>
5:13 pm - Sunday April 19, 6578

አወይ ህወሓት ተደናጊረ (ሀብታሙ አያሌው)

የአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ በኦሮሚያ የመታወቂያ ካርድ ላይ ብሔር የሚል ጥያቄ እንዳይኖር ቁርጥ ያለ ውሳኔ ማስተላለፉ ተሰምቷል። ይህ በእጅጉ የሚደገፍ ተራማጅ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2001 ዓ/ም በቀድሞ ጊዜ ደርግ ለህፃናት ማሳደጊያ በሰራው ዝዋይ በሚገኘው አምባ (በአሁኑ አጠራራ የግብርና ኮሌጅ)  የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች “የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ስልጠና” ለመከታተል በከተሙ ጊዜ በመካከላቸው ነበርኩ። እናም ይህ መታወቂያ ላይ ብሔር የመፃፍ ነገር ለምን አይቀርም? የሚል ጥያቄ ወደ መድረኩ ወረወርኩ። ያገኘሁት ምላሽ ጥሩ አልነበረም፤  የኃይል መድረኩ መሪ የነበረው በረከት ስምዖን ተቆጣ፤ “የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን ልዕልና በትምክህት ኃይሎች ሲፈተን የሚሸራረፍ አይደለም፤ የብሔረሰቦችን ስም ከመታወቂያ ላይ እንፋቅ የሚል እምነት ከዚያው ከትምክህተኛው አስተሳሰብ ጫና የሚነሳ ነው…”

የበረከት ስምዖን ቁጣ የተቀላቀለበት የማሸማቀቂያ ምላሽ ሲጠናቀቅ ዛሬም እዛው ያለ በመሆኑ ለደህንነቱ ስል ስሙን የማልጠቅሰው አንድ ባለ ስልጣን ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ እንዲህ አለኝ  “ወዳጄ ምን ነካህ? እቺን ሀገር እስከ ጥግ የዘረፈው ማን እንደሆነ ይታወቃል፤ ከመታወቂያ ላይ ብሔር የሚለውን ቃል  አንተ እንዳልከው ሰርዘው ከተደባለቁ በኋላ በምን ሊለዩ ነው ? ”  አፌን ይዤ እስኪደክመኝ ሳቅኩኝ።

…እናም ዛሬ የለማ መገርሳ አስተዳደር ብሔር የሚለው ቃል በመታወቂያ ላይ እንዳይፃፍ  ውሳኔ ለማሳለፍ እንደምን ብርታት አገኘ ? የሚል ጥያቄ ወደ አዕምሮዬ ጎራ ብሎ ዝዋይ አምባ (አላጌን)  አስታወሰኝ።
አወይ ህወሓት ተደናጊረ ተደናጊረ  ተደናጊረ…

Filed in: Amharic