ዛሬ ሁሉም ለክልሉ እንጂ ለሀገሩ እንደሚገነባ አያስብም፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ፣ የሌላትን ገንዘብና ሀብት የህዝቦችን አመጽ ለማቆምና በዚህም የገዢዎችን ስልጣንን ለማደላደል እያባከነችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ክልሎች ለምን ለሙ?›› የሚል ብኩን ተጠየቅ ለማንሳት ፈልጌ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ዩኒቨርሲቲን ለየብሄሩ ለማዳረስ በየምድረበዳው (ለትራንስፖርትና ለአቅርቦት አስቸጋሪ በሆነ ቦታ) መገንባት ከዚህ ተለይቶ የሚታይበት ሁኔታ አልታየኝም፡፡ ቤተመጻህፍት፣ ላብራቶሪ (ቤተሙከራ) እና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች የተሟሉላቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሌሏቸው አካባቢዎች፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን›› ብለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡት፣ ከሌላው ክልልና ብሄረሰብ እንዳያንሱ እንጂ፣ በጤነኛ አእምሮ ለልጆቻቸው አስበው አይመስለኝም፡፡ ለልጆቻቸው አስበው ቢሆን ኖሮ፣ ከዩኒቨርሲቲው ህንጻ በላይ 12ኛ ክፍል ጨርሰው የስምንተኛ ክፍል ፈተና የሚወድቁ ልጆቻቸው የወደፊት ህይወት ያስጨንቃቸው ነበር፡፡
ከሱማሌ ክልል ወደሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቀሉ – እነዚህ ሰዎች ለሱማሌዎቹ ኦሮሞዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ በኦሮምያ ክልል ስኳር የጫኑ መኪኖች እንዳያልፉ ተደረገ – እነዚህ መኪኖች ስኳሩን የጫኑት ለሌላ ክልል ህዝቦች እንጂ ለኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ የራሱን ክልላዊና ጎሳዊ ማንነት ያደመቀ ህዝብ፤ ሌላውን ህዝብ በኢትዮጵያዊነት መለጽር ሊመለከት አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በ27 አመት የአስተዳደር ጊዜው ኢትዮጵያን በጎሳዊ – ክልል እንደመከፋፈል ውጤታማ የሆነበትን ተግባር አላከናወነም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክልሎች መካከል እጅግ ያልተመጣጠነ ልማታዊ እድገትም የታየው በዚሁ በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ነው፡፡ አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ከሀገሪቱ ውስጥ ተቆርጠው የወጡ ይመስል በወረፋ ከሚዳረሰው የኢቢሲ የልማት ዘገባ እንኳን ሲጠፉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ልማታዊ ባለሀብት ሌማት በቀን ሶስት ጊዜ በየቲቪው ሲቀ ርቡ፣ እራሱ ኢህአዴግ በየአካባቢው እንዲዳብር ያደረገው ጎሳዊ ጡንቻ ዝም ብሎ ያየኛል ብሎ መጠበቁ የሚገርም ነው፡፡
. .. . . . አሁን ኢህአዴግ በየአካባቢው ለ27 አመት የተመጣጠነ ምግብ እየመገበ፣ አካል ብቃት እንቅስቃሴ እያሰራ ያዳበረው ጎሳዊ ጡንቻ ምን ሊያመጣበት – ሊያመጣብን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ እና አሁን ኢህአዴግ ማድረግ ያለበት ‹‹የግጭቶች መንስኤ የፌደራል ስርአቱ እንዳልሆነ ምሁራን ገለጹ›› የሚል ፕሮፖጋንዳ መስራት ሳይሆን፣ የፌደራሊም ስርአቱን ማሻሻል ወይም ሙሉ በሙሉ መቀየር ነው፡፡
የሆነው ሁሉ የሆነው እንደ ኢትዮጵያዊ መኖርና ማሰብ እንድናቆም በመደረጉ ነው!(ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
Filed in: Amharic