>

ህወሃትን ለማዳን ገደል ከምትገቡ እሱን ግደሉት እና ንስሀ ግቡ! (ስዩም ተሾመ)

ከ1993ቱ የህወሃት መከፋፈል በኋላ አቶ #መለስ_ዜናዊ መላ-ቅጡ ጠፍቷቸው ነበር፡፡ ከዚያ ከአቶ በረከት ስምዖን ጋር #ዝጉብኝ ክፍል ገብተው  “ምን ይሻለናል? እንዴት ከዚህ ጉድ መውጣት ይቻለናል?” በማለት መከሩ፡፡ አቶ በረከት’ሻ  “ድርጅታችን ኢህአዴግ ሀገሪቱን የመምራት ስልጣኑን በህዝብ ፍቃድና ምርጫ ላይ የተመሠረተ ማድረግ አለበት” የሚል ምክር ሰጡ፡፡ አቶ መለስም ” ዳይ… በረከት የተግባር ዕቅዱን አዘጋጅ” አሉና ከዝጉብኝ ክፍል ወጡ፡፡ አቶ በረከት እዚያው ቆዩና የ1997ቱን ምርጫ ዕቅድ አዘጋጁ፡፡ ምርጫው እየቀረበ ሲሄድ በረከትና መለስ አፍንጫቸውን አላባቸው፡፡ የምርጫው ዕለት የኢትዮጲያ ህዝብ በአፍ-ጢማቸው ደፋቸው፡፡ የምርጫው እለት ማታ ከተደፉበት ተነስተው የምርጫ ኮሮጆ ሲገለብጡ አደሩ፡፡ ሁለቱ መላጣዎች በፈጣጣው ምርጫውን አጭበረበሩ፡፡ የኢትዮጲያ አምላክ ነገረ-ስራቸውን ተመለከተና የሁለቱንም ጤና አንጨበረረው፡፡ በረከትም ተንጨብርሮ በሼሁ (ምፅ) እርዳት ደ/አፍሪካ ሄዶ ታክሞ ዳነ፡፡ መለስ ዜናዊ ሊታከም በሄደበት ደየመ (“ሙት ወቃሽ” መሆን ጥሩ አይደለም)፡፡ ድርጅታቸው #ኢህአዴግ ደግሞ እንዳይሞት-እንዳይድን ሆኖ ታመመ፡፡ ግማሹ ኢህአዴግ እንደ አቶ በረከት “የአዕምሮ መታወክ ነው” ይላል፡፡ ሌላው አይ እንደ አቶ መለስ “በበታችነትና እብሪት የተሞላ የፍርሃት ደዌ ተጠናውቶት ነው” ይላል፡፡ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ እንደ እብድ የሚያደርገውን ነገር አያውቅም ነበር፡፡ በመጀሪያ በ2001 ዓ.ም “ፀረ-ሽብር” የተባለ የፍርሃት መድሃኒት #ከአሜሪካ አስልኮ አስገዛና እሱን መውሰድ ጀመረ፡፡ ይህ መድሃኒት በቀጣዩ አመት 2002 99.6% አይንና ጆሮው ተደፈነ፡፡ የተለየ ሃሳብና አስተያየት በሰማ ቁጥር ድንጋይ እያነሳ መወርወር ጀመረ፡፡ በዚያ ላይ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ፥ የሚዲያ አዋጅ፥ የበጎ አድራጎት ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ፥ …ወዘተ የሚባሉ መድሃኒቶች ሰወስድ በሽታው እየባሰበት ሄደ፡፡ በመጨረሻ በ2007 100% መስማትና ማየት ተሳነው!! ይሄው ከዚያ በኋላ የእውር-ድንብሩን ይሄዳል፡፡ ይሄዳል አያይም፣ ቢጠሩት አይሰማም፡፡ ብቻውን ይሄዳል፣ ማንም አብሮት የለም፡፡ ብቻውን ያወራል ማንም አይሰማውም፡፡ በ2008 #ቄሮ የሚባል “የባህል መድሃኒት” አዋቂ ተጠርቶ መጣና #ኦህዴድ የሚባለው የኢህአዴግ ክፍል ጆሮውን ቆረጠው፣  የአይን ግርዶሹን ያለማደንዘዥ በስለት ገፈፈው፡፡ የኦህዴድ አይንና ጆሮ ሲከፈት #የብአዴን አይን ጭላንጭል ማየት ጀመረ፡፡ የህወሃትና ደህዴን አይን ታውሮ እና ጆሮ ደንቁሮ ደንቆሮ ቀረ፡፡ እና እንዳልኳችሁ ኦህዴድ የአይን ሞራው በጩቤ ሲገፈፍለት ከገደል አፋፍ ላይ እንደ መንጠልጠሉን  ተመለከተ፡፡ የህዝቡ ጩኸት ጆሮ ያደነቁራል፡፡ ከዚያ ጅብ እንዳየ አህያ ሽምጥ ጋለበ፡፡ ብአዴን ኦህዴድን ተከትሎ መጋለብ ጀመረ፡፡ ህወሃትና ዴህዴን ግን በነበሩበት የገደል አፋፍ ፈፍ ላይ ተንጠልጠለዋል፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ከገደሉ አፋፍ ለመራቅ እያናፉ ሲገልቡ ከህወሃት ጋር የተሳሰሩበት “እትብት” ጠልፎ ጣላቸው፡፡ አሁን ያላቸው አማራጭ ሁለት ነው፦ ከህወሃት ጋር ያላቸውን እትብት በጥሶ መጣል ወይም ከህወሃት ጋር ተያይዞ ከገደል መግባት፡፡ ህወሃትና ደኢዴን እንደው ቢጠሯቸው አይሰሙም፣ ቢወጏቸው አያዩም፤ ቢስቧቸው አይመጡም፣ ቢለቋቸው ገደል ከመግባት አይድኑም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድና ብአዴን ያላቸው አማራጭ ህወሃትን ገድሎ መዳን ወይም እሱን ለማድን አጉል ሲታትሩ አብሮ መውደቅ! እንደ እኔ “የማይድን በሽተኛ ለማዳን ከመሞት እሱን ገድሎ ንሰሃ መግባት!” ይሻላል፡፡ ስለዚህ #ኦህዴድና_ብአዴን ህወሃትን ለማዳን ገደል ከምትገቡ እሱን ግደሉትና ንሰሃ ግቡ!

Filed in: Amharic