>
5:13 pm - Tuesday April 18, 2884

''ከምኒልክ በፊት እግዚአብሔር የእኔን ሞት ያስቀድም'' ንጉሥ ተክለሃይማኖት  (በጳውሎስ ኞኞ)

በቀድሞ ስማቸው አዳል ተሰማ ይባሉ የነበሩት ንጉሥ ተክለሃይማኖት ከአባታቸው ደጃች ተሰማና ከእናታቸው ወ/ሮ ምዕላድ በ1830ዓ/ም ተወለዱ፡፡ አዳል ገና በልጅነት እድሜያቸው አባታቸው በግዞት ስለተወሰዱ ወደ አጎታቸው ደጃች ተድላ ጎሉ ዘንድ ተጉዘው ማደግ ጀመሩ፡፡ በዚያም ሳሉ የ15 ዓመት ልጅ እንደሆኑ የጉርምስና እድሜ አሳስቷቸው ከደጃች ተድላ ጎሉ ዕቁባት ጋር የፍቅር ግንኙነት በመጀመራቸው ከደጃች ተድላ አምልጠው ወደ ዳሞት ሸፈቱ፡፡ ከአጎታቸው ተድላ ጎሉ ጋርም ተባራሪና አባራሪ ሆነው ሳለ ኢትዮጵያን ለሦስት ዓመታት ከመሩት ከተክለጊዮርጊስ ጎን በመቆማቸው ኃይላቸው በርትቶ የራስነት ማዕረግን አገኙ፡፡ በመቀጠልም አጼ ዮሐንስ ሲነግሱ ራስ አዳል የሚለው ስማቸው ተቀይሮ “ተክለሃይማኖት ንጉሠ ከፋ ወጎጃም” ተብለው ተሾሙ፡፡ በዚህም ዘመን ንጉሥ ተክለሃይማኖት ከጎጃም አጼ ምኒልክ ከሸዋ ተነስተው በሚያደርጉት የግዛት ማስፋፋት እርስ በርሳቸው ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው እምባቦ በሚባል ስፍራ ጦርነት አድርገው ድሉ የምኒልክ ሆነና ንጉሥ ተክለሃይማኖት ቆሰሉ፡፡ አጼ ምኒልክም ንጉሥ ተክለሃይማኖትን በሕዝብ ፊት አቅፈውና ስመው ደማቸውን በለበሱት ጋቢ ጠረጉላቸውና አሳከሟቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የአጼ ምኒልክና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጠላትነት አብቅቶ በፍጹም ወንድማማችነት ፍቅር ተተካ፡፡ አጼ ዮሐንስ ሞተው ምኒልክ ሲተኩም ንጉሥ ተክለሃይማኖት ምንም ሳያንገራግሩ የምኒልክን ንጉሠ ነገሥትነት ተቀበሉ፡፡ በአድዋ ዘመቻም ከምኒልክ ጎን ተሰልፍው የድሉ ተጋሪ ሆኑ፡፡ ንጉሥ ተክለሃይማኖት በአጠቃላይ በአስተዳደር ዘመናቸው ደግና ሁሉን መጋቢ የነበሩ ቢሆንም አንዳንድ ክሶች ግን ምኒልክ ዘንድ ይቀርብባቸው ነበር፡፡ ምኒልክም “ና ተከሰሃል ቅረብና ተናገር” ከማለት ይልቅ ከከሳሾቻቸው ጋር በዘዴ ሊያስታርቋቸው ይሞክሩ ስለነበር ንጉሥ ተክለሃይማኖት “ጃንሆዬ ለኔ ሁልጊዜ እንደተመቹኝ ነው እግዚአብሔር ያስመችዎ….. ጃንሆይ እንደ ፈጣሪዎ እንደ ክርስቶስ ሰው አለማስቀየም ልማዶ ነው፡፡” ብለው ደብዳቤ እስከ መጻፍ ደርሰው ነበር፡፡ በተጨማሪም ንጉሥ ተክለሃይማኖት ምኒልክን እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ በደብዳቤዎቻቸው ላይ ሁሉ በቁልምጫ ‘ጃንሆዬ’ እንደሚሉና ሁልጊዜም “ከምኒልክ በፊት እግዚአብሔር የእኔን ሞት ያስቀድም” ይሉ እንደነበር ተጽፏል፡፡ በመጨረሻም ንጉሥ ተክለሃይማኖት በታህሳስ ወር የጀመራቸው ህመም ጸንቶባቸው እንደተመኙት ከምኒልክ ቀድመው የዛሬ 117 ዓመት በዕለተ አርብ ጥር 3 ቀን 1893 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ራሳቸው ቀድመው ባሰሩት መካነ ጎሎጎታ ከጳጳሱ አቡነ ሉቃስ ጎን ተቀብረዋል፡፡

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ታሪክ በአለቃ ተክለኢየሱስ
– የኢትዮጵያ ታሪክ ከቴዎድሮስ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ እና አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በተክለጻዲቅ መኩሪያ
– አጤ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ
Filed in: Amharic