>

የብአዴን አመራሮች ለራሳችሁ እና ለልጅ ልጆቻችሁ አልቅሱ! (ሃብታሙ አያሌው)

አይሁድ ክርስቶስን ሊሰቅሉት ወደ ቀራንዬ ይዘውት ሲወጡ የእየሩሳሌም እናቶች እየተከተሉት ያለቅሱ ነበር። እሱም የእሱ ፅዋ ስለሰው ልጆች ሁሉ መዳን የግድ ናትና

” እናንተ የእየሩሳሌም ሴቶች ለኔ አታልቅሱ ለልጅ ልጆቻችሁ አልቅሱ” አላቸው። የልጅ ልጆቻቸው አምላክን የሰቀሉ የወንበዴ ልጆች እየተባሉ በታሪካቸው ሁሉ ሲሳደዱ ይኖራሉና ይህንን አላቸው።

የብአዴን አመራሮች ከዚህ በኋላ በአጉል ንግግር በቁስላችን እንጨት አትስደዱ በሞታችን ዜና ዳንኪራ አትደልቁ፤ እንደ ካናዳ በረዶ አጥንታችንን ሰርስሮ ለሚጠዘጥዘን የህወሓት ክፋት ለጊዜው ሰላም ባስ ላይ ፍም አራግበን እንሞቃለን። ፊታችንን ብንመልስ ግን ቶሎ የሚግለበለበው የእናንተ ጎጆ እንደሚቀርበን ልታውቁ ይገባል። ከቻላችሁ እንደ ለማ መገርሳ ካቢኔ ኮምጨጭ በሉ አየለያ ግን እየረፈደ እንደሆነ እወቁት ።

የሚቆጭ ህሊና ያላችሁ እንደሆነ እነዚህን አስር ነጥቦች ብቻ በየቀኑ እየደረሰብን ያለውን የስብራታችንን ልክ ይናገራሉ።

1. በአዲግራት ዩኒቨረስቲ በነዉጠኞች ተቀጥቅጦ የሞተዉ ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ከዳሞት ጎጃም
2. ለጊዜዉ የትዉልድ ቦታቸዉ በደንብ ያልታወቁ 3 ከአማራ ክልል የተመደቡ እና አዲግራት ዩኒቨርስቲ የተገደሉ :-
3. አዲግራት ዉስጥ በቀላል ጉዳት 29 በከፍተኛ ጉዳት 14 የተመዘገበው ተማሪዎቻችን ጉዳይ፤
4. በአክሱም ዩኒቨርስቲ ሁለት ከአማራ ክልል በተመደቡ ተማሪዎች ላይ የተፈፀመው በድንጋይ መወገር
5. በወልድያ ዩኒቨርስቲ በአጋዚ ወታደር ተገዳ የተደፈረች ተማሪ ነገሩን ለፖሊስና ለዩኒቨርስቲዉ ብታሳዉቅም ጉዳዩ እንዳይሰማ ተብሎ የመሸፋፈኑ ነገር
6. በዉርጌሳ በአጋዚ የተረሸኑት የአራቱ የወሎ ወጣቶች ጉዳይ
7. ከደብረታቦር ዩኒቨርስቲ  በፌደራል ፖሊስ ደብድቧቸዉ ወደ ባህርዳር ሪፈር ተብለዉ ፈለገህይወት ሆስፒታል ዉስጥ ስላሉት ዜጎቻችን ጉዳይ

8. ወልድያ ዩኒቨረሲቲ በከፍተኛ ጉዳት ዉስጥ ሆነዉ ህይወታቸዉ ላይተርፍ ይችላሉ የተባሉ አራት ተማሪዎች ዛሬም ወልዲያ ሆስፒታል ተኝተዉ ያሉበት ሁኔታ

9. የመቀሌ ከነማ እግር ኳስ ደጋፊዎች የሰሩት አጸያፊ ነገሮችና የክልሉን ህዝብ ሰላም በማደፍረስ እንዲሁም ለሁለት ዜጎች ሞት ምክንያትና በሚሊዬኖች ለሚቆጠር ንብርት ዉድመት ተጠያቂ የመሆናቸዉ ጉዳይ፤

10. የመቀሌ ከነማ ደጋፊዎች ወልድያ ያረፉበት የላል ሆቴል አንዲት ሰራተኛ በቡድን አስገድደዉ መድፈርና የሆቴሉን ንብረት አውድመው የመሄዳቸው ጉዳይ፤
ለማን የተተወ ነው ? አቶ ንጉሱ ምን አልባት ይሰማዎት እንደሁ የኦህዴድ አቻዎት አቶ አዲሱ አረጋ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ቁጭታቸውን የገለፁበትን ንግግር ላስታውስዎ፤

አቶ ለማ መገርሳ ኮምጨጭ ባለ ንግግር እንዲህ ሲሉ ነበር በህወሓት ውጅሌዎች እግር ስር ፍማቸውን ያኖሩት።

“ሰው ሲያጠፋ የሚጠየቅበትና የሚቀጣበት ህግ አለ! ከዛ ባለፈ መልኩ በህዝባችን ላይ የዚህን አይነት ድርጊት መፈፀሙን እናወግዛለን!ተቀባይነትም የለውም! እንደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይህ ድርጊት ተጣርቶ ግድያውን የፈፀሙ አካላት ለህግ ቀርበው በህግ እንዲቀጡ ከማደረጋችን በተጓዳኝ ህዝቡ ጉዳዩን እንዲያውቅ ግልፅ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ተጣርቶ ይህን ህገ ወጥ ጭፍጨፋ የፈፀሙ ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ እንደምንሰራ ለመግለፅ እፈልጋለሁ! የሰላም ኃይሎች ከህዝብ ጋር በመቆም በአንድነት ለህዝቡ ሰላም መረጋጋት ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ ጉዳይ ነው! የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ ከክልሉ ህዝብ ጎን ሊቆም ይገባል !”

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዬች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩሉ እሮብ ህዳር 13 ቀን ማምሻውን በአሜሪካን ድምፅ ራዲዬ ቀርቦ የአቶ ለማ መግርሳን ንግግር በሚገባ በማብራራት :-
“ፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት በህገ መንግስቱ መሰረት ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ችግር አጋጥሞ እርዳታ እስካልተጠየቁ ጣልቃ ሊገቡ አይገባም። ይሁን እንጂ ማን እንዳዘዘ ሳይታወቅ እኛ ሳንጠራቸው ባዶ እጃቸውን ሰልፍ የወጡ ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙትን ገድለዋል። በዚህ መላው የክልሉ ህዝብ እና እኛ ከባድ ሃዘን ውስጥ ነን የልብ ስብራት ደርሶብናል”
በማለት እጅግ በሚገርም መንገድ ሲገልፅ ተሰምቷል።

Filed in: Amharic