>

የሰቆቃና ቶርቸር ዳይሬክተር ጄነራል ጌታቸው አሰፋ (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ከአድዋ ስረወ መንግስት መሪዎች አንዱና ዋናው ነው። የደህንነት(የሰቆቃ) መስሪያ ቤት ዳይሬክተር፡ ገዳይ አስገዳይ፡ ገራፊ፡ አስገራፊ፡ የለየለት ጨካኝ። መልኩ ቀይ፡ ልቡ ጥቁር፡ ባህሪው ልስልስ፡ ተግባሩ እርኩስ፡ ድምጹ የማይሰማ፡ የጭካኔው ወሰን በኢትዮጵያ ምድር ጫፍ እስከጫፍ የደረሰ ፍጹም አረመኔ ሰው ነው። በቴሌቪዥን መስኮት ታይቶ አይታወቅም። የአደባባይ ሰው አይደለም። መድረክ፡ ስብሰባ ላይ አይታይም። ቢኖር እንኳን በፎቶና በቪዲዮ ራዳር ውስጥ እንዳይገባ ይደረጋል። እናቶቻችን ‘ቀትረ ቀላል፡ ጥላቢስ፡’ የሚሉት ዓይነት ሰው ነው።

ማዕከላዊን ረገጠው ህይወታቸው ሳያልፍ የወጡ እድለኛ ታሳሪዎች በአንድ ቃል እንደሚናገሩት ሰቆቃ፡ ግርፋት፡ ግድያ፡ የሚፈጸሙት ትግርኛ በሚናገሩ ሰዎች ነው። የእነዚህ ሰዎች አለቃ፡ መሪ ደግሞ ይህ ሰው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት በተፈጸሙት ፖለቲካዊ ሰቆቃዎች፡ ግድያዎች፡ እስሮች፡ውስጥ ይህ ሰው ዋናው ተዋናይ ነው።  ይህ ሰው የስንቱን የኢትዮጵያ ልጅ የቀን ብርሃን አጨልሟል፡፡ የስንቱን ወጣት ተስፋ ቀጥፏል፡፡ አያሌ ህጻናትን ያለአባት፡ ያለእናት አስቀርቷል። ስንቱን ቤተሰብ በትኗል።

ይህ ሰው ማዕከላዊ ሌሊቱን ሲገርፍ ሲያስገርፍ፡ ያድራል፡ ሲደክመው ዋሽንግተን ዲሲ መጥቶ ውስኪውን ይጎነጫል። የኢትዮጵያን ወጣት ዘቅዝቆ፡ በርበሬ እያጠነ፡ በሽንት የተነከረ ጨርቅ እያጎረሰ ወፌ ላላ እየሰቀለ፡ ብልት እያኮላሸ ሲያሰቃይ ይቆይና ለእረፍት ጣሊያን ሲሲሊያ የባህር ዳርቻ በረር ብሎ ይንፈላሰሳል። ድንቁርናው አይጣል ነው። በዊኪሊክስ እንደተጋለጠው ከሆነ ይህ ሰው አሜሪካንን አስፈራርቷል። ያማማቶ ለተባሉ የአሜሪካ አምባሳደር ”አሜሪካ የእኛን ተቃዋሚዎች መርዳት የማታቆም ከሆነ እኛም ለአሜሪካን ተቃዋሚዎች ድጋፍ እናደርጋለን” ማለቱን ዊክሊክስ አስነብቦናል።

ህወሀት የአድዋን ስረወ መንግስት በሰየመበት በሰሞንኛው መድረክ ይህን ሰው ዳግም ከፍ ያለ ቦታ ሰጥቶታል። መልዕክቱ ግልጽ ነው። ለውጥ የለም። የነበረው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ቀጥቅጠን፡ ረግጠን እያኮላሸን፡ በኤሊክትሪክ ሽቦ ጡት እየተለተልን በጉልበትና በሃይል እንቀጥላለን የሚል መልዕክት መሆኑ ይገባናል። ህወሀት ተውሳኩን አስወግጄ መጣሁ፡ ታድሼ፡ ተወልውዬ በአዲስ መንፈስ ለለውጥ ተነሳሁ ያለው ይህን የዲያቢሎስ ቁራጭ፡ የሳጥናኤል ወንድም፡ ክፉና ነውረኛ ሰው ከስልጣን ማማ ላይ አስቀምጦ ነው።

ይህ ሰው በሰው ልጅ ላይ በፈጸመው ወንጀል፡ በዘር ማጥፋት፡ ወደር በሌለው የሰቆቃ ተግባሩ እጁ ወደ ኋላ ተጠርንፎ በፍትህ አደባባይ ቅጣቱን ማግኘት የሚገባው ሰው ነበር። ደግሞም አይቀርም። ይዘገይ እንደሁ እንጂ ፍትህ ይመጣል።

Filed in: Amharic