>

ግልጽ ደብዳቤ፦ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

ጉዳዩ፦ በቂሊንጦ እሳት ሰበብ ስለታሰሩት ሰዎች የተደረገውን ምርመራ በተመለከተ

እንደሚታወቀው ኢሰመኮ በቀን 20 ጥቅምት 2010፣ በደብዳቤ ቁጥር ሰመኮ/2.1/29/2010 እንደገለጸው ነሐሴ 1/2008 አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (ቂሊንጦ) ግቢ ውስጥ የተነሳውን እሳት መንስዔ ለማጣራት በተደረገው ምርመራ አሰቃቂ የመብቶች ጥሰቶች ተፈፅመዋል። በእነ መቶ ዐለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ (38 ተከሳሾችን) በተመለከተ መንግሥት ባለበት አገር ይፈፀማሉ ተብለው የማይጠበቁ የጥፍር መንቀል፣ በሚስማር ሰውነት የመብሳት፣ ግርፋት እና የመሳሰሉት አካላዊ ጉዳት የሚያደርሱ፣ ሰብኣዊ ክብርን የሚያዋርዱ የጭካኔ ተግባራት በተያዙ ሰዎች ላይ ተፈፅሞባቸዋል። ይሄ ሁሉ የሆነው ፍርድ ቤት በአደራ እንዲጠብቃቸው ያስረከበው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ነው። ሆኖም፣ ዋነኞቹ የምርመራው (ወይም በትክክለኛ አገላለጽ የማሰቃየት ተግባሩ) በፖሊሶች የተፈፀመ መሆኑን ታራሚዎቹ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከላይ በጠቀስኩት ሪፖርቱ ያካተተው በተለይ በአንድ መዝገብ ከተከሰሱት 38 ሰዎች ውስጥ የ16ቱን ብቻ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተከሳሾቹ በጻፉት አንድ ደብዳቤ ላይ የኮሚሽኑ ሪፖርት «1ኛ) የተፈፀመብንን ኢሰብአዊ ድርጊት ሙሉ ለሙሉ አላካተተም፣ 2ኛ) የማሰቃየት ተግባር የፈፀሙብንን አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ፈንታ የተለሳለሰ ‘ምክረ ሐሳብ’ ማስቀመጡ አግባብ አይደለም፣ 3ኛ) የደረሰብንን የማሰቃየት ተግባር የፈፀሙብን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሕክምና ቡድን አባላት እንዲያጣሩ ማዘዙ ‘ኢሰመኮ መልሶ አሳልፎ ለነሱ ሰጥቶናል’ በሚል ቅር እንድንሰኝ አድርጎናል» በማለት ቅሬታዎቻቸውን ከገለጹ በኋላ፣ ሪፖርቱ በምርመራ ወቅት በግዳጅ እንዲያምኑ የተደረጉትን የሐሰት ውንጀላ ለመከላከል ስለሚረዳቸው ኮሚሽኑን አመስግነዋል። በተጨማሪም፣ ተከሳሾቹ ታኅሣሥ 6፣ 2010 ሪፖርቱን በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ወቅት በኮሚሽኑ እምነት በማጣት እና “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላደረሱባቸው ሰዎች መረጃውን የሚሰጡባቸው ስለመሰላቸው” የደረሰባቸውን ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሳይናገሩ የቀሩ ተከሳሾች እንዳሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም በክስ መዝገባቸው ላይ የከሳሽ፣ ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሆነው እየቀረቡ ያሉት ራሳቸው እስረኞች መሆናቸውን ገልጸው “እነርሱም ሊመሰክሩብን የተስማሙት በድብደባ ብዛት ነው እና የመብቶች ጥሰት ማጣራት ምርመራው እነሱንም መጨመር አለበት” የሚል ጠቃሚ ምክር ሰጥተዋል። ኮሚሽኑ ገጽታውን ለማስተካከልም፣ ሕጋዊ ኃላፊነቱንም ለመወጣት ሲል ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በእርግጥ ይህንን ዓይነቱን የምርመራ ሪፖርት ማዘጋጀት የኮሚሽኑ ሥራ ቢሆንም፣ ሕዝባዊ አመኔታን ካጣው ኢሰመኮ ያልተለመደ ውጤት በመሆኑ በዚህ የተሻለ ሪፖርቱ እኔም መደሰቴን እገልጻለሁ። ይሁን እንጂ፣ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ የጻፍኩት፣ ሪፖርቱ ውስጥ የተጓደሉት የመብት ጥሰቶች ተሟልተው፣ አስቸኳይ ፍትሐዊ እርምጃ ለእነዚህ መብቶቻቸው እና ሰብአዊ ክብሮቻቸው የተገፈፉ ዜጎች እንዲሰጥ ግፊት በማድረግ ኮሚሽኑ ሕዝባዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወ:ጣ ጥሪ ለማድረግ ነው።

ኢሰመኮ መጋቢት 27 ቀን 2009 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቃጠሎውን መንስዔ እና ጉዳት አብራርቷል። በዚህ ወቅት የቃጠሎው ዋነኛ መነሻ ከቃጠሎው አንደ ቀን በፊት የቤተሰብ ምግብ እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ የተከሰተው አድማ እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ በዕለቱ የቀረበው ሪፖርት እንደሚለው ለአድማው ቀድመው ሲዘጋጁ የነበሩ ሰዎች አሉ። ኮሚሽኑ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች እና በቃጠሎው ወቅት የነበሩ የጥበቃ አባላትን በመጠየቅ ነው። ይሄ ጉዳይ ኃላፊዎቹ እና የፀጥታ ኃይሉ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ላለመሆን የሚሰጡት ሰበብ አስባብ መሆኑን መረዳት ቀላል ነው። ኮሚሽኑ እንዳረጋገጠው በወቅቱ ምንም መሣሪያ ባልያዙ ታራሚዎች ላይ የጥበቃ አባላት ከውጭ ወደ ውስጥ መተኮሳቸው ተገልጿል። በዚህም በሕግ መጠየቅ ያለባቸው አካላት እንዳሉ በኮሚሽኑ ቢገለጽም እስረኞቹ የሁሉንም ዕዳ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።

በቃጠሎው ጉዳይ ከ150 እስረኞች በላይ መታሰራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ እኔ በተለይ የምከታተለው በሽብር የተከሰሱትን 38 እስረኞች ጉዳይ ነው። የእነርሱ ክስ የሚለው ከቃጠሎው ወራት በፊት አድማውን ለሽብር ተግባር አቅደውታል ቢሆንም በቂ ማስረጃ እስካሁን አልቀረበም። ተከሳሾቹ የቂም በቀል መወጫ እና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊነታቸውን አለመወጣት ለመሸፈን ሲባል ሰለባ እየሆኑ ነው ያሉት። ከነዚህ ውስጥ ቢያንስ ሦስቱ (ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ አግባው ሰጠኝ እና ሚስባሕ ከድር) ከቀድሞው ክሳቸው ነጻ በመውጣታቸው መፈታት ነበረባቸው። እነዚህ ሰዎች በነጻ በመፈታታቸው በፊት የተጠረጠሩበትን ነገር አልሠሩም ማለት ነው። ስለዚህ አግባብ ባልነበረው ክሳቸው ምክንያት ባይታሰሩ ኖሮ ለዚህ ክስ አይዳረጉም ነበር። ከነርሱም በተጨማሪ፣ ሌሎችም የቀድሞ ክሳቸውን ፍርድ ታስረው በመጨረሳቸው አባሪዎቻቸው ተፈትተው ከቤተሰባቸው ሲቀላቀሉ ያልተፈቱ ተጠርጣሪዎችም አሉ።

ስለሆነም፣ ኢሰመኮ የነዚህን ተከሳሾች ኢፍትሐዊ አያያዛቸውን፣ የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመረዳት የሚከተሉትን እርምጃዎች እንዲወስድ በአንድ የዜጋ ድምፄ እጠይቃለሁ፦

1ኛ፣ ተጨማሪ የመብቶች ጥሰት ምርመራ በጉዳተኞቹ ላይ እና በእነሱ ላይ እንዲመሰክሩ በተደረጉት እስረኞች ላይ እንዲደረግና ለሕዝብ እንዲገለጽ፣

2ኛ፣ በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥይት የተኮሱ የጥበቃ አባላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ የተገኘውን የምርመራ ማስረጃ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲያደርስ እና ጉዳዩ ፍትሕ እንዲያገኝ ግፊት እንዲደረግ፣

3ኛ፣ በምርመራ ወቅት ተከሳሾች ላይ የማሰቃየት ተግባር የፈፀሙ የመንግሥት አካላትን በአስቸኳይ አጣርቶ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማቅረብ በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ፣

4ኛ፣ ትክክለኛው የቃጠሎው መንስዔ የማረሚያ ቤቶቹ ብልሹ አስተዳደር ያስቆጣው የእስረኛ አያያዝ ስለሆነ ክሱ ተቋርጦ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ኮሚሽኑ ግፊት እንዲያደርግ እጠይቃለሁ።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በፖሊስ ምርመራ ወቅት እና በየማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ የሚደርሱ የመብቶችን መተላለፍ እና የማሰቃየት ተግባሮችን ለማስቆም እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ይህንን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ እና ትኩረት እንዲከታተለው እጠይቃለሁ። ይህንን በማድረግ ኢሰመኮ ከሕዝብ ያጣውን አመኔታ ከመመለስም ባሻገር፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት ይችላል።

ከሠላምታ ጋር
በፍቃዱ ኃይሉ
ከሕግ አክባሪ ዜጎች አንዱ

Filed in: Amharic