>
5:14 pm - Wednesday April 20, 6327

«ጥልቅ ምርመራ» ከልምዳችን ስንነሳ ትርጓሜው «መንገድ ላይ የምታገኘውን የኦሮሞ ወጣት ሁሉ በቄሮ ስም እሰር!»ነው (ዮናስ ሃጎስ)

ኢህአዴግ ተፈጥሯዊው ባህርይው ለመታደስ የሚያበቃው አይደለም። ኢህአዴግ ኤክስፓየሪ ዴቱን ግንቦት 97 ላይ ጨርሶ በኦክሲጅን ቅጥያ ሕይወት እየኖረ ያለ የበሰበሰ ድርጅት ነው። ኢህአዴግን ለማደስ መሞከር ለዘመናት ያህል ሲሰሩ የነበሩና በብልቃጥ ታሽገው ተቀምጠው ያሉ የወንጀል ክምሮችን የብልቃጡን ክዳን ከፍቶ ማውጣት ማለት ነው። በኢህአዴግ ውስጥ በወንጀል ያልተነካካ ሰው ማግኘት አዳጋች ስለሚሆን ሁሉም ተያይዘው የሚያልቁበት ክስተት ነው የሚሆነው። ያንን እሽግ የወንጀሎች መዓት የያዘውን ብልቃጥ ሳይከፍቱ ደግሞ ስለ ተሐድሶ ምንም ማውራት አይቻልም።

•°•
ከወራት በፊት ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን ካረጋጋ በኋላ ወደ ኦሮሚያ መዝመቱ የማይቀር መሆኑን አስረግጬ ተናግሬ ነበረ። ያ ቀን ዛሬ ላይ መድረሱን መገመት ይቻላል። የፌደራል ፖሊስ በቄሮዎች ላይ «ጥልቅ» (አቤት ይህቺን ቃል ሲወዷት) ምርመራ ለማድረግ መወሰኑ ዛሬ ላይ በድንገት የተወሰነ ነገር አይደለም።
•°•
የአቶ ለማ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት ይታያል። ከኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች የተነሳው ብሔር ተኮር ሰደድ እሳት እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ድረስ ዘልቆ የብዙ ተማሪዎችን ሕይወት አጥፍቷል። ብዙ ከተወለዱበት ከተማ ርቀው የተመደቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ትምህርት አስተጓጉሏል። ብዙ ተማሪዎችን ከቤት እንዲቀሩ ምክንያት ሆኗል። በጎሳ ተኮር ግጭት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ኦሮሞዎችን ሲፈናቀሉ ለማየት በቅተናል። ከዚያው ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ ብዙ የሌላ ብሔር ተወላጆች ተፈናቅለዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል። የክልሉ አስተዳደር ልዩ ፖሊሶች በድንጋይ ተወግሮ ከሞተ ወጣት ጀርባ ፎቶ ከመነሳት ጀምሮ ተቃውሞ ያነሱ ሰልፈኞች ጋር በጋራ ሆነው በፊት ለሲቪልያኑም ያስፈራ የነበረውን እጅ ማጣመር ምልክት እያሳዩ ታይተዋል። አስተዳደሮች ለተቃውሞ ሰልፈኞች ድጋፍ እስከ መስጠት የደረሱበት ሁኔታ ታይቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ኦህዴድ እንደ ክልል አስተዳዳሪነቱ ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር ከኢህአዴግ ራሱን ካላገለለ በቀር ሌሎቹ የኢህአዴግ ድርጅቶች ፍላፃቸውን እንደሚያዞሩበት ግልፅ ነበረ።
•°•
አሁን የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ አልቋል። እነ ለማ በዝረራ ተሸንፈዋል። አገኘነው የሚሉት ድል «የሕሊና እስረኞች መፈታት» ጉዳይ ራሱ እክል ገጥሞት ባለበት ቆሟል። ከቃላት ድርደራ ውጭ እነ ለማ ለሕዝባቸው ሊተያሳዩት የሚችል አንዳችም ድል አልተጎናፀፉም።
በነለማ ተቃራኒ የቆሙት አካላት (ሕወሐትና አጋሮቿ) ግን በየዕለቱ አዳዲስ ድል እያስመዘገቡ ነው። በስራ አስፈፃሚው የተወሰነውን የፖለቲከኛ እስረኞች የመፍታት ውሳኔ ተፈፃሚ እንዳይሆን ገትሮ የያዘው ሕወሐት የሚቆጣጠረው የደህንነት ቢሮ ነው። አሁን ደግሞ በፌደራል ፖሊስ አማካይነት በነለማ ኦህዴድ እና በሕዝቡ እየታገዘ ሲታገል የነበረውን የቄሮ ስብስብ ላይ «ጥልቅ ምርመራ» ለማድረግ ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል እያሉ ነው። ከዛ በተረፈ ለሕወሐት ከዚያ ስብሰባ በሰላም መውጣቷ በራሱ ትልቅ ድል ነው።
•°•
እነ ለማ ኢህአዴግ ውስጥ ያላቸው ቁጥር ትንሽ ነው። የኢህአዴግ ስብስብ ውስጥ የሕዝብ ድጋፍ አንዳችም ሚና የለውም እንጂ እነ ለማ ባላቸው የሕዝብ ድጋፍ መመርኮዝ ቢችሉ ስራ አስፈፃሚው ሐይለማርያምን አውርዶ ለማን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ባደረገ ነበረ። ነገር ግን ኢህአዴግ ውስጥ ያለው ትግል የቁጥሮች ጨዋታ ነው። ሕወሐት፣ ደኢህዴግ፣ ከብዓዴንና ኦህዴድ ለሕወሐት ያደሩ አባላት ቁጥር ተደማምረው ሕወሐትን ማሸነፍ እጅግ አዳጋች ያደርጉታል።
•°•
የፌደራል ፖሊሱ «ጥልቅ ምርመራ» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ባይታወቅም ቅሉ ከልምዳችን ስንነሳ ትርጓሜው «መንገድ ላይ የምታገኘውን የኦሮሞ ወጣት ሁሉ በቄሮ ስም እሰር!» ከሚል የዘለለ አይሆንም። በዚህ የቄሮውን ትግል ማዳከም ቢችሉም ቅሉ እስሩ ደግሞ ሌላ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቅስ ይችላል። ያንን ሕዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ እነ ለማን አጠቃልለው ለማስወገድ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
•°•
ስናጠቃልለው አቶ ለማና ካቢኔያቸው አሁን ለሕዝቡ የሚያቀርቡት ገፀ በረከት የሌላቸው መሆኑ የደጋፊዎቻቸውን ቁጥር በጥቂት ቀንሶታል። (ስብሰባው ላይ እንዲህ ብዬ ነበረ። በድምፅ ብልጫ ተሸንፌ ነው እንጂ… ካስፈለገ 17ቱን ቀን ስንወያይ የነበረው አንድ በአንድ ለሕዝብ ይቅረብ… ዓይነት ወሬዎች ውጤት አይሆኑም። ውጤት ማለት ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ «የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!» ሲል ደህንነቱ (ከስራ አስፈፃሚው በወጡ ሰዎች የሚታዘዝ መ/ቤት እንደሆነ ሳንረሳ…) «አልፈታም! ምናባታችሁ ታመጣላችሁ!» ሲል ነው። ይህ ሕወሐትን ለሚደግፉ አካላት ድርጅታቸው አሁንም ጠንካራ እንደሆነ የሚያሳያቸው ሲሆን የለማ ደጋፊዎች ግን ከዚህ በኋላ ከለማ እናየዋለን ብለው የሚጠብቁት ነገር ያላቸው አይመስልም።
•°•
ይህ እያለ የቄሮዎች «ጥልቅ ምርመራ» ከጀመረና አቶ ለማ ለማስቆም ምንም ማድረግ የማይችሉ ከሆነ አንደኛ በኦሮሚያ መስተዳድር ውስጥ ያላቸው መዋቅር ዓይናቸው እያየ መፈራረሱ ነው። ሁለተኛ ወጣቶቻቸው በስመ «ቄሮ»ነት ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ ሲጋዙ ምንም ማድረግ የማይችሉ ከሆነ የሕዝባቸውን ደህንነት መጠበቅ አይችሉም ማለት ነውና ከደጋፊዎቻቸው አብዛኞቹ እንደሚሸሿቸው አያጠራጥርም። በዚያ ላይ ያንን እስር ተከትሎ የሚመጣው ተቃውሞ መጀመርያ የሚያነድደው የርሳቸውን ካቢኔ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
•°•
ምን ተሻለ ታድያ?
•°•
አቶ ለማ እውነተኛ የለውጥ ሐዋርያ ለመሆን ካሰቡ ኢህአዴግ የሚባለውን የእቃ እቃ ውሸት ጨዋታ ጥለው በመውጣት እንደ ጲላጦስ እጅዎትን ታጥበው ሕዝብዎትን ለእስካሁኑ ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብዎታል። እርስዎ ከሚልዮኖች ደጋፊዎች ጋር የለቀቁትን ወንበር በኦሮሚያ ውስጥ ምንም ድጋፍ የሌላቸው እነ ኩማ ደመቅሳ ሊቀመጡበት ይከጅላሉ ብለው አያስቡ! ይልቅስ ከዚህ ድሪቶ ራሰዎትን ያላቅቁና በእውነተኛው ህዝባዊ ትግል ላይ ለመሳተፍ ይወስኑ። አውቃለሁ እስር ወይ ድብደባ አሊያም ሞትም ድረስ ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን የእርስዎ ሞትም ሆነ ድብደባና እስራት ለኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ ትንሳዔ እንደሚሆን ጥርጥር የለውምና።

Filed in: Amharic