>

የቄሮዎች እንቅስቃሴ የመንግስትን መዋቅር ከጥቅም ውጪ አድርጎታል (ኢሳት) 

የኦሮሞ ወጣቶች እያደረጉ ያሉት ትግል ያሳሰበው የሕወሃት አገዛዝ በቄሮዎች ላይ ምርመራ ጀመርኩ አለ። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ምርመራውን ከንቱ ድካም ሲል አጣጥሎታል። የፌደራል ፖሊስ ቄሮ ተብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ምርመራ ጀመርኩ ባለበት መግለጫ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመንግስት መዋቅር ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ያመነበት መሆኑ ታውቋል።
የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን ከእጃችን አልወጣም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የታሰበ መግለጫ ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሰፋ ባዩ ባለፈው ሃሙስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተናገሩበት ጊዜ ነው ቄሮ ላይ ምርመራ ጀምረናል ያሉት። የቄሮዎች ትግል ከአገዛዙ አቅም በላይ መሆኑን መረጃዎች በሚያመላክቱበት በዚህን ወቅት ነው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ መጀመሩን ያስታወቀው። ፌደራል ፖሊስ እንዳስታወቀው በተለይ በምስራቅ ሐረርጌ የቄሮዎች እንቅስቃሴ የመንግስትን መዋቅር ከጥቅም ውጪ አድርጎታል። ፋይል የአካባቢ ባለስልጣናትን መሾምና መሻር ፣መንገዶችን በመዝጋት እስረኞችን ማስለቀቅ በስፋት በቄሮዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ያመነው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የመከላከያ ሰራዊቱንና የፌደራል ፖሊስ ተልዕኮንም አስተጓጉሏል ሲል ከሷል። ኢሳት ያነጋገራቸው የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ኦፌኮ አመራር አባላት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቄሮዎች ላይ ምርመራ ጀመርኩ ያለው ከንቱ ርምጃ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
 ከ20 ሚሊየን በላይ በሆነው የኦሮሞ ወጣት ላይ በምን ተአምር ምርመራ ይደረጋል ሲሉም በአግራሞት ይጠይቃሉ የኦፌኮ አመራር አባላት። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከዚህ ቀደም ቄሮ ጠላት አይደለም፣ይሄን ወጣት በጠላትነት ፈርጀን እንዴት ሀገር እንመራለን?ይህ መቼም የማይሆን ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቄሮዎች ላይ ምርመራ ጀመርኩ ይላል እንጂ መቼና በምን መልኩ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ዝርዝር ማብራሪያ አላቀረበም።
 ኢሳት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ጉዳዩን ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ሲሉ ይገልጹታል። በሕቡዕ ይንቀሳቀሳል ብሎ መንግስት የሚያምን ከሆነ እንዴት በይፋ ምርመራ ጀመርኩ ተብሎ ይገለጻል ያሉት እነዚህ ታዛቢዎች አጀንዳ መፍጠር ትኩረት ለማስቀየስና ፍርሃት ለመልቀቅ ታስቦ የተዘጋጀ የፕሮፓጋንዳ አካሄድ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። የቄሮዎች ትግል በሁሉም የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተዳረሰና ከዚያም ባለፈ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር እየተቆራኘ መምጣቱ ለሕወሃት አገዛዝ ትልቅ አደጋ መደቀኑን የሚገልጹት የፖለቲካ ምሁራኑ የማይቀለበስን ትግል በዚህ መልኩ ማዳፈን መሞከር የማይቻል ነው ይላሉ። የአቶ ለማ መገርሳ አመራርን ለማንበርከክና ከቁጥጥራችን አልወጣም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚሆንም ምሁራኑ ይገልጻሉ።
Filed in: Amharic