>

የለማ መገርሳና የገዱ ካቢኔ እጣ ፈንታ (ሀብታሙ አያሌው)

የለማ መገርሳና የገዱ አንዳርጋቸው ካቢኔ ወደ ህወሓት ማጀት አዘንብሎ በስልጣን መቋደስ ስምምነት  ኢህአዴግ የሚባል ዘባተሎ ግንባር በጋራ እናስቀጥላለን፤ የህዝቡ ትግልም በዚህ ይዳፈናል የሚል ቅዠት ውስጥ ከገቡ አብዝተን እናዝንላቸዋለን።

ሞት እማይፈሩ ወጣቶች የአጋዚን ጥይት ለመቀበል ደረትና ግንባር የሰጡት ኦህዴድና ብአዴን ስልጣን አንሷቸዋል ይካፈሉ ብለው እንዳልሆነ ይጥፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። የነበረውና የቀጠለው ትግል እና መስዋዕትነት
(Down Down Weyane) የወያኔ አገዛዝ በቃን፤ የታሰሩ ጀገኖቻችን ይፈቱ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ መድረክ ይጠራ ወንጀለኞቾ ለፍርድ ይቅረቡ፤  ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ይቋቋም፤  ህዝብ የራሱን መንግስት ይምረጥ። የማያሻማ ግልፅ ጥያቄ ነው፤ የስርዓት ለውጥ። አራት ነጥብ

ይህ የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ‘ጠያቂው ህዝብ አይገደል ወንጀል አልሰራም አይታሰር፤ እስከዛሬ የተሰበከው የዘረኝነት ስብከት ተገቢ አይደለም፤ ቋንቋ ባህል የማይለየን የተጋመድን የተደመርን የተዋሃድን አንዳችን በአንዳችን ላይ የተሰራን የአንድ አካል ስሪቶች ታሪካዊት አገር በአንድ የገነባን የነፃነት ምልክቶች ነን። ‘  ወደሚለው ከፍታ ለመምጣት የህወሓትን የዘረኝነት ካብ በመናድ እረገድ የተጫወቱት ሚና በርግጥ ሲያስመሰግናቸው ይኖራል።

ይሄ ጅምራቸው ቀጣዩን ፈተና ካለፈና ከህዝብ ጎን ተሰልፈው ከቀጠሉ ስማቸውን ታሪክ ከሚዘክራቸው ከኢቲዮጵያ ጀግኖች ተርታ በወርቅ ቀለም ለማፃፍ ይበቃሉ። ጉልበታቸው ዝሎ እንደ እርያ (አሳማ) ታጥበው ወደ ጭቃው ከተመለሱ በነሱ መመለስ የሚቀለበስ ትግል እንደሌለ በሚገባ ሊገነዘቡ ይገባል።  ወትሮም ትግሉ በነሱ አልተጀመረም በነሱም አይቀለበስም፤ ይልቁንስ  ጨቋኙን ህወሓትን  ለመለብለብ ወደ ነደደው የህዝብ ነበልባል ተጠግተው ለአመታት ከተመሸጉበት የሎሌነት ምግባር ለመላቀቅ ያገኙትን ጉልበት ይሄን ቅዱስ እድል በከንቱ አምክነው ፊታቸውን ወደ ህወሓት ከመለሱ ጉልበት የሆነቸውን ህዝብ ካጡ ይብላኝ ለነሱ።

ህወሓት እንደምንም ከህዝብ ነጥሎ ለብቻ ካቆማቸው በእውነቱ ፍፃሜያቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ይሆናል። ወደ ትግሉ ሲመጡ በእልልታ የተቀበላቸው ህዝብ ፊታቸውን ወደ ህወሓት ከመለሱ ባንዳን አይቀጡ ቅጣት መቅጣቱ ልማዱ ነውና ከወንበዴው ጋር ደምሮ እንደሚያሳድዳቸው ግልፅ ነው። ከሁለት ያጡ ስለሚሆኑ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ይበላቸዋል።  የህወሓት ጉጅሌ ኢህአዴግ በሚል ስም (ጭምብል)  በያዘው ግምገማ የለማ መገርሳንና የገዱ አንዳርጋቸውን  ካቢኔ ካምበረከከ ትግሉ አለቀለት የሚሉ አንዳንድ ገማቾች የትግሉ ባቡር የቱ ጋር እንዳሳፈራቸው ባግባቡ ያልተረዱ እንደሆኑ ይሰማኛል። እነ ለማ መገርሳ የተሳፈሩት መንገድ ላይ ነው እስከመጨረሻው ከተሳፈሩ ያተርፋሉ፤  በርግጥም ባቡሩንም (ትግሉንም ) ለማፍጠን ይረዳሉ።  በአሻፈረኝ ወይም በህወሓት አሳሳችነት  ያለፌርማታቸው ከወረዱ አስቀድሞ እነሱን የሚድጠው የባቡሩ ጎማ ፍጥነቱ ላይ ለውጥ ከማምጣት በቀር ፈፅሞ እንደማያቆመው መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል።

Filed in: Amharic