>
5:14 pm - Tuesday April 20, 1706

መንደርተኛው የህወሃት ቡድን ለጊዜውም ቢሆን በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላይ የበላይነቱን ሊያስቀጥል ችሏል። (አበጋዝ ወንድሙ)

በቅርቡ ከተጠናቀቀው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በፊት ፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተካሄዱት
ስብሰባዎች በአማካይ የፈጁት ጊዜ ሁለት ቀናት ብቻ ሲሆኑ፣ የዘንድሮው 17 ቀናት የፈጀ መሆኑ የሚጠቁመው
በድርጅቶቹ መሃል ያሉትን በርካታ አለመግባባቶች በአጭሩ ለማስማማት አለመቻሉን ነው። ከወሰደው የጊዜ
እርዝማኔ በላይ የዘንድሮውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው፣ ልክ በቅርብ እንደተጠናቀቀው የህወሃት መሃከላዊ
ኮሚቴ ስብሰባ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴው አባላት ያልሆኑ በርካታ የቀድሞ አባላት የስብሰባው(ምናልባትም
የውሳኔው) ተካፋይ መሆናቸው ነበር።
የሀውሃትን አመራር የጨበጠ ቡድን ድርጅታዊ ውሳኔዎች ለሱ በሚመቸው መንገድ እንዲቃኝ ሲፈልግ
የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ ስብሰባዎችን ያለቅጥ በማርዘም ፣በመሃልም ስብሰባው ሲጀመር ያልነበሩ
አጀንዳዎችን ወደፊት በማምጣት፣ከሱ በተጻራሪ የቆሙ አባላትን ቢቻል ለመከፋፈል አለበለዚያም ነጥሎ
ለመምታት መሞከር ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ያልሆኑ ሰዎች ውጭ ሀገር ያላቸውን የስራ
ኃላፊነት ትተው በስብሰባው አንዲገኙ የተደረገውም ይሄን ለማሳካት አንደሆነ ግልጽ ነው።
ይሄ ህወሃታዊ አካሄድ በ 1993 ድርጅቱ ውስጥ መከፋፈል በተነሳ ወቅት በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ሥራ
አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተግባራዊ ተደርጎ እንደነበር ይታወቃል። የዘንድሮውንም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ
ኮሚቴ ስብሰባ በዚህ በተለመደ አካሄድ፣ ስብሰባውን ለረጅም ጊዜ አጓቶ ፣ ከኦህዴድም ሆነ ከብአዴን የተወሰኑ
አባላትን ወደሱ እንዲወግኑ ለማድረግ በመቻሉ ለጊዜውም ቢሆን መንደርተኛው የህወሃት ቡድን በኢህአዴግ ሥራ
አስፈጻሚ ኮሚቴ ላይ የበላይነቱን ሊያስቀጥል ችሏል። ከጉባኤው መጠናቀቅ በዃላ ባወጣው መግለጫው 'የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ካልሆነ በቀር በሌላ የማይተዳደሩበት ሁኔታ ፈጥሯል ።በዚህ የተነሳ ስርዓቱ ለበላይነትና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል ።በተግባርም እኩልነት እንጂ የበላይነትም ሆነ የበታችነት የማይፈጠርበት ስርዓት ተገንብቷል ።' እ ያለ ሊያጃጅለን ይሞክራል።
ህወሃት ራሱ በ1993 ክፍፍሉ ወቅት ሰለሞን ጢሞና ቢተው በላይ የተባሉ ከፍተኛ አመራሮቹን ፣ የኦህዴድና
የደህዴድ የበላይ ሃላፊ አድርጎ የሞግዚት አስተዳድር ያካሂድ አንደነበረ ያመነውና፣ በዚህም ንስሀ ገብቼበታለሁ
ብሎ የነበረ መሆኑን አንዘነጋም።
ከዚህ በተጨማሪና ዋናው ቁምነገር ፣ በተግባር ህወሃት በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊትና የደህንነት ተቋሞች ላይ
ያለውን ሙሉ ለሙሉ ሊባል የሚችል የበላይነት፣አስፈርሶ ህብረ ብሄራውነታችንን በሚያንጸባርቅ መልኩ
እንደገና እስካልተዋቀሩ ድረስ በወረቀት ላይ የሰፈረው እኩልነት ባዶ ምኞት ከመሆን አያልፍም።
አገሪቱን እመራለሁ የሚል አካል፣አገራችን ላይ ከተጋረጠው መጠነ ሰፊ ችግርና የህልውና አደጋ አንጻር፣
የችግሮቹን መንስኤ አንድ በአንድ ተመልክቶና ከሕዝብም ጋር መክሮ መፍትሄ ከመፈለግ ይቅር ፣ የአንድ
ጠባብ ቡድንን የበላይነት ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ በዚህ አይነት ሴራ መጠመድ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ብቻ
ሳይሆን፣ የአገራችንን ችግር የበለጠ የሚያቆላልፍና በሂደትም ብዙ ዕዳ የሚያስከፍለን ይሆናል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ በሚል በታህሳስ 21 ቀን የወጣው ጽሁፍ ለሽንገላ እንዲያመች
አንዳንድ ስህተቶችን የተቀበለ ፣ ለሰህተቶቹም ሃላፊነት በመውሰድ ይቅርታ እንደጠየቀ ቢያካትትም (ለየትኞቹ
ጥፋቶች ኃላፊነት አንደወሰደና ለየትኞቹ ይቅርታ እንደሚጠይቅ ግልጽ አይደለም)፣ ዋናው መልአክት ግን የህዝብ እንቅስቃሴ ጫና አሳድሮ መነቃቃት እንዲያሳዩ የገፋፋቸውን ኦህዴድና ብአዴን 'በጠንካራ ዲስፕሊንና የሃሳብና የተግባር አንድነት' በሚል ለማፈንና፣ ሀዝባዊ ተቃውሞውንና አንቅስቃሴዎችን ደግሞ፣ ሰላምና የህግ የበላይነት በሚል በወታደር ኃይል ለማፈን የወጣ ፍኖተ ካርታ ነው።

መግለጫው እርስ በርሱ የሚጣረስ ሀተታ ካቀረበ በዃላ ትኩረት ሰጥቼ እንቀሳቀስባቸዋለሁ ያላቸውን
አቅጣጫዎች በሚል ስምንት ነጥቦች አስፍሯልና እስቲ ትንሽ እንዳስሳቸው።
አቅጣጫ ቁጥር አንድ በሚል የሰፈረው በርካታ ነገሮችን በተደበላለቀ መንግድ በማቅረብ አድበስብሶ ለማለፍ
ከመሞከሩ ባሻገር ፣ በሀገሪቱ ሰላም በማስፈን ስም በተፈጠሩት አንዳንድ ጉድዮች ላይ (ለምሳሌ የጨለንቆው
እልቂት) በሃላፊነት ጭምር መጠየቅ የሚገባውን የመከላከያና ጸጥታ ሰራዊት በማሞካሸት ይቋጫል ።
በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተነሱ በርካታ ግጭቶች መንስኤ ምንድነው? ተጠያቂውስ ማነው? ላለፉት
26 አመታትና ከዛ ብዙ ቀደም ብሎ በነበሩ ዘመናት በአካባቢው በሚኖረው ሁለት ህዝብ መሃል ግጦሽንና
ሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮችን አስመልክቶ ግጭቶች ቢኖሩም፣ ለዝንት ዓለም በአካባቢው ሽማግሌዎች በተለመደው
ባህላዊ መንገድ የሚፈታ ነበር ። የዘንድሮው እንዲህ የከፋና ስፋት ያለው ሊሆን እንዴት ቻለ?የብዙ መቶ ዜጎች
ሞትና ከ 900000 በላይ ሕዝብ መፈናቀል፣ የአንድ ጀንበር ክስተት ሳይሆን ጊዜ የፈጀና የተቀናጀ ተግባር
በመሆኑ፣ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ መጠን ታይቶ የማይታወቅ ህዝብን ከቀዬው የማፈናቀል አስከፊ የጅምላ
ወንጀል ሲካሄድ መሃከላዊው መንግስት የት ነበር? ችግሩ እንዳይባባስስ ምን እርምጃ ወሰደ?ችግሩንስ
የፈጠረውና ተጠያቂውስ ማነው?… ወዘተ የሚሉና በርካታ መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ሆነው ሳለ ፣ ባንዳንድ
ስፍራ ከሚካሄዱ የህዝብ እንቢተኝነቶችና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሰዎች ጋር ደምሮ አድበስብሶ ለማለፍ
መሞከሩ፣ ከስልጣኑ ውጭ የህዝብ መፈናቀል ስቃይና እንግልት ብዙ እንደማያስጨንቀው አመላካች ነው።
አቅጣጫ ቁጥር ሁለት ስለ ሁሉም ድርጅቶች የሚያወራ ቢመስልም፣ ህወሃት 38 ቀን የፈጀ ስብሰባ አካሂጄ
ጣጣዬን ጨርሼ መጥቻለሁ ባይ ስለሆነና ስለ ደህዴድ ይህ ነው የሚባል ፍንጭ እስካሁን ባለመኖሩ ፣ ኦህዴድና
ብአዴን 'የማስተካከያና የአርምት አርምጃ እንዲወስድ ተውስኗል ' በሚል ልንተረጉመው እንችላለን።
አቅጣጫ ሶስት ስርአቱ ድህነትን ለመቅረፍ የወሰዳቸውን አርምጃ አስመልክቶ ረጅም ርቀት እንደሄደና በዚህም
ራሱን ለማመስገን ቢጥርም ፣ በመሬት ላይ ያለው ሃቅ ሊካድ የሚቻል ባለመሆኑ ግማሽ አውነት ማለትም 'ሩብ የሚጠጋው ህዝባችን ከድህነት ወለል በታች መገኘቱ' (ዓለም ባንክ የዛሬ ሁለት ዓመት ባወጣው ሪፖርት 29.6% ከድህነት ወለል በታች፣ 30.7% የሚሆነው ህዝባችን ደግሞ በዓለም አቀፍ መስፈርት የድሃም ድሃ የሚባለው ውስጥ ይካተታል ነው የሚለው!)እጅግ አሳሳቢ ነው በሚልና ጠንካራ ትግል እንደሚያስፈልግ ይናገራል።ለሁለት አስርት አመታት የሁለት አሃዝ እድገት ያመጣ ኢኮኖሚ እንዴት ይሄን መቅረፍ እንዳልቻለ እንቆቅልሽ ቢሆንም፣ በቀጣይ ግን ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ሃላፊነቱን ወደ ክልላዊ መንግስታት ያዞረ ይመስላል።በተግባር ምን ያህል ክልሎቹ ያለ ፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነት ይሄን ሊያካሂዱ ይችላሉ የሚለው በሂደት የሚታይ ይሆናል።
አቅጣጫ አራት ስለ አስተዳደራዊ ቅልጥፍና ሲሆን መሻሻል ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ይገባል።
በሙያዊ ብቃትና መልካም ስነምግባር ባላቸው ሰዎች ሳይሆን፣ ሃላፊነት በማይሰማቸውና በሙስና በናወዙ
ታማኝ ካድሬዎች የተሰገሰገው ቢሮክራሲ ይሄን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል የሚለው በሂደት የሚታይ ይሆናል።
አቅጣጫ አምስት 'በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛ ሚስጥር የህዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ነው'የሚል ልግጫ ቢኖርም፣ ለወደፊት 'የህዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንድሚገባ ተወስኗል' ይለናል። ወጣቶችን አስመልክቶ እንደከዚህ ቀደሙ 'አነስተኛና ጥቃቅን ' በሚል ለማማለልና ለማዘናጋት ተግባራዊ አንቅስቃሴ ሊያደርግ አንዳሰበም ያመለክታል። ከሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት አንጻር የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘውን የወጣት ትውልድ የፍትህ የዴሞክራሲና የአስተማማኝ የኑሮ ሁኔታ ጥያቄዎች 'ያጉል ተስፋና ባዶ ቃልኪዳን' ባለቤት የሆነው ኢህአዴግ ያሟላል የሚል ተስፋ ለመሰነቅ አስቸጋሪ ነው ።
አቅጣጫ ስድስት ስለ መድበለ ፓርቲ ግንባታንና የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎን አስመልክቶ ያሉ ጉድለቶችን
ስለማረም፣ ምህዳሩን ስለማስፋትና ምቹ ሁኔታ ስለ መፍጠር ቢጠቅስም ፣ ተግባራዊ አርምጃ በመውሰድ ፣
ማለትም ያለአግባብ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችንና መሪዎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ፣የፖለቲካ

ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ባለመገደብና ሲቪክ ማህበራትን አስመልክቶ ደግሞ አላሰራ ያሉትን አፋኝ ሕጎችን
በመሻር እስካልታጀበ ድረስ ባዶ ፉከራ ሆኖ ይቀራል።
ጠ/ሚ ሀይለማርያም ትላንትና ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነመናብርት ጋር በመሆን በሰጠው
ጋዜጣው መግለጫ፣ ብዙዎች ባልጠበቁት፣ ሆኖም መታሰራቸው ግን ፍትሃዊ እንዳልሆነ ማንም የሚያውቃቸው
አንዳንድ የፖለቲካ አመራር አባላትና ሌሎች ግለሰቦች ክሳቸው ተቋርጦ ወይንም በይቅርታ ከእስር ሊፈቱ
እንደሚችሉና፣ መንግስትም ይሄንን እርምጃ የሚወስደው፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት በቅርቡ ባገባደደው
የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ መግባባት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች እንደ አንዱ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። ፍችው
ማንን እንደሚመለከት ፣ምን ያህል ሰዎች እንድሚያካትትና መቼ እንደሚሆን ፍንጭ ባለመስጠቱ ፣ እንዲሁ
መልካም ጅማሮ ነው ከማለት ውጭ ብዙ ማለት አይቻልም።
ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ምኒስትሩ 'ደርግ ይጠቅምበት የነበረውን' ማእከላዊ (ላለፉት 26 ዓመታት የኢህአዴግ የስቃይ መአከል አንደነበር ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የዓለም የመብት ተሟጋች ድርጅቶችና መንግስታት በሚገባ የሚያውቁትን! ) አፍርሰን ወደ ሙዚየምነት በመለወጥ ሌላ የዘመነ እስር ቤት እንገነባለን ብሎ ቃል ገብቷል።
የዛሬ አስራ ስምንት ወር አዲስ ስታንዳርድ የተባለው መጽሄት 'ማአከላዊ' የተስኘው የስቃይ ጉሮኖ ለምን እስካሁን ስራውን እንደቀጠለና፣ መፍረስ ግን አንዳለበት ሞግቶ ጽፎ የነበረ እንደነበር የሚታወስ ነው። ውሳኔው26 ዓመት የዘገየ ቢሆንም፣ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስም የነበረው ገፊ ምክንያት ምንም ሆነ ምንም ግን ኢህአዴግ ለማፍረስ መወሰኑ አበረታች ነው። አቅጣጫ ሰባት የህዝብን ሰብዓዊና ዴሞክራቲክ መብቶች በዋናነት ደፍጣጩ ኢህአዴግ መሆኑ እየታወቀ፣ በአስተማማኝ ደረጃ ስለማስከበር አቅጣጫ አስቀምጧል የሚለው ክፉ ቀልድ ነውና ስለሱ ብዙ ማለትምአስፈላጊ አይደለም።
አቅጣጫ ስምንት በመሰረቱ የኦሮሚያ ክልልና የአማራ ክልል የዜና አውታሮችና የቴሌቪዥን ፕሮግራም
ጥንቅሮች ፣ ሌሎች የመንግስት የዜና አውታሮች ከሚያስተጋቡት ለየት ያለና አንዳንዴም ሕዝብ የሚያሰማቸውን
ብሶቶችና የህዝብ ጥያቄዎች ማስተናገዳቸው ያልተመቸው የህወሓት ቡድን በተደጋጋሚ ጫና ለማሳረፍ
አንደሞከረና እንዳልተሳካለት የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁን በኢህአዴግ ስም መስመር እንድያስተካከሉ መወሰኑን
የሚያበስር ነው።

እስካሁንም ግልጽ ካልሆነላቸው የኢህአዴግ መሪዎች ሊገነዘቡት የሚያስፈልገው አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ
በኢህአዴግ ስርዓት እንደተማረርና ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እንደሆነበትና ፣ከእንግዲህ ወዲህ ባዶ ተስፋ፣
ሽንገላም እንደማያማልለው፣ እስርና ግድያም እንደማይገድበው ነው። እርግጥ ነው የተናጠልና ያልተደራጀ ትግል
ውጤቱ ውሱን መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ወጣቱ ትውልድ አስፈላጊነቱን በመገንዘብ ወደዛ አቅጣጫ እየተግዋዘ
እንድሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ ነው።የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ጥረቶች ፍሬ አፍርተውና ሕዝቡን
ከጀርባቸው አድርገው ፍትህ የሰፈነባትና የዴሞክራሲ መብቶች እውን የሚሆንባት ኢትዮጵያን እንደሚገነቡ
አንዳችም ጥርጥር ሊገባን አይገባም። የተባበረና የተደራጀ ህዝብ ምንጊዜም አሸናፊ ነው!
አበጋዝ ወንድሙ

Filed in: Amharic