>

በራስ መተማመንና ፅናት ያለው የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ይወስናል (ያሬድ ጥበቡ) 

አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ በኢህዴን/ብአዴን 37ኛ አመት በአል ላይ ያደረገው ንግግር ሊደመጥ የሚገባው ነው ። ይህን በአል የምናከብረው ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን የተቀበልነውን አደራ ትልቅነትና ይህንንም ለመወጣት መክፈል ስለሚኖርብን መስዋእትነት ለማሰላሰልም ጭምር ነው በሚል መልእክት “ኢህዴን/ብአዴን እህት ድርጅቴ ሳይሆን የራሴም ድርጅት ጭምር ነው” በማለት እንዴት ከድርጅቱ አራተኛ አመት በአል ጀምሮ በውስጡ እንደታገለበት ዘክሯል ። አባዱላ የተያያዘው ትግል ውስብስብና ከባድ እንደሚሆን የተረዳ ሰው መሆኑ ከንግግሩ መረዳት ይቻላል ። ያውም ይህን ያለው የወያኔ ስብሰባ ከማለቁ በፊት ነው ።

አሁን ወያኔ የነጌታቸው ረዳን ዓይነት የእሳትና ጭድ አራጋቢዎች ወደከፍተኛው ሥልጣኑ ማምጣት ግልፅ ያደረገው ነገር ቢኖር የኦህዴድ መሪዎች ለወያኔ ሰይፍ የተጋለጡ መሆኑን ነው ። አባዱላና ለማ የሚያሳዩት የመስዋእትነት ድፍረት ራሳቸውንና ትግሉን ለመከላከልም ከሚያስችል ብልሃትና አርቆ ማስተዋል ጋር የተጋመደ ነው ብዬ ማመን እወዳለሁ ። የብአዴን አመራርና አባላት ለአባዱላ ንግግር በተደጋጋሚ የሞቀ ጭብጨባ ያደረጉ ቢሆንም፣ አሁን ወሳኙ ሰአት እየተቃረበ ስለሆነ ከማጨብጨብ በዘለለ ከኦህዴድ አመራር ጋር ትክሻ ለትከሻ ተደጋግፈው በመቆም በመምጣት ላይ ያለውን የጌታቸው አሰፋንና ደብረፅዮንን ጭለማ መመከት ይጠበቅባቸዋል ። ፅናት የሚጠይቅ ሰአት ስለሆነ፣ በራስ መተማመንና ፅናት ያለው የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ይወስናል ።

ብአዴኖች ማወቅ ያለባቸው ትልቁ ነገር፣ በፍርሃት ወይም በብልጠት ከወያኔ ጋር አይደለም መሰለፍ ፣ ከኦህዴድ ጋር በቁርጠኝነት ለመወገን እንኳ ካመነቱ ለሚደርሰው ብካይና ጥፋት የታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ ። ኦህዴድም ኢህአዴግ ውስጥ አብሮት የሚያግዘው ክንድ ሲያጣ በአክራሪ ብሄርተኞች ተፅእኖ ስር ሊወድቅ ይችላል ። ይህ እንዳይሆን በብአዴን ላይ የወደቀው አደራ ከፍተኛ ነው ። ብአዴን ግን በውስጡ ያሉትን የወያኔ ወሬ አመላላሾች ከአመራሩ ሳያፀዳ የኦህዴድ አለኝታ ለመሆን ያለው እድል አጠራጣሪ ነው ። እነገዱ ለዚህ ምን ብልሃት አበጅተው ይሆን?

ለማንኛውም የአባዱላን አጭር የ11 ደቂቃ ንግግር ተመልከቱ፣ አድምጡ።

https://www.youtube.com/watch?v=f0MxjlSRxcs&feature=

Filed in: Amharic