>
5:13 pm - Thursday April 18, 8486

ንግስት ይርጋ፥ በኦነግ ስም የሽብር ወንጀል ለተመሰረተባት፣ ሰሚራ አማን ምስክር ሆና ቀረበች

ጥሩነህ ይርጋ

ንግስት ነጻነትና ፍትህ ይገባናል፥ አማራ ሕዝብ አሸባሪ አይደለም፥ በማለት ድምጿን ከፍ አድርጋ በአደባባይ በማሰማቷ፥ አሸባሪ በሚል የወያኔ ሃሰተኛ ክስ በቃሊቲና በማዕከላዊ ማሰቃያ ቤቶች ታስራ፥
ጥፍሮቿ በጉጠት ቢነቀሉና ለጋው ሰውነቷ በጠላት በትር ቢደቅምም መንፈሷ እጅግ ጠንካራ ነው።

በጨለማ ክፍል ተዘግታ፥ እጆቿ በሰንሰለት ታስረው፣ ጠመንጃና ቆመጥ በታጠቁ የወያኔ ጀሌዎች ተከባ በይስሙላው ፍርድ ቤት ስትመላለስ፥ እንደ እንስት አንበሳ በሚያስደነግጥ ግርማ እየተጓደደች፥ ቁጣዋ እንደ አራስ ነብር ከፊቷ እየተንቦገቦገ፥ ዛሬም የፍትህ ያለህ በማለት ጠላቶቿን መሞገቷን አላቆመችም።

ከጎንደር ወልቃይት ጠገዴ እስከ አርማጭሆ ተራሮች በግፍ የፈሰው የአማራ ሕዝብ ደም ቢቆረቁራት፥
ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ ተጉዛ ያየችው የሰው ልጆች እንባና የንጹሃን ጩሆት ውስጧን ቢያንገበግባት፥
ከአዲስ አበባ፣ ዝዋይ እስከ ሸዋ ሮቢት፥ ከደዴሳ እስከ ብር ሸለቆ በተገነቡት የወያኔ ማሰቃያ ጉሩኖዎች የሚሰማው የወገኗ መከራና ስቃይ እረፍት ቢነሳት ወደ አደባባይ የወጣችው የአማራ ሕዝብ የማንነት ታጋይ ወጣት ንግስት ይርጋ፥ በኦነግ ስም የሽብር ወንጀል ለተመሰረተባት ሰሚራ አማን የተባለች ወጣት የመከላከያ ምስክርነቷን ያለ ምንም ፍርሃት ለችሎቱ አስደምጣለች፡፡
ንግስት ይርጋ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ ም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርባ ሰሚራ አማን በማታውቀው እና ባልጻፈችው ወረቀት ላይ እንድትፈርም በማስገደድ ድብደባ እንደፈጸሙባት የመከላከያ ምስክር ሆና ተናግራለች፡፡
በአስከፊው ማዕከላዊ እስር ቤት በወንጀል መርማሪዎች የደረሰባትን ግፍ ለፍርድ ቤት በመዘርዘር፥ ሰሚራ አማን በተፈጸመባት ድብደባ የተነሳ ያለ ፈቃዷ በተጻፈው ወረቀት ላይ እንደፈረመች የገለጸችው፥ በአማራ ክልል ከተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረገችው ወጣት ንግስት ይርጋ፥ ሰሚራ አማን በማዕከላዊ እስር ቤት በተፈጸመባት ድብደባ የተነሳ ጭንቅላቷ እና እግሯ ላይ ጉዳት በመድረሱ ለህክምና ሆስፒታል ገብታ እንደነበር ለችሎቱ አክላ አስረድታለች፡፡
ሲል የተነተነውን ዘገባ በተመለከትኩ ጊዜ አይ ጀግና!በእስር ላይ ሆናም የማትፈራ አንበሳ፥ እውነትም እቴጌ ጣይቱ በሚል እሄን ለመጻፍ ተገደድኩ።

Filed in: Amharic