>

“እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠው…” (ኤፍሬም እንዳለ)

አሁን ችግራችን አገራዊ ሆኗል፡፡ ሰዎች በግልምጫ ሳይሆን፣ ፊት በመንሳት ሳይሆን፣ “ውጣ አትበለው እንዲወጣ አድርገው፣” በሚል ብቻ ሳይሆን ሰዎች በግልጽ ‘ውጡልን፣ ጥፉልን፣ ዓይናችሁን አንየው’ እየተባሉ ነው፡፡ ከዚህ ውጡልን፣ የምትሄዱበት ሂዱልን አይነት ነገር እንደ ወረርሽኝ እያደረገን ነው፡፡

አያናግረንም የያዘን አባዜ
ዝም አያሰኘንም የያዘን አባዜ
እንደው ፍዝዝዝዝ ያሰኘናልሳ
ቅጥ አምባሩን ያጣ የቁም-ሞት አበሳ

ይላል ነቢይ መኮንን፡፡ ቅጥ አምባሩ ጠፍቶብን አንደኛውን ወደቁም ሞት ከመግባት ይሰውረን፡፡

ምሳሌ ለመጥቀስ፣ በአንድ የአገራችን አካባቢ ከወራት በፊት ሆነ የተባለ ነገር ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት አብረው ኖረዋል፡፡ በደስታም፣ በሀዘንም ተለያይተው አያውቁም፡፡ በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች ናቸው፡፡ እነኚሁ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ያወራሉ፡፡ ይሄን ጊዜ አንደኛው ሌላኛውን “ለምን አትወጣልንም!” ይለዋል፡፡ እንዲህ ባዩ እኮ እጅግ በጣም ቅርብ የተባለው የልብ ጓደኛው ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ደረጃ የሚቀራረበው ነው ! እናም ድንጋጤ ይሆናል፡፡ ሌላኛው ሰው “እንዲህ ስትል ምን ማለትህ ነው?” ይለዋል፡፡

“በቃ፣ ይውጣልና! ይሄ የእሱ አካባቢ አይደለም፣” ይላል፡፡ ምልልሰ ቢጤም ይፈጠራል፡፡ በዚህ ጊዜ “ለምን አትወጣልንም!” የተባለው ሰው፣ “ይሄ እኮ እትብቴ የተቀበረበት ቦታ ነው፣” ይላል፡፡

ይሄኔ ነው አስደንጋጩ ነገር፣ “የእውነትም ወዴት እየሄድን ነው?” የሚያስብለው ነገር የተከሰተው፡፡ ያ “ውጣልን” ባዩ ሰው ለሌላኛው ምን ቢል ጥሩ ነው፣ “እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠውና ይሂድልን!” አለና አረፈው፡፡ አሳዛኝ ነው፣ አስደንጋጭ ነው፣ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚዳዳ ነው፡፡ ወዳጅነቱ እንኳን ቀርቶ ይህ ከሰብአዊነት የተፋታ አስተሳሰብ አገር እያፈረሰ ነው፡፡

በሰማንያዎቹ መጀመሪያ መንግሥት ሲለወጥ አንድ መንደር ውስጥ የሆነች ክፍት ቦታ ነበረች፡፡ እናም… አንዷ ሴትዮ ጠዋት ወጡና የሆነ ስፋት ያለው ቦታ ላይ በአራት ማእዘን አስምረው “ይሄ የእኔ ነው፣ እዚች ማንም ሰው እንዳይገባ!” አሉ፡፡

ሌሎቹም እየመጡ እያሰመሩ “የእኔ ነው፣” “የእኔ ነው፣” እያሉ ያሰምሩ ገቡ፡፡ አንድ እግራቸውን ዘርግተው ቢቀመጡ እንኳ የማይበቃ ስፍራ ነው እኰ! የሄ የሁላችንም የሆነ መሬት ላይ መሰመር እያሰመሩ “እዚች ማንም ሰው እንዳይገባ!” አይነት አመለካከት ዘንድሮም እያመሰን ነው፣ መልኩን ለውጦ ደረጃውን አሳድጎ…“እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠውና ይሂድልን!” እየተባለ ነው፡፡

እና ይሄ “እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠው…” አይነት ነገር ማንንም ሳይለይ መታየቱ አስፈሪ ሊሆን ይገባል፡፡ ‘የእውቀት ማነስ ነው’ ከሚባል ደረጃ አልፏል፡፡ በነገራችን ላይ…ሰዋችን “የተማረ ይግደለኝ፣” የሚልበት ጊዜ ነበር፡፡ ምክንያቱም መማር ማለት፣ በእውቀት መምጠቅ፣ በስነምግባር መታደስ ማለት ነበራ ! የተማረ ነገሮችን ማገናዘብ ይችላል፣ ከስሜታዊነት የጸዳ ነው ይባል ነበራ!

አዎ፣ ያ “የተማረ ይግደለኝ” ይል የነበርው ህዝብ አሁን ተማሩ የተባሉት የሚሆኑትን እያየ በእሱና በእነሱ መካከል ያለው ልዩነት ምን እንኳን እንደሆነ ግራ እየገባው ነው፡፡ የ“እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠውና ይሂድልን!” አስተሳሰብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በነገ አገር ተረካቢዎች፣ በነገ ቤተመንግሥት ወራሾች፣ በነገ ፖሊሲ አውጪዎች መሀል ብሶ ማየቱ የምር ተስፋ የሚሸረሽር ነው፡፡ ለምን ? እንዴት እዚሀ ደረጃ ልንደርስ ቻልን?

በፊት ባል ሚስቱን ማለዳ ተነስቶ “በይ ጨርቅሽን ሰብስቢና ወደምትሄጂበት ሂጂ!” ማለት የሚችልበት ህብረተሰብ ነበር፡፡ አሁን ባይጠፋም ቅሉ እንዲሁ በቀላሉ “ጨርቅሽን ጠቅልለሽ ውጪልኝ” ብሎ ነገር ጊዜ ያለፈበት እየሆነ ነው፡፡

ታዲያ እንዴት ነው፣ “አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡልን!” ማለት እንዲህ ቀላል የሆነው? በነገራችን ላይ…አይደለም ስንት ዘመን አብሮ የኖረን አይቶ የማያውቀውን የመሸበት መንገደኛ እኮ ተቀብሎ፣ አብልቶ፣ አጠጥቶ እግር አጥቦ ባማረ መኝታ የሚያሳደር ህብረተሰብ ነበር እኮ!

በፊት እኮ ከአንድ ስፍራ ወደሌላ ሲኬድ ኪሳችንን እንፈትሻለን፣ መታወቂያችንን መያዛችን እግርጠኛ ለመሆን፡፡ “መታወቂያ የለኝም፣” ማለት ማንነታችንን የምናረጋግጥበት ነገር የለንም ማለት ነው፡፡ አሁን ግን ራቅ ብሎ ሲኬድ “መታወቂያ፣” ስንባል ለማሳየት መስጋት ደረጃ እየደረስን ነው፡፡ ምንም አይነት ነገር ስለሠራን አይደለም፡፡

ምንም አይነት ጥፋት ፈጽመን ‘ተፈላጊ ወንጀለኛ’ ስለተባልን አይደለም፡፡ መታወቂያ ላይ የተከተበው ማንነታችን፣ የዘር ግንዳችን አደጋ ላይ ሊጥለን ስለሚችል እንጂ፡፡ አዎ መድገም ያስፈልጋል…ማንነታችን፣ የዘር ግንዳችን አደጋ ላይ ሊጥለን ስለሚችል ! ልክ “መታወቂያዎች ሁሉ እኩል ናቸው፣ አንዳንድ መታወቂያዎች ግን ዝቅተኛ ናቸው፣” የሚባል ነገር ያለ ይመስል፡፡ “መታወቂያዬን አይተው ይተናኮሉኝ ይሆን!” ብለን የምንሰጋበት ዘመን መድረሳችን ያሳዘናል፡፡

በፊት የእንትን ሰፈር ልጅ፣ የእንትን ግሩፕ እየተባለ ሰፈር ለሰፈር ይፈሳፈስ ነበር፡፡ የዚህኛው ሰፈር ልጅ በዛኛው ሰፈር አካባቢ ዝር ማለት አይችልም ነበር፡፡ በደመ ነፍስ የጉርምስና አስተሳሰብ “እንትን ሰፈርን ሄደን እንበጥብጠ፣” ተብሎ ከአራት ኪሎ እስከ አትክልት ተራ ወላ ሱቅ፣ ወላ መኖሪያ ቤት በር ሁሉ የሚከረቸምበት ዘመን ነበር፡፡

ዘንድሮ ሰዎች ከልጅነት እስከ እውቀት በኖሩበት ስፍራ በማንነታቸው የተነሳ የሚመጣባቸውን በመፍራት በርና መስኮታቸውን ከርችመው መኖር የተገደዱ ዜጎቻችን መኖራቸውን ማወቁ ያሳዝናል፡፡

በቀደም በኳስ ተብሎ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ግጥሚያው ሳይጀመር፣ ቡድኖች ሜዳ ሳይገቡ፣ ዳኛው የጀምሩ ፊሽካ ሳይነፋ በደጋፊዎች መሀል ጠብ ተነሳ አሉ፡፡ የንጹሀን ህይወት ሁሉ እስክመጥፋት ደረጃ ደርሷል፡፡ ምንም አይነት ኳስ፣ ምንም አይነት ፕሬሚየር ሊግ ምናምን በማንኛውም መለኪያ ከሰው ህይወት በላይ ሊሆን አይችልም፡፡

እናም … በደፈናው “ስርአተ አልባ ደጋፊዎች በፈጠሩት ረብሻ፣” ብሎ ደባብሶ ማለፉ የትም አያደርስም፡፡ ነገሩ አስፈሪ በሆነ መልኩ ከኳስ ያለፈ ነውና፡፡ የፍቅር፣ የወንድማችነት፣ የሰላም የተባለው ኳስ ጭራሽ “በለው፣ በለውና አሳጣው መድረሻ!” ለመባባል ምክንያት ሲሆንና አጄንዳው ኳሷን ሜዳ ላይ ከማንከባለል አልፎ ሲሄድ ማየቱ አሳዛኝ ነው፡፡

አንድ ችግራችን እንደ በግ ጨጓራ ቢያጥቡት፣ ቢያጥቡት አልጠራ ያለ የጣት መቀሳሰር የፖለቲካ አስተሳሰባችን ነው፡፡ የሆነ ቦታ ላይ የትራፊክ መብራት ያቁመው፣ ነዳጅ ይለቅበት፣ ሞተሩ ፉዞ ይሁን … ብቻ የሆነ ቦታ ላይ ቀጥ ያለ ይመስላል፡፡ ከዘመነው አስተሳሰብ ጋር እኩል መራመድ አለመቻላችን በብዙ አጥፍ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡

ዓለም በአስተሳሰብ እየገሰገሰ፣ ሀሉም አይነት አመለካከቶች መሬት ላይ ካሉት ሁኔታዎች እየተዛመዱ እያለ፣ እኛ ግን “ማን ወንድ ነው ከመሬቴ የሚነቅለኝ” እንደሚል ባለርስት፣ ለበርካታ አስርት ዓመታት ከያዝነው እንደ ኤሊ ከሚጎተት አስተሳሰብ “ማን ወንድ ነው የሚነቀንቀኝ!” ያልን ይመስላል፡፡

በኮምፒዩተር ቋንቋ ዊንዶው ኤይት፣ ዊንዶው ምናምን እየተባለ የፍጥነት ሩጫ ተይዞ እኛ ገና ለዘመኑ ፕሮግራሞች ያልተቃኘ ‘ኤም፣ኤስ ዶስ’ ላይ ቆመናል፡፡ የዘመኑን ጫና መሸከም የማይችል፣ ከዘመኑ ሁለገብ ግስጋሴ ጋር ትከሻ ለትከሻ የማይገጥም አስተሳሰብ ቀፍድዶ የያዘን ይመስላል፡፡

ዲስኩር እንደ ልብ ነው፣ ልብ የሚነኩ አረፍተ ነገሮች፣ የሚያስጨበጭቡ ቃላቶች፣ ለጥቅስ የሚበቁ አባባሎች በሽ ናቸው፡፡ ግን … ከጥቅስና በንግግር ከማጨብጨብ ማለፍ ያለብንና ወደ አስራ አንደኛው ሰዓት እየተጠጋን ያለ ጊዜ ላይ ነን፡፡ ያጣነው፣ የናፈቀን፣ የማይደረስበት የተራራ ጫፍ የሆነብን የሚያስጨበጭብ ሥራ፣ ለታሪክ የሚበቃ ተግባር ነው፣ እሰይ ስለቴ ሰመረ የሚያሰኝ የሚታይ፣ የሚዳሰስ ስኬት ነው፡፡

በበርካታ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ብዙ ዘመን ከኖሩበት፣ ንብረት ካፈሩበት፣ ቤተሰብ ከመሰረቱበት፣ ወልደው ከከበዱበት… “እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠውና ይሂድልን!” ሲባሉ ማስደንገጥ አይደለም፣ እንቅልፍ ሊያሳጣ የሚገባ ነው፡፡

እንዴት ይሆናል! ወደ ውጪም ተሰደን፣ በአገራችን ውስጥም ተሰደን… እንዴት ይሆናል! እንደ አስራ ዘጠኝ አርባዎቹና ሀምሳዎቹ አሜሪካ፣ እንደ ጥቂት አስርት ዓመታት በፊቷ ደቡብ አፍሪካ ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ በፈለጉት የአገሪቱ ክፍል የማይሄዱበት፣ በፈለጉት ስፍራ የማይኖሩባት አገር ልትፈጠር ዳር፣ ዳርታው ያስፈራል፡፡

ምነው ዝምታው በዛ ! ምነው “ወንበሬን አይንኩብኝ እንጂ ለሌላው እንደፍጥርጥራቸው!” አይነት ቸልተኝነት በዛ ! “እኔም ግዴታዬን እወጣለሁ፣ እነሱም መብቴን ያስጠብቁልኛል ያልናቸው…ምነው “በእኛ ጊዜማ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር ዝም ብለን አናይም!” ወይም ፈረንጅ እንደሚለው “ኖት ኦን ማይ ዋች!” ማየት፣ መስማት ተሳነን!

በነገራችን ላይ አለቆች ስለተቃቀፉ፣ የቴሌቪዥን መስኮቶች በሳቅ በሚፍለቀለቁ ባለወንበሮች ሰለተሞሉ ሁሉም ነገር ተስተካክሏል ማለት አይደለም፡፡ መተቃቀፍ መጨባባጥ ለተመልካች ደስ ሊል ይችላል፡፡ ህዘቡስ ! “ለምን አትወጣልንም!” የተባለው ህዝብስ… አብሮ ስንት ዘመን በኖረው ሰው “እትብቱን አውጥተህ ስጠው፣” የሚባለው ህዝብ ድምጽስ ! አስወጪና ‘ውጣ’ የሚባለው ለምንድነው ፊት ለፊት የማይነጋገሩት!

በነገራችን ላይ መድረክ ላይ ያሉት ተናገሪ ሁሉን አዋቂዎች፣ ትንታኔ ሰጪዎች፣ ብያኔ አሳላፊዎች፣ ከመድረክ በታች ያለው ደግሞ አዳማጭ ብቻ፣ “በእርሶ መጀን!” ባይ ሆኖ የትም አይደረስም፡፡

“ለእናንተ የሚያስፈልጋችሁ የስንዴ ዳቦ ነው፡፡”
“የለም፣ ለእኛ የሚያሰፈልገን የጤፍ እንጀራ ነው፡፡”
“እኛ ዳቦ ነው አልናችሁ እኮ…”
“እኛ ደግሞ ምርጫችን ጤፍ ነዋ፡፡”

“ዳቦ እንዳይሆን የማይፈልጉ ጥቅማቸው የተነካባቸው አንዳንድ የጤፍ ነጋዴዎች…”
ሁልጊዜ ጣት መቀሰሪያ ፍለጋ፣ ሁልጊዜ ፊት ለፊቱን በደንብ ሳያዩ ከጀርባ ያለ ነገር መቆፈር!

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ‘እናት ዓለም ጠኑ’ ትያትር ላይ ደምበል የተባለው ገፀ ባሀሪይ እንዲሀ ይላል… “ልጆቻችንን በላን…ትላንት የነፃነትን ምጥ ከአፋፍ መንግለን የጥላቻ ውርስ አቆይተን አፈአዊ ነፃነት አውርሰን ምነው ባሉ ልጆቻችንን ገፍተን፣ አፈአዊ እኩልነት፣ አፈአዊ ክትባት ከትበን ፍርሀት ወርሰን ፍርሀት አውርሰን፣ ጥላቻ ወርሰን ጥላቻ አውርሰን፣ ሕያው ሳንሆን አፈአዊ፣ ቃለ ሕይወት ሳንሆን ብኩን ቃለ አፍ … እንጂ ቤታችንስ አንድ ነው፡፡”

አዎ፣ አሁንም ቤታችን አንድ ነው እያልን ነው፡፡ በምስራቅም፣ በምዕራብም፣ በሰሜንም በደቡብም…የትም የመኖር፣ የትም የመሄድ መብታችን ደስ ያለው ሹም የሚሰጠው፣ ደስ ያላለው ሹም የሚነፍገው አይደለም፡፡ ማንም ሰው ማንንም … ማንንም … ማንንም “ከዚህ ውጣ” ማለት አይችልም፡፡ ማንም፣ ማንንም “እትብቱን ከተቀበረበት አውጥተህ ስጠውና ይሂድልን!” ሊል አይችልም፡፡

Filed in: Amharic