>
5:13 pm - Saturday April 19, 5902

ደኢህዴን ለህወሃት ለምን ጭራውን ይቆላል ? (ዮሴፍ ይጥና)

በደቡብ ክልል ከ56 በላይ ብሄረሰቦች ይገኛሉ ።ሁሉም የራሱ ቋንቋና ባህል ቢኖረውም የሚወራረሰውም አለው።

ደኢህዴን እነዚህን የሚወክል ድርጅት ነው።ነገር ግን የሁሉንም ፍላጎት የማያሟላ የግለሰቦች መፈንጫና መበልፀጊያ ድርጅት ነው።

በደቡብ ክልል አጋሚዶው ስርዓት ይህ ነው የማይባል በደልና ወንጀል ፈፅሟል።ነገር ግን አመራሮቹ ህዝብን ከማፈን ውጪ ለህዝብ መብት ቆመው የታዩበት አንድም ጊዜ የለም።

ሲዳማው የጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድበት ፣ኮንሶው እሳት ሲነድበት ፣የቁጫ ህዝብ በጠራራ ፀሃይ ሲፈጅ ፣ጋሞጎፋ ግፍ ሲዘንብበት ፣ጌዴኦ ላይ ሴራ ሲጎነጎንበት ፣ሃዲያው ፕ/ርበየነ ጴጥሮስን ደግፈሃል ተብሎ ከሁሉም ነገር ሲረሳ ፣ጉራጌውንም በቂም የልማት ተቋዳሽ እንዳይሆን ሲደረግ ፣ሃመር ፣ፅፀማይና በና እንደ እንስሳ ሲታደን ፣ኛንጋቶም በስኳር ፕሮጀክት ስም በገፍ ሲፈናቀልና ሲገደል ደኢህዴን በዋና ተዋናይነት ወንጀልም ሃጥያትም ሰርቷል።

ሁሉን መዘርዘር ስለሚከብድ ነው እንጂ ግፉማ የትየለሌ ነው።

የደቡብ ባለስልጣናት ከማዕከል የወረደን መመሪያ ሳይከልሱ ሳይበርዙ ህዝቡ ላይ ያወርዱታል።ይተገብሩታል።የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታ ማገናዘብ ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም።

ከዛም በላይ የደቡብ ባለስልጣናት ወደ ፌደራል በእድገት የሚዛወሩት ከሰው ተሽለው ፣ብቃት እና እውቀት ኖሯቸው ፣በመልካም ስራ አፈፃፀማቸው ወዘተ አይደለም።ይልቅስ በሴራቸው ፣ለህወሃት ባላቸው ታማኝነት ፣ከህዝብ ይልቅ ከርሳቸውን ያስቀደሙ መሆናቸው በተግባር ስለተረጋገጠ ፣ህሊና ቢሶች ስለሆኑ ፣በሙስና በሌብነትና በደም የተጨማለቁ በመሆናቸው ነው።

በሹመት ወደ ፌደራል ከሄዱም በኋላም። ክልሉን ወይም ዞኖችን በእጅ አዙር የሚያስተዳድሩት እነርሱ ናቸው።የክልል አስተዳዳሪ እና የካቢኔ ሹመት የሚሰጠውም በእነርሱ በጎ ፈቃድ ነው።

ሲራጅ ፈጌሳ እስካሁን ስልጤ ዞንን ያሽከተክራል።ሽፈራው ሽጉጤ ሲዳማ ዞንን እንዳሻው ይዘውራል ።ሃይለማርያም ክልሉን ይመራል።ሁሉም ስልጣናቸውን እስካሁን እየተጠቀሙበት ነው።ያለእነርሱ ወንበር የሚያገኝ ማንም የለም።

የሚያስቀው ደግሞ ወደፌደራል የተሾሙት የደቡብ ሰዎች የየብሄረሰባቸውን ልማት ማህበር በቀጥታ የቦርድ አባል በመሆን ህዝቡን ይመዘብሩታል።እነርሱ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ይሾሙና የግል ብልፅግናቸውን ያካሂዳሉ።

የስልጤ ልማት ማህበር በግልፅ የግለሰብ መጫወቻ ነው ።ሃላፊ የሚደረጉት በነ ሲራጅና ረድዋን ሁሴን ፈቃድ ሲሆን ለፈፀሙት ታማኝነት (ሌብነት )የግል አስመጪና ላኪ ሃብታም ሆነው ስራቸውን ይለቃሉ።

የሌሎቹም ልማት ማህበሮች እንዲሁ ነው ።ሽፈራው ሽጉጤ በየቀኑ 50 ሺህ ብር አካውንቱ ውስጥ ይከተትለታል።ከደቡብ ክልል።

እዛ ሙስና ወንጀልም ሃጥያትም አይደለም።ሁሉም እንዳቅማቸው ያነኩሩታል።እሽቅድድም ውስጥ ገብተዋል።ላጋልጥ የሚል አለቀለት ።እዛ ወንጀለኛው የሚሰርቀው ሳይሆን ላጋልጥ የሚለው ነው።

ህዝቡ ደላው አልደላው ግዳቸው አይደለም።በተዋረድ ያሉት ሹመቶች ባብዛኛው ቤተሰባዊ ትስስር ያላቸው ናቸው።ህዝቡን እንደ ጭሰኛ ነው የሚቆጥሩት ።

የህዝቡ ፍላጎት ረይጠየቅም።የአጋሚዶውን ፍላጎት ግን ባንድ ጀምበር ያስፈፅማሉ ።ህዝቡ እጅግ ይፈራቸዋል።1 ለ 5 ጠርንፈው በወሬ ብቻ ከመሬት ተነስተው ያስራሉ ።ሌላው ይፈራል ።ህዝቡ ፀጥ እንዲል ያደረጉት እኒህ ከርስ አደሮች እና የዘረጉት ሰንሰለት ነው።

በማያዙበት ስልጣን የሚቆለሉት እኒህ ድኩማን ህሊና የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም።የአገሪቷ ህዝብ በጭንቅ ላይ ርያለ ከመካከላቸው አንዳቸውም ጥያቄ መጠየቅ አልፈለጉም።

ይልቅም ከገዱና ከነ ለማ በተቃራኒ ሆነው ጭራቸውን በመቁላት ለሽፍታው ቡድን ታማኝነታቸውን ሲያሳዩ ነው የከረሙት።

የደቡብ ህዝብ እምቢ ማለትን ከኮንሶ ወንድሙ መማር አለበት ።አሁንም ድረስ ጫካ እየኖሩ መንግስትን ተገዳድረውታል።ትምህርትም ስራም በማቆም ትግላቸውን ቀጥለዋል።እሳት ቢዘንብባቸውም ተስፋ አልቆረጡም።

ነፃነት ያለመስዋዕትነት አይገኝም።የደቡብ ህዝብ በከፋ ጭቆና ውስጥ ነው ያለው።መነሳት ያለበት ግን እራሱ ነው ።ሹመኞቹ እንደሆኑ ድሮም አልሰሩለትም ።ሰሩበት እንጂ።በስሙ እየነገዱ የግል ምቾታቸውን ይጠብቃሉ።በማያዙበት ስልጣን ይኮፈሳሉ ።በሽፍቶች እየተሰደቡ ይቆለላሉ። ጭራ የሚቆሉት ስድብ እየጠጡ ውስኪ ለመጨለጥ ነው ።የሚያሸረግዱት እየተዋረዱ ህዝብ ላይ ለመጎረር ነው ።

ከእንዲህ አይነቱ ውሻነት ምናለ ሁሉስ ቢቀር !

Filed in: Amharic