>

የምሕረት አደራረግ ሕጉና ዓላማው ሲገለጥ፤ (ውብሸት ሙላት)

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአባል ድርጅቶቹ ሊቃነመናብርት ጋር በመሆን የግንባሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአስራ ሰባት ቀናት ያደረገውን ግምገማ መሠረት በማድረግ ማብራሪያና መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም፣ የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በጥፋታቸው ምክንያት ጉዳያቸው በዓቃቤ ሕግ ተይዞ በእስር የሚገኙም ሆኑ የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና እና ግለሰቦች ክሳቸው እንደሚቋረጥ ወይም ምሕረት እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከተናገሩት በተለዬ ሁኔታ፣ የሚፈቱ እስረኞችን ዝርዝር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እና ከማረሚያ ቤት አስተዳደር እንዲቀርበላቸው፣ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት መጠየቃቸው በእንዳንድ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በይፋ የገለጹት በምሕረት (amnesty) እንደሚፈቱ ሲሆን፤ ፕሪዚዳንቱ እንዲቀርብላቸው የጠየቁት ደግሞ በይቅርታ (pardon) ለሚፈቱ እስረኞች የሚደረግ ሥርዓትና ሒደት በመከተል ነው፡፡

አንዳንድ የሕግ ምሑራንም ፓርላማው የምሕረት አደራረግ አዋጅ ስለሌለው በዚህ መልኩ እስረኞችን መፍታት እንደማይቻል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸውን ገልጽዋል፡፡

የዚሕ ጽሑፍ ዓላማ የምሕረት ምንነትን፣ የምሕረት አድራጊውን ማንነት፣ዓላማው ምን እንደሆነ፣ እንዲሁም ምሕረት እንዴት እንደሚሰጥ ከኢትዮጵያ ሕግ አንጻር ማሳየት ነው፡፡ እገረ መንገዱንም በምሕረትና በይቅርታ መካከል ያለውን ልዩነትም ይብራራል፡፡

የምሕረት ምንነት፤

ስለምሕረት የሚናገር ሰፋ ያለና የተብራራ ሕግ የለንም፡፡ በተሻለ ሁኔታ የተቀመጠው የወንጀል ሕጉ ላይ ነው፡፡ በዚሁ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 የተቀመጠውም ቢሆን ለምሕረት ግልጽና ቀጥተኛ የሆነ ትርጓሜ የለውም፡፡ ነገር ግን ከድንጋጌው ምንነቱን መረዳት ይቻላል፡፡ ከይቅርታ የተለዬ ስለመሆኑም በተከታታይነት ከተቀመጡት ከአንቀጽ 229 እና 230 መረዳትም አይከብድም፡፡

ምሕረት፣ለአንድ ዓይነት ወንጀል ወይም በአንድ ዓይነት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወንጀለኞች ጥፋታቸው እንዳልተፈጸመ ይቆጠርና እንደንጹህ ሰው እንዲታዩ የሚደረግበት ሥርዓት ነው፡፡ ወንጀላቸው ይሰረዛል፤ ይተዋል፤ እንዳላጠፉ ይወሰዳል ማለት ነው፡፡

ከሕግ አንጻር ሲታይ ምሕረት የሚያመለክተው መንግሥት የወንጀል ታሪክን ሙሉ በሙሉ በመተው፣ ያለፈን ድርጊት በመርሳትም በማስቀረትም አንድ ዓይነት ወንጀልን ወይም የሆነ ወንጀል ፈጽሟል የተባለ ቡድንን (ግለሰቦችን) በተለይም ከወንጀል ክስ ነጻ ማድረግን ነው፡፡

ምሕረት የሚሰጠው ላልተከሰሱና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ላልተባሉ ግለሰቦች ነው፡፡ የተፈረደባቸው ከሆነ ግን ምሕረት ሳይሆን ይቅርታ ነው የሚሰጠው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምሕረቱ በወንጀል የተፈረደባቸውንም ጭምር ሊያካተት ይችላል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ላይም የተገለጸው በዚሁ መርሕ ቅኝት ነው፡፡ መርሑን ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ሲያስቀምጥ “ለአንድ ዓይነት ወንጀሎች ወይም በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ወንጀለኞች” በማለት ነው፡፡

ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ምሕረት የሚደረገው ክስ ያልቀረበባቸውን የሆነ የወንጀል ዓይነት ፈጽመዋል የተባሉን እንጂ የተፈረደባቸውን አይደለም፡፡ ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክረው ስለይቅርታ የሚደነግገው አንቀጽ 229 ነው፡፡ አንቀጹ “በፍርድ የተወሰነ ቅጣት ሥልጣን በተሰጠው አካል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በይቅርታ ሊቀር … ይችላል” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይቅርታ ለፍርደኞች የሚሰጥ መሆኑን በግልጽ ሲያሳይ ምሕረት ግን በዚህ መልኩ አልተገለጸም፡፡

ይሁን እንጂ፣ አንዳንዴ ደግሞ የተፈረደባቸውንም ሊጨምር እንደሚችል አንቀጽ 230 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ከተቀመጠው መረዳት የሚቻለው “ምሕረት በሚሰጥበት ጉዳይ ቅጣት ተወስኖ እንደሆነ” በማለት የተገለጸው አንዳንድ ጊዜ ፍርደኛንም ሊያካትት መቻሉን ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ከተፈረደባቸው በኋላ በምሕረት ለመልቀቅ ሳይሆን ምሕረት በተደረገበት የወንጀል ጉዳይ ላይ ምሕረት ከመደረጉ በፊት ቅጣት የተላለፈባቸው ሰዎች ካሉ እነሱን ላለመለየት ነው፡፡ ልዩነት ማድረጉ የአድልኦ ድርጊት ስለሚሆን ነው፡፡

በመሆኑም፣ ጥፋተኛ ለተባለው ሰው በመርሕ ደረጃ ይቅርታ እንጂ ምሕረት አይደረግም፡፡ በልዩ ሁኔታ ግን ምሕረት በተሰጠበት ጉዳይ ጥፋተኛ የተባሉ ካሉ እንደ ይቅርታ ሁሉ የተፈረደባቸው ሰዎችንም ይጨምራል፡፡

ምሕረት በባሕርይውም በተለምዶም ፖለቲካዊ ነው፡፡ አንድን የፖለቲካ ይዘት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ የፖለቲካ ወንጀሎች ተብለው የሚታወቁ እንደ ለሌላ አገር መሰለል፣ ፀረ-መንግሥት የሆኑ የፕሮፓጋንዳ ድርጊቶችን መፈጸም፣የፖለቲካ ግብን ለማሳካት ሲባል (ከማሳካት በተያያዘ) ማንኛውንም ወንጀል (ስርቆት፣ድብደባ ወዘተ) መፈጸም ሊሆን ይችላል፡፡

ምሕረት፣ አንዲት አገር በሉዓላዊነት ሥልጣኗ ልታደርገው የምትችለውም ድርጊት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ምሕረት ማድረግ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ፣ በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸሙ ዘግናኝ ወንጀሎችን ምሕረት ማድረግ እየቀረ መጥቷል፡፡ ጉዳዩም በአንዲት ሉዓላዊት አገር ሥልጣን ሥር መወሰኑ ቀርቶ ዓለም አቀፋዊ ሆኗል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ምሕረት የማይሰጥባቸውን የወንጀል ዓይነቶች ለይተው አስቀምጠዋል፡፡

ስለዚህ፣ ምሕረትን የሚያስከለክሉ ወንጀሎች መኖራቸው በሕግ ከተገለጸ መንግሥት ይህንን ዘዴ መጠቀም አይችልም ማለት ነው፡፡ መንግሥት ላይ የተጣለ ገደብ መሆኑ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶቹ በተጨማሪ በእኛም ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ላይ ምሕረት የማይደረግባቸው ወንጀሎች ተለይተዋል፡፡ ንስሐ የሌላቸው ኃጢአቶችን መምሰላቸው ነው፡፡ እነዚህም፣ የዘር ማጥፋት (genocide)፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ (summary executions)፣ አስገድዶ ሰውን መሰወር (forced disappearance)፣ ኢሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶች መፈጸም (torture) ናቸው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ላይም በሕግ በሌላ አኳኋን ገደብ ካልተደረገ በስተቀር ለማንኛውም ዓይነት የወንጀል ድርጊቶች ምሕረት ሊሰጥ እንደሚችል መግለጹ ይሄንኑ ሲያጸና ነው፡፡

የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 240 እና አሁን በሥራ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 230 ከስያሜ እና በቀድሞው ሕግ ለማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ምሕረት ማድረግ የሚፈቅድ ከመሆኑ፣ የአሁኑ ደግሞ ከላይ ለተገለጹት የወንጀል ድርጊቶች መንግሥት በእዚህ መንገድ ከወንጀል ነጻ ማድረግ እንደማይችል ገደብ ከማበጀቱ የዘለለ ልዩነት የላቸውም፡፡

በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ‘የአዋጅ ምህረት’ ሲለው ‘ይቅርታ’ን ደግሞ ‘ምሕረት’ ይለዋል፡፡ ስለሆነም፣ በደርግም ይሁን በአሁኑ ጊዜ ምሕረት ለማድረግ መሠረት የሆኑት ሕግጋት ተመሳሳይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ምሕረት ማድረግ ባይቀርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አከራካሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ግቡ ነው፡፡ የምሕረት ግቡ እርቅ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ አንድነት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ምሕረት የሚደረገው ሰላም ለማስፈን ነው፡፡ በተጻራሪው፣ ምሕረት የሚደረገው በተፈጸመ በደልና ወንጀል ላይ ነው፡፡ በደልና ወንጀል ከተፈጸመ ደግሞ ፍትሕ መሥጠት አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ፍጥጫው በፍትሕና በሰላም መካከል ነው ማለት ነው፡፡ ለሰላም ሲባል ፍትሕን አለመስጠት ተገቢ አይደለም የሚለው ነው አከራካሪ እየሆነ የመጣው፡፡

ዓላማና ግቡ፤

ምሕረት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ብለናል፡፡ አገራዊ መግባባት፣ ዕርቅ፣ ሰላም ማውረድ፣ የእርስ በርስ ጦርነትን ማስቆም ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም፣ በአገር ውስጥ የተፈጠረ ፖለቲካዊ ትኩሳትን ያበርዳል፡፡ የመንግሥት ተቋማት በፖለቲካ ቅሬታ ምክንያት መንግሥት ላይ ወንጀል ቢፈጽሙም እንዳይከሰሱ ያደርጋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ጫና ይገላግላል፡፡ አገር ጥለው የተሰደዱን ወደአገር ቤት እንዲመለሱ ያግዛል፡፡

ከምሕረት በኋላ ዕርቅ የሚኖርበት ሁኔታ የሚደረግ ከሆነ አፈጻጸሙ በባህላዊና በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የመሆን ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ እነዚህ ዕሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና የማኅበረሰቡ መታመኛዎች እንዲሆኑም ያበረታታል፡፡

ምሕረት ማድረግ የቆዬ እና ጥንታዊ ተቋም ነው፡፡ አተገባበሩም በተወሰኑ አገራት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሕዝባዊ ወይም መንግሥታዊ ግጭት ተከሥቶ አሸናፊና ተሸናፊ ተፈጥሮ ግጭቱ ሲቋጭ በአሸናፊው በኩል ምሕረት ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ የሥርዓት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ቀድሞ ተፈጥሮ የነበረውን የጠበኝነት ሁኔታ አስቀርቶ ሰላም ለማስፈን ሲባል ምሕረት ይደረጋል፡፡

በአንዲት አገር ላይ በተዘረጋው ሥርዓትና መንግሥት ላይ ያመጸ ቡድን፣ ሽፍታ፣ የሥልጣን ተቀናቃኝ ወዘተ ሲፈጠርም ምሕረት በማድረግ ሰላም ማውረድ እኛም አገር የቆዬ ልማድ ነው፡፡ ባህልም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም አዲስ ንጉሥ ሲነግሥ፣ መንግሥት ሲቀየር ምሕረት ማድረግ ወትሮም የነበረ ነው፡፡

ነገሥታቱ ሲያደርጓቸው የነበሩትን የምሕረት አዋጆች ትተን ደርግ የሰጣቸውን ሁለት ምሕረቶች እንመልከት፡፡ እነዚህ የምሕረት አዋጆች ማንሳታችን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230ን የበለጠ እንድንገነዘበው አስረጅ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ምሕረት የተደረገው ለሁለት የተለያዩ ድርጊቶች ነው፡፡

የመጀመሪያው በዐጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና ራሱ ደርግ በአዋጅ የተለያዩ ውሳኔዎችን ከማሳለፉ በፊት ወንጀል ፈጽመው ለሸፈቱት ምሕረት ያደረገበት ነው፡፡ የታወጀው በ1967 ዓ.ም. መጋቢት 18 ቀን ነው፡፡ አጠራሩም፣ “በነፍስ መግደልና በሌላም ወንጀል ለሸፈቱ ኢትዮጵያውያን የምሕረት አዋጅ ቁጥር 29/1967” የሚል ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በዕድገት በኅብረት ዘመቻ ወቅት “ግዳጃቸውን ስላልፈጸሙ ዘማቾች የወጣ አዋጅ ቁጥር 72/1968” በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሁለቱም በአዋጅ የተሰጡ ናቸው፡፡

በአዋጅ ባይሰጥም፣ በግልጽና በዐደባባይ ምሕረት እንደሆነ አልተነገረም እንጂ በአቶ ሞላ አስገዶም እየተመራ ከኤርትራ ወጥቶ ወደአገር ውስጥ የገባው አማጺ ቡድን አባላት ሳይከሰሱ በሰላም እንዲኖሩ የተደረገው ያው በምሕረት ነው፡፡ ባለፈው ዓመትም የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር የነበሩ ሰዎችም ወደአገር ቤት ሲገቡ ክስ ያልቀረበባቸው ምሕረት ስለተደረገላቸው እንጂ በሌላ መንገድ ሊሆን አይችልም፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ የክልል መንግሥታት ይፋ እንደተደረገው በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ሲገለገሉ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች እስከተወሰነ ቀን ድረስ በራሳቸው አምነው ለሚመለከተው አካል ካሳወቁ በወንጀል ከመጠየቅ እንደሚማሩ መገለጹም ያው ምሕረት እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡

በመሆኑም፣ በዚህ ዘመንም ቢሆን ምሕረት ማድረግ አልቀረም ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ነፍጥ አንስተው፣ ጦርነት ያወጁ ቡድኖች ሠራዊት በወንጀል ሳይከሰሱ፣ በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ የሚቻለው በምሕረት ብቻ ነው፡፡

በደርግም ጊዜ የተደረጉት ይሁኑ በቅርቡ በምሕረቱ ተጠቃሚ የሆኑት ግለሰቦች በአገሪቱ ጥቅም ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመው ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ግብን ለማሳካት ሲባል ወንጀላቸው ቀሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ወንጀል በምሕረት ቀሪ የሚደረገው ከፍ ላለ አገራዊ ፋይዳ ላለው ነገር ነው፡፡

አገሪቱ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ሲታይ ምሕረት ማድረጉ ለአገሪቱ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሊሆን እንደሚችል የወንጀል ሕጉ ይገልጻል፡፡ በደርግ ዘመን የተደረጉ ሁለት የምሕረት አዋጆች ላይ የተቀመጡትን ግቦችም ከእዚሁ ከሕጉ አገላለጽ ጋር የሚስማማ ነው፡፡

በነፍስ መግደልና በሌላም ወንጀል ለሸፈቱ ሰዎች የተደረገው የምሕረት አዋጅ ከመግቢያው ላይ መረዳት እንደሚቻለው ዋና ዓላማው ደርግ እያደረኩት ነው የሚለው የለውጥ ሒደት ተካፋይ እንዲሆኑ፣ በለውጥ እንቅስቃሴውም አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ሠላም፣ አንድነትና ፍቅር እንዲሰፍን ለማድረግ ነው፡፡

እነዚህን ግቦች ለማሳካት ሲባል ነፍስ የገደሉ፣ ዝርፊያና ቅሚያ የፈጸሙና በሌሎች ወንጀሎችም ምክንያት ከመኖሪያቸው ሸሽተው የሸፈቱ በሙሉ ወደየቤታቸው ቢመለሱ ምንም ዓይነት ክስ እንደማይቀርብባቸው በሰላም እንዲኖሩ መንግሥታዊ ተግባራትንም ሳያደናቅፉ ይልቁንም እንዲደግፉ የተደረገ ጥሪ ነው፡፡

ግዳጃቸውን ላልተወጡ ዘማቾች የተሰጠው ምሕረት ዓላማው በወቅቱ እየተደረገ የነበረው ዘመቻ ለሰፊው ሕዝብ የፖለቲካ ንቃትና የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ስለነበር በአንዳንድ ጊዜያዊ ችግሮች እና ዘማቾቹ ላይ በቀረበባቸውና በሚቀርብባቸው አስተዳደራዊና የወንጀል ቅጣት ምክንያት ዘመቻው እንዳይደናቀፍ ለማድረግ ታስቦ ስለመሆኑ የአዋጁ መግቢያ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምሕረት እንዲፈቱ ተወስኗል” በማለት የገለጹት ምሕረት ማድረግ ለሚያስፈልግባቸው ድርጊቶች ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ ከእዚህ መረዳት እንደሚቻለው ምሕረት ማድረግ ያስፈለገበት የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት ነው፡፡ ምሕረት የማድረጉ ግብ ፖለቲካዊ ነው የሚለው ሐሳብም ጋር የተስማማ ነው፡፡

በተቃራኒው፣ ይቅርታ የሚሠጠው ጥፋተኛነታቸው ለተረጋገጠና ለተቀጡ በመሆኑ፣ እንዲሁም በይቅርታ ተጠቃሚ የሚሆን ወንጀለኛ አስቀድሞ ራሱ መንግሥትን ይቅርታ መጠየቅ ስለሚጠበቅበት ብዙም አገራዊ መግባባትን ለማምጣት አይጠቅምም፡፡ መንግሥትን አሸናፊ፣ የሚፈቱትን ተሸናፊ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ያጋጠማት የአገራዊ መግባባት አለመኖርና የዴሞክራሲ ምህዳሩ መጥበብ እንደሆነ ስለተገለጸ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያግዝና በእነዚህ ችግሮች ምክንያት መንግሥት ላይ ያመጹ፣ መንግሥትን የተቃወሙ፣ የተቹ፣ አመኔታ እንዲታጣበት ያደረጉ ሰዎች የምሕረቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው የሕጉ መንፈስ፡፡

ምሕረት የማድረግ ሥልጣኑስ የማን ነው?

ስለምንነቱና ዓላማው ይሄን ያህል ካልን ቀጣዩ ጉዳይ ምሕረት የሚያደርገው አካል ማን ነው የሚለውን እንመልከት፡፡ ይቀርታ የሚያደርገው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት እንደሆነ ሕገ መንግሥቱም የይቅርታ አዋጁም ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ምሕረትን በተመለከተ ግን በግልጽ ይህ ተቋም ነው አይልም፡፡ ምንም እንኳን ሕጉ የምሕረት አድራጊውን ማንነት ሲገልጽ “አግባብ ባለው አካል” ብቻ በማለት ወዝፎ ቢተውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊሆን እንደሚችል መረዳት አይከብድም፡፡

በቅድሚያ ይህን “አግባብ ያለው አካል” የመለየትና የመሰየም ሥልጣን የራሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ በመቀጠልም ምሕረት ሲደረግ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ አንቀጹ ምሕረት በሚደረግበት ጊዜ ለማን እንደሚደረግ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ፣ የተፈጻሚነቱ ወሰን ምን እንደሆነ በሕግ መገለጽ እንዳለበት ይናገራል፡፡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በውክልና እስካልተሰጠ ድረስ ሕግ የማውጣት ሥልጣኑ የዚሁ ተቋም ነው፡፡

እዚህ ላይ ከግምት ሊገባ የሚገባው ነጥብ ቢኖር ሕጉ የሚወጣው አስቀድሞ ሳይሆን ምሕረት ማድረጉ በሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ ለይቅርታ አሰጣጥ አስቀድሞ ሥነሥርዓቱና ሒደቱ ምን መምሰል እንዳለበት ሕግ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

በተቃራኒው፣ ምሕረት በተደረገ ጊዜ ሁሉ ሕግ ይወጣል እንጂ በአንድ አዋጅ ብቻ በየጊዜው ምሕረት አይሰጥም፡፡ ንዑስ ቁጥር 1 ላይ “የምሕረት አሰጣጥ ሁኔታው በሕግ እንደተደነገገው ይሆናል” በማለት ያጠናክረዋል፡፡ ዝርዝር ሁኔታውን በሌላ ሕግ ይወሰናል አላለም፡፡ ምሕረት የሚደረግበትን ጉዳይ የሚገልጸውን ሕግ ሲያመለክት ነው፡፡ ከላይ በደረግ ጊዜ የወጡት አዋጆች ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ ምሕረት የሚሠጠው በአንዲት አገር ከፍተኛ ሥልጣን ባለው አካል መሆኑ ነው፡፡ በእንግሊዝኛውም “sovereign act” ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ላይ ውሳኔ የሚያሳልፈው ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል እንደሆነ የእኛም አገርም የሌሎች አገራት ልማድም ምስክር ነው፡፡

በ1923 እና በ1949 ዓ.ም. በወጡት ሕገ መንግሥቶች ላይ ከሕግ መምሪያውም ሆነ መወሰኛው ምክር ቤቶች የላቀ ሥልጣን የተሰጠው ለንጉሠ ነገሥቱ ስለነበር በእዚሁ መሠረት ምሕረት ማድረጉም የንግሠ ነገሥቱ ሥልጣን ነበር፡፡ እንደ አወጣጣቸው ቅደም ተከተል፣ አንቀጽ 16 እና 35 ላይም ይኸው ሁኔታ ተደነንግጓል፡፡ ባይሆን ሁለተኛው ላይ አሁን ምሕረት የምንለውን ‘ይቅርታ’ (አምነስቲ) በማለት አለዋውጦታል፡፡

በደርግ ዘመንም የነበረውን ብንመለከት አዋጅ ቁጥር 2/1967ን በማሻሻል፣ ‘’የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግንና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር108/1969’’ ምሕረት የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በላይ ለሆነው የደርግ አባላት በሙሉ የሚገኙበት ‘ጠቅላላ ጉባኤ’ መሆኑን አንቀጽ 5(7) ላይ ተደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ላይ ደግሞ ይሄው ምሕረት የማድረግ ሥልጣን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰበሰበውን የብሔራዊ ሸንጎውን ተግባር ወክሎ የሚሠራው ‘የመንግሥት ምክር ቤት’ እንደሆነ አንቀጽ 62(1)(ሠ) ላይ ተገልጿል፡፡ የመንግሥት ምክር ቤት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለየና በእርከንም ከፍ ያለ መሆኑን ያጤኗል፡፡

በደርግ ጊዜ የተሰጡት ሁለቱ ምሕረቶችም የተሰጡት ከእዚህ በራቀ አሠራር አይደለም፡፡ በእርግጥ፣ ከመስከረም 2/1967 ዓ.ም. ጀምሮ ቀድሞ የነበረው የዐጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ስለፈረሰ በአዋጅ ቁጥር 2/1997 መሠረት አዋጆችን የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው “ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ነበር፡፡ ይህ ቡድን ነው እነዚህን የምሕረት አዋጆች ያወጣቸው፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር ብቻውን ወይም ለደርጉ ተጠሪ የሆነ ሌላ አካል አላወጣቸውም፡፡

ከላይ ከተገለጹት ምክንያቶች በተጨማሪ፣ ሕግ አውጭው ወንጀል እንዲሆን የወሰነውን ድርጊትን ብሎም ይህን የወንጀል ሕግ የተላለፈውን ሰው አስፈጻሚው አካል በመያዝና በመቆጣጠር ለፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር ለወንጀል ፈጻሚዎች ምሕረት በማድረግ መተው እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ፓርላማው ያወጣውን ሕግ ከማክበር ውጭ በምሕረት ሰበብ መሻር አይችልም፡፡ በመሆኑም፣ ፓርላማው ያወጣውን ሕግ በልዩ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማድረግ የሚችለው ራሱ ነው፡፡

ምሕረት ለማድረግ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን በመለየት፣ የሚያስገኘው ጥቅም አሳማኝ እስከሆነ ድረስ ምሕረት ማድረጉ ያስፈለገበትን ምክንያት (ዓላማ)፣ የተጠቃሚዎቹን ማንነት በመወሰን በአዋጅ ምሕረት የማድረግ ሥልጣኑ የሕግ አውጭው (ፓርላማው) ነው፡፡

በመሆኑም፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በመንግሥትነታቸው ሳይሆን በድርጅታዊ ሥልጣናቸው ከሰጡት መግለጫ መረዳት የሚቻለው የድርጅታቸውንና የመንግሥታቸውን ፍላጎት እንደሆነ እንጂ በፓርቲው ሊቀመንበርነታቸውም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ምሕረት የማድረግ ሥልጣንን ያላቸው መሆኑን ሕገ መንግሥቱም ይሁን ሌላ ሕግ አይደግፋቸውም፡፡

የምሕረት ዓይነቶች፤

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድም የበለጠ ቅቡልነት ለማግኘት ምሕረቱ የሚሰጥበት ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በርካታ አገራት በፓርላማ ውሳኔ ሲሰጡ አንዳንድ ለሕግ የበላይነት ደንታ የሌላቸው መንግሥታት ባለቡት አገር ግን በሕግ ምሕረት ባለማድረግ ብሎም ሳይከስሱ በመተው በተዘዋዋሪ ምሕረት ያደርጋሉ፡፡

ስለዚህ በሕግ የሚሰጡና በተግባር በአስፈጻሚው ወንጀለኞችን ሳይከሥሱ በመተው የሚደረጉ በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ በደርግ የተደረጉት ከመጀመሪያው ምድብ ሥር የሚወድቁ ሲሆን የቤኒሻንጉሉ እና በሞላ አስገዶም ለተመራው ቡድን የተደረገው ምሕረት ግን በሁለተኛው ነው፡፡

ምሕረት በጅምላ ለሁሉም የወንጀል ድርጊቶች ሊሰጥ ይችላል፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ሙሉ በሙሉ በመተው ሁሉንም የወንጀል ድርጊትና ወንጀለኛ ምሕረት ሊደረግ ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረገው ብዙ ጊዜ መንግሥት ሲቀየር ነው፡፡

አንድ መንግሥት በሥልጣን ላይ እያለ በርካታ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽሞ ነገር ግን ሥልጣኑን ለሕዝብ ለማስረከብ በሚወሰንበት ጊዜ በተተኪው መንግሥት በወንጀል እንዳይጠየቅ የሚያደርግ ሕግ በማውጣት ለራስ ምሕረት (self-amnesty) ማድረግም በአንዳንድ አገራት ተለምዷል፡፡ እ.አ.አ. በ1983 የአርጀንቲና ወታደራዊ መንግሥት ለራሱ ምሕረት ሰጥቶ ሥልጣን አስረክቧል፡፡ በጓቴማላም እና በቺሊም እንዲሁ ተደርጓል፡፡

ለፖለቲካዊ ወንጀሎች ብቻ የሚሰጥ የምሕረት ዓይነትም አለ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ አገዛዝ በኋላ፣ ሩዋንዳ፣ ሴራሊዮን ወዘተ በተለያዩ ጊዜያት ተደርጓል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች በራሳቸው ወንጃላቸውን በመግለጽ የምሕረቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተመሠርቶ የሚሰጥ የምሕረት ዓይነትም አለ፡፡ የፈጸሙትን ወንጀል መናዘዝ፣ ተጎጅዎችን በይፋ ይቅርታ መጠየቅና ጸጸትን በዐደባባይ መግለጽ፣ ካሳ ለመክፈል መስማማት፣ ነፍጥ አንስቶ የሸፈተ አማጺ ቡድን ከሆነ ደግሞ ነፍጡን ማስረከብ፣ ስለአማጺ ቡድኑ እና አባላቱ መረጃ መስጠት፣ በቀሪዎቹ ላይ ለሚቀርብ ክስ ለመመስከር መስማማት፣ ወዘተ የሚሉ ሁኔታዎችን አስቀምጦ እነዚህን ለሚያደርጉ ብቻ ምሕረት ሊሠጥ ይችላል፡፡

በሌሎች የትግል አጋርና ጓድ ላይ እንዲመሰክሩ የሚያድረግ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ ምሕረት ዋና ግቡ እውነትን በማውጣት ዋና ዋና መሪዎችን በፍርድ ሂደት እንዲያልፉ በማድረግ በከፊል ለሰላም፣ በከፊል ደግሞ ለፍትሕ ዋጋ ለመሥጠት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡

የደርጉ የመጀመሪያው የምሕረት አዋጅ በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠው ሽፍቶቹ በግለሰቦች ላይ ጉዳት አድርሰው ከሆነ ከግል ፈላጊዎቻቸው ጋር በሽምግልና ዕርቅ መፈጸም ያለባቸው መሆኑን በግዴታነት አስቀምጧል፡፡ ዘማቾቹን በተመለከተ ደግሞ ማንኛውም ከክስና ቅጣት ነጻ የተደረገ ዘማች፣ በዘመቻ መምሪያው የበላይነት የዘመቻ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ዘመቻ ለማይሄድ ግን ከምሕረቱ ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ እነዚህ

አንቀጽ 230 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ምሕረት በሚሰጥበት ጊዜም ያልምንም ገደብ ሊደረግ እንደሚችለው ሁሉ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ለሚያሟሉ ብቻ ምሕረት ሊደረግ እንደሚችልና ሕጉ ይሄንን መያዝ እንዳለበት አስቀምጧል፡፡

ማጠቃለያ ነጥቦች፤

የምሕረት አዋጅ በግልጽ ተጠቃሚዎቹ እነማን እንደሆኑ ለይቶ ማስቀመጥ አለበት፡፡ እንዳንዴ በአንድ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ቢሳተፉም መሪውን፣ የድርጊቱን ዋና አቀናባሪ፣ፖሊሲ አውጭዉን ወዘተ በመተው ለሌሎች ብቻ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የመሪዎቹን በፍርድ፣ የሌሎቹን በምሕረት ለመጨረስ ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ አገራዊ መግባባትን እንደግብ የሚወስድ ምሕረት ግን እንዲህ ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን አያስቀምጥም፡፡

ምሕረት የተደረገላቸውን ሰዎች በሕጉ ላይ በሚገለጽ ጊዜና ቦታ በመቅረብ ምሕረቱን መቀበላቸውን ማመልከት የሚገባቸው ከሆነም ይሄንኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ደርግ የሰጣቸው ሁለት ምሕረቶች በዚህ መልኩ ሆነው እስከመቼ እና የት መመዝገብ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡

ምሕረት ከተደረገ የወንጀል ታሪክም አብሮ ይደመሰሳል፡፡ ይቅርታ ሲሆን ግን ወንጀለኛነቱ እንደተመዘገበ ይቆያል፡፡ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነትን በተመለከተ ግን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 231(1) ላይ ምሕረት የተደረገለት ሰው ግለሰቦች ላይ ጉዳት አድርሶ እንደሆነ ካሳ እንዳይከፍል የሚያደርግ ምሕረት መስጠት እንደማይቻል አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም፣ ጉዳት ደረሰብን ባዮች ከፈለጉ በፍትሐ ብሔር መጠየቅ ይችላሉ፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ደግሞ ጉዳቱ የደረሰው መንግሥት ላይ ከሆነ ምሕረቱ ከወንጀሉ ብቻ ሳይሆን ካሳ ከመክፈልም ጭምር መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዋጋ የሚተመን ጉዳት ቢደርስም እንኳን ለመንግሥት እስከሆነ ድረስ ምሕረቱ ይህንንም ያካትታል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በምሕረት ማድረጊያው ሕግ በልዩ ሁኔታ በማስፈር ለመንግሥትም ቢሆን ካሳ እንዲከፈል ሊደረግ ይችላል፡፡ በመሆኑም፣ በመርሕ ደረጃ ለግለሰብ ተጎጂዎች ካሳ የመክፈል ግዴታ ሲኖርባቸው፣ ለመንግሥት ከሆነ ግን በምሕረት አዋጁ ካልተገለጸ በስተቀር ከካሳ ነጻ ናቸው፡፡

ምሕረት ለግለሰቦች በተናጠል ሳይሆን በጥቅል ለቡድን ወይም ለሆነ ጉዳይ ይደረጋል፡፡ የተለያዩ አገራዊ ችግሮች ላይ ዕልባት ለማድረግ በአዋጅ የሚሰጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን የአሁኑ ሕገ መንግሥት ባልተለመደ ሁኔታ ምሕረት የማድረግ ሥልጣን የማን እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጥም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጭ እንደማይሆን አይተናል፡፡ አስቀድሞ በሚወጣ ሳይሆን ምሕረቱ በሚደረግበት ጊዜ ነው ሕጉ የሚወጣው፡፡ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርም የፖለቲካ ምህዳሩንም ለማስፋት ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡

(ይኼው ነው!)

Filed in: Amharic