>

ቄሮ የድርጅት ስም አይደለም የትውልድ እርከን ነው (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባለፈው የኢሬቻ በዓል አከባባር ላይ ሳይጠየቁ እና ከክልሉ አመራር ጋር ምንም ሳይነጋገሩ ለበዓሉ አከባበር ፌደራል ፓሊስ፣የደህንነት መስሪያ ቤት እና የመከላከያ ሰራዊት ለበዓሉ አከባበር ጥበቃ ያደርጋል ብለው መግለጫ ሰጡ።
በወቅቱ የክልሉ መንግስት ለበዓሉ አከባበር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት ሰለነበር ከአባገዳዎች ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ ዝግጅት ነበረው።በስምምነቱ መሰረትም ለበዓሉ ጥበቃ የሚያደርጉት ያልታጠቁ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት እና ፎሌዎች ብቻ ናቸው።ስለዚህ የበዓሉ አከባበር 1 ቀን ሲቀረው የኦሮሚያ ፖሊስ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የሰጡትን መግለጫ የሚቃረን መግለጫ ለመስጠት ተገደደ። ለበአባሉ አከባበር ጥበቃ የጠየኩት ተጨማሪ የፌደራል መንግስት ኃይል የለም።የሚመጠም የለም።በዓሉ በአባገዳዎች ጋር በተስማማነው መሰረት ጥበቃ ይደረግለታል አለ።
እንደተባለው በዓሉ የኦሮሚያ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ መሰረት ጥበቃ ተደርጎለት በሰላም አለፈ።
አሁን ደግሞ ትንሽ እንኳን የህዝቡን ባህል እና የገዳን ስርዓት ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ እንዲሁም የክልሉ መንግስት በነገሩ ላይ ያለውን አቋም ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ በቄሮ ላይ ምርመራ እናደርጋለን እያሉ ነው።
ቄሮ ማለትስ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶአቸዋል?
በአጠቃላይ ወንጀል የፈፀመ አካል ካለ ህጉን ተክትሎ መጠየቅ አለበት። ምርመራውም ህጉን በተከተለ መልኩ መካሄድ አለበት።ወንጀሉን ለመመርመር ህጋዊ ስልጣን ያለው የፌደራል ፖሊስ ከሆነ ፌደራል ፖሊስ መመርመር አለበት።የክልል ፖሊስ ስልጣንም ከሆነ እንደዚያው ነው።
ከዚያ ውጭ ዝም ብሎ በዘልማድ ዘሎ መግባት እና እንደፈለጉት ማብኳት አሁን ጊዜው አይደለም።በክልሉ በፌደራል ፖሊስ ስም እስከአሁን የተሰራው ይበቃል።
ሌላው ነጥብ ወንጀለኛውን ለይቶ ማየትን ይመለከታል።ጠዋት ተነስተህ ኦሮሞ የሚባል ህዝብ ስላስቸገረ እመረምራዋለሁ አትልም።ቄሮን መረምራለሁ ማለት ኦሮሞን መረምራለሁ ከማለት በምንም አይለይም።ምክንያቱም ቄሮ የድርጅት ስም አይደለም።የትውልድ እርከን ነው።ማንኛዉም ኦሮሞ የሚይልፍበት የትውልድ እርከን ነው።አባት ቢያልፍ ልጁ እርከኑ ላይ ሊሆን ይችላል።ወይም ወንድምየው ወደ እርከኑ እየገባ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ይህንን የትውልድ እርከን በሙሉ ወንጀለኛ የሚያደርግ ሰው ፀቡ ከመላው ኦሮሞ ጋር ነው።ፀቡ ከክልሉ መንግስትም ጋር ነው።
Filed in: Amharic