፡ የመንግሥት የአስተዳደር እና የአገልግሎት ተቋማት በሕጉ መሠረት ለዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት የማይሰጡና ኹሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተናግዱ አይደሉም፡፡የአገሪቱን የልማት እና የንግድ ሥራዎች በበላይነት የሚመሩት የመንግሥት ተቋማትም በአገሪቱ ሕግ መሠረት በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎችም ኾነ የግል ድርጅቶች ከአድልዎ የጸዳ ፍትሐዊ አገልግሎት የሚሰጡ አይደሉም፡፡ በዚኽም ምክንያት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኮንስትራክሽንና መሰል የአገሪቱ ወሳኝየኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ጥቂቶች ብቸኛ ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡
ይህም በሥርዓቱ ውስጥ የሕግና የፖለቲካ አይነኬ ሕዋሶችን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሕዋሶችሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን በመጣስ የፈጠራቸው ከመኾኑ አኳያ፣የእነዚኽ ሕዋሶች ህልውና እስከ ቀጠለ ድረስ ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችልርምጃ ለመውሰድ አይቻልም፡፡

በኢሕአዴግ ሥርዓት በመሾምና ንብረት በማግበስበስ መካከል እምብዛም ልዩነት የለም፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ተሾመ ማለት ከበረ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ችግር በአገሪቷ ውስጥ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እና ነጻ የኢኮኖሚ ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ አገሪቷን ወደማትወጣውአዘቅትውስጥ ጨምሯታል፡፡
በመሆኑምከላይ ያነሣናቸውየፌዴራሊዝም፣ የዴሞክራሲ እና የሙስና ችግሮች ባለው የኢሕአዴግ ሥርዓት መፍትሔየሚያገኙት፣ ቀደም ብሎ እንደዚኽዓይነት ጥያቄዎችን የሚያስተናግድና የሚፈታ አሠራርና ተቋም ቢኖር ነበር፡፡ ኾኖም ይህ በሌለበትና ሕዝቡ ውስብስብና አስቸጋሪ ጥያቄ ባነሣበት በዚኽ ወቅት፣ አገዛዙ ሥርዓቱን ለማዳን የሚያስችል መፍትሔ ይዞ ይቀርባል ብሎ ማመን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ከእነዚኽመፍትሔ አልባ ችግሮችተነሥቼ ነው፣ ኢሕአዴግወደ ‹‹ኦሮማይ ቀጣና›› እየገባ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡

መጣጥፌን የምደመድመው፣ የደበበ ሰይፉ፣ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ››ግጥም፣ በአኹኑ ወቅት እየተከሠተ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ያሳያል ብዬ ያመንኩበትን ስንኞች በማቅረብ ነው፡፡

……….በእሱ ውድቀት እናንተ እርካብ ብትመቱ
በብሶቱ ብትፈይዱ 
በመክሊቱ ብትነግዱ፤…
ይህ ፍጹም ባድማ፣ ይህ ፍጹም ድቅድቅ ጨለማ
እሚበራ እንዳይመስላችሁ በእናንተ የይስሙላ ቁራጭ ሻማ፡፡
ግን መጋረጃው ያልተነሣ ተውኔት፣ 
ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ፣ አለውና ጨለማ
ነፋስ – እሳት ገሞራን፣ ሊታቀፍ ይችላልና ጠፍ ባድማ
ዐይን ያለው ይይ!
ልብ ያለው ያስተውል!
ጆሮ ያለው ይስማ!

Filed in: Amharic