>

የኦቦ ለማ፣ የኦሮሞ ህዝብና ልሂቃን ንቃት (ከጎሰኝነት ወደ አንድነት) [መሐመድ ነስሩ (ሶፎኒያስ አቢስ)]

ኦቦ ለማ መገርሳ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ውስጥ በመንግስት ወታደሮች ለተገደሉ ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡ የክልሉ መስተዳደር የወታደርን ጣልቃ ገብነት እንዳልጠየቀና ግድያውን የፈፀሙ አካላትም ለህግ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡
የኦቦ ለማ ንግግሮች፤ የኢህአዴግን የበርካታ ዓመታት፣ አካሄድና አቋም ለምናውቅ ሰዎች፣በእጅጉ  አስገራሚ እየሆነ ነው፡፡ ሰውየው ከኢህአዴግ አመለካከት ባፈነገጠ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን እየዘመሩ ይገኛሉ፡፡ ለማ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለበርካታ ዓመታት ተቆጣጥሮ፣ እንደ እንኩሮ እያነከረን ያለው የ1960ዎቹ ትውልድ አባል እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢህአዴግን ፖሊሲ ከማስፈፀም ወደ ኋላ ብለው የማያውቁ ቢሆኑም፣ አሁን እያሳዩ ያሉት ሁኔታና ንግግሮቻቸው፣ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ቀልብ ሊይዝና ልቡን ሊማርክ ችሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከኢህአዴግ የጥላቻ ፖለቲካ የጸዱ ናቸው ብሎ መደምደም መቸኮል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን እየታየ ያለው ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
የአቶ ለማ ንግግር ብዙዎችን ሊስብ የቻለውና በባህርዳር እንደታየው የጭብጨባ ጎርፍ የተከተላቸው እንዲሁም በሰመራ እንደሆነው፣ በርካቶች ከእሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሳት (እንደ ሰለብርቲ) እስከ መራኮት የደረሱት ህዝቡ “ጀግና” አድርጎ እያያቸው በመሆኑ ይመስላል፡፡ የሰውዬውን ድንገተኛና ያልተገመተ ተቀባይነት ማግኘት ለመረዳት፣ ይሄ አንድ ጠቋሚ ምልክት ነው፡፡
ይህ ኢትዮጵያን የማሞጋገስና “አብረን የኖርን ብቻ ሳንሆን፣ አብረን የሞትን ነን” የሚለው የለማ ንግግር፤ በእርግጥም ከኢህአዴግ አመለካከት ያፈነገጠ ነው፡፡ ይሄ በህወሓት እንደሚዘወር በሚነገርለት የኢህአዴግ ቤት ያልተለመደ፣ አዲስ ክስተት ነው፡፡
ከዓመታት በፊት፣ በአንድ ወቅት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዋና ከተማ ሀዋሳ፤ አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ የፓርቲያቸውን አዲስ አበቤዎችን በብሔር የማደራጀት ሃሳብ ተቃውመው (ኢህአዴግን የተቃወመ ብቸኛው የኢህአዴግ አባል ሆነው) ካሰሙት ተቃውሞ ውጪ በኢህዴግ ባህል መቃወምም ማፈንገጥም ያልተለመደ ነው፤ እንግዳ የሆ ነገር፡፡ የኦህዴድ እንዲህ መነቃቃት ህወሓትን ሊያስደነብረው አይችልም ወይ? ብለን ብንጠይቅ፤ መልሱ ይችላልም፤ አይችልምም የሚል ይሆናል፡፡ የመጀመሪያውን ላስቀድም፤ … ህወሓት ሊደነብር የሚችለው ሰውየው ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥራቸው ውጪ ከሆኑና ፈፅሞ አልታዘዝም የሚል የነጠረ አቋም ላይ ከደረሱ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ህወሓት የለማን አካሄድ የፈራው ወይም አካሄዱ ያሰጋው ለመሆኑ የታየ ፍንጭ የለም፡፡ ወይስ ህወሓትም ተለውጦ ይሆን? (መቼም አያርመንም!) ወይስ ደግሞ ለፖለቲካ ዓላማ ብቻም ቢሆን አካሄዱ ተመችቷቸዋል ብለን እንውሰድ? ወይስ …?
…. እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ህወሓትም ለዝቧል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህን ያልኩት ፓርቲው በጫካም ሆነ በስልጣን ዘመኑ፣ ልዩነቶችን ሲታገስና እንዳላየ ሆኖ ሲያልፍ፣ ታይቶ አያውቅምና ነው፡፡ ነገሩን በሌላ አቅጣጫ እንየው ከተባለ ደግሞ ህወሓት የለማን ንግግር ጊዜ እንደ መግዣና የሰውን ልቦና መቆጣጠሪያ አድርጎ እያየው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ተመችቶታል፡፡ ስለዚህ ደስ ብሎታል፤ ስለዚህ ይደግፈዋል፡፡
አንድ ስጋት ግን አለ፡፡ ሙስናን አጥብቆ ይጠላ የነበረው፣ በኦሮሚያ አስተዳደር ውስጥ ተገጥግጠው የነበሩ ብዙ ሙሰኞችን በገፍ ያሰረውና ከዓመታት በፊት ተመርዞ የሞተው የቀድሞው የኦሮሚያ መስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ የደረሰበት፣ ለማ ላይ ስላለመድረሱ እርግጠኛ መሆን የምንችል አይመስልም፡፡ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጥቅማቸው የሚነካ ከሆነ፣ ምንም ምርጥ አሳብ ብታራምድና መልካም ሰው ብትሆንም አይምሩህም፡፡ እና ይህን ብንጠረጥር “ሟርተኛ!” አያሰኘንም፡፡ የለማ አቋም እውነተኛ ከሆነና፣ ይህን እምነቱን ማራመድ ከቀጠለ ማለቴ ነው፡፡
የለማን አካሄድና ንግግሮች በጥርጣሬ ዓይን የሚያዩ ሰዎችና “ውስጣቸው ያው ኢህአዴግና የህውሓት ሎሌነት አለ” የሚሉ ፅሑፎች ገጥመውኛል፡፡ የሰውዬውን ዝንባሌ አይቶ አጀንዳ የመቀማት አካሄድ እንጂ ለውጡ እውነተኛ ለውጥ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች “ልክ አይደሉም” ወይም “ተሳስተዋል” ብሎ መፍረድ ከባድ ነው፡፡ ሊሆን የማይችልበት አጋጣሚ እንዳለ ለመከራከር ትንሽ ጊዜ መስጠት ይፈልጋል፡፡
ሆኖም መጥፎ መጥፎውን (negative) እያሰብን፣ ፀለምተኛ (Pessimist) ከምንሆን፣ በጎ በጎውን (Positive) እያሰብን፣ብሩህ ተስፈኛ (Optimist) ብንሆን ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፀለምተኝነት የሚያሸክመን የነፍስ ህመም ሲሆን ቀና አሳቢነት የሚያጭርብን ተስፋን ነው፡፡ መቼም ከህመም ተስፋ እንደሚሻል ከማንም  የተሰወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ በኦቦ ለማም ሆነ በሀገራችን ተስፋ ብናሳድር በተሻለ ሁኔታ ብዙ ርቀት የመጓዝ አቅም እንጎናፀፋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ የሰውየውን ንግግሮች  የማየው በመልካምነታቸው ነው። ልባቸው ምንም ይሁን ምን፣ ከኢህአዴግ አመራሮች መሀል እንደዚህ አይነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለምስና ኢትዮጵያን የሚያወድስ ንግግር መስማት መቻል በራሱ አንድ በጎ ነገር ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ስሜትም ይፈጥራል፡፡
እና ግድየላችሁም ሰውየውን በመልካም ዐይን እንያቸው ስል እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች ይህን ሲያደርጉ አልተመለከትንምና፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ ታሪካችንና ፖለቲካችን ባሳደረብን ተፅዕኖና ስነ – ልቦናዊ ጫና የተነሳ ሲበዛ ተጠራጣሪዎች ነን፡፡ ስለዚህ ኦቦ ለማ ላይ ብሩህ ተስፋ በማሳደር፣ ይህን ክፉ አባዜ መላቀቅ  ይኖርብናል፡፡
በመቀጠል የሰውየውን አቋም፣ከጠቅላላው የኦሮሞና ኦሮሚያ ፖለቲካዊ መልክዐ ምድር አንፃር ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡
እኔ የለማን አቋም የምረዳው፣ አሁን እየተፈጠረ ባለው የጠቅላላው የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሞ ልሂቃን ንቃት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ኦነግ በ1967 ጫካ ሲገባ ያነገበው ዓላማ ኦሮሚያን መገንጠል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለዚህም የኦሮሞ ልጆች ከፍተኛ ዋጋና ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ኦነግ ኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረውም የሚታወቅ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ለኦሕዴድ አባላት “እንደ ፈጣን ሎተሪ ብትፋቁ ሁላችም ውስጣችሁ ኦነግ ነው” ማለታቸው ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ይህም እንኳን ሌላው ኦሮሞ፣ የኢህአዴግ አባላት ጭምር በልባቸው የኦነግን አላማ ያነገቡና ባንዲራውን የሚያውለበልቡ ስለመሆናቸው አመላካች ነው፡፡ ግን ይህ የኦነግ አካሄድ ትክክል ነበር?! ፍፁም ስህተት እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከቶ እንዴት ነው ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ልትገነጠል የምትችለው? ኦሮሚያ ሰፊ ግዛት እንዳላት የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ኦሮሚያ መሆኑም ግልፅ ነው፡፡ ኦሮሚያ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም ኦሮሚያ ናቸው፡፡ በእርግጥ ወደ ኋላ ላይ እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳን የመሰሉ “ኦሮሞ ቅርንጫፍ ሳይሆን ግንድ ነው፤ የሚገነጠለው ደግሞ ቅርንጫፍ ነው፤ ግንድ አይገነጠልም፤ስለዚህ ኦሮሚያ አትገነጠልም!” የሚሉ የኦሮሞ ልሂቃን መምጣታቸው እሰየው የሚያስብል ነበር፡፡
ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና ኦነግም ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ፣ ከቀደመ የከረረ አቋሙ መለሳለስ አሳይቷል፡፡ ኦሮሚያን መገንጠል የሚለውን ፕሮግራሙን ለውጦ፣ “ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት መቀጠልንም ሆነ መገንጠልን የሚወስነወ የኦሮሚያ ህዝብ ነው” ወደ ማለት አድጓል፡፡ “ህዝበ ውሳኔ አካሂደን የህዝቡን ፍላጎት እናስፈፅማለን” ማለት ጀምረዋል፡፡ ይሄ ከቀድሞው ፍላጎቱን በህዝብ ላይ የመጫን የድርጅቱ አምባገነንነት በእጅጉ የተሻለና የሰለጠነ ሊባል የሚችል አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ በጣም የተሻለው መልካም ዜና ደግሞ የቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር ኦቦ ሌንጮ ለታና ጓደኞቻቸው፣ “በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ፣ ለኦሮሞው መታገል ይቻላል” በሚል ከኦነግ ወጥተው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የተሰኘ ድርጅት ማቋቋማቸው ነው፡፡ ይህም በጊዜ ሂደት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ዳግም ተመልሶ ሊያብብ እንደሚችል ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው፡፡
አሁን በኦሮሚያ የፖለቲካው መልከዓ ምድር እየተለወጠ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ የኦቦ ለማ የወቅቱ አቋምም ይህን እውነት ከመገንዘብ የመነጨና ንቃት የወለደው እውነታ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢጆሌ ኦሮሞና በቴዎድሮስ ልጆች መካከል እየታየ ያለው መቀናጀትና አንድነት፣ የኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ እየኮሰመነ፣ የትብብርና አንድነት አስፈላጊነት እየተገለጠ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡
ይህን ስል ግን አሁን የኦሮሞ ብሄርተኝነት የለም፤ “ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊ መባልን የሚጠሉ ዜጎች የሉም” እያልኩ እንዳልሆነ ይያዝልኝ! ነገር ግን ከዓመታት አዝጋሚ ሂደት በኋላ ኦነግ እንደተለወጠው ሁሉ፣ እነዚህም ዜጎችም እንደሚለወጡ ተስፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚሻለውም እሱ ነው! እና አቶ ለማ ጊዜው የሚጠይቀውን እውነት ተረድተው፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ቢዘምሩና ታሪክ እያጣቀሱ ኢትዮጵያን ቢዘክሩ መደነቅ የለብንም ባይ ነኝ፡፡ ሌላው ሀሳቤን የሚያጠናክርልኝ ነገር፣ የኦሮሞ ልጆች ባለፈው ወር ግድም “ጣና ኬኛ” በማለት ወደ ባህር ዳር ተጉዘው፣በእምቦጭ ነቀላ ላይ መሳተፋቸው ነው፡፡ በእርግጥም የኢህአዴግና የአንዳንድ ተቃዋሚ የኦሮሞ ፓርቲዎች የጎሳ ፖለቲካ፣ ግብዐተ መሬቱ በቅርቡ የሚፈፀም ይመስላል፡፡ እውነት ይሁንልን ከማለት በቀር ሌላ ምን ማለት ይቻላል?! ከዚህ በተቃራኒ የሆነውን ሌላኛውን ጎን (The other side of the story) ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡ የነገ ሰው ይበለን!

Filed in: Amharic