>

ህወሃት የመጨረሻ ተሰላፊ አሳውቋል ምን አዲስ ነገር አለው? (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

 ህወሃት ሁለት ወር በፈጀ ግምገማ አመራር ቀይሪያለሁ ብሏል። ህወሃት አሁን በካሄደው ረጅም ግምገማ የተወሰነ የአፈፃፀም ልዩነት ሊታይባቸው የሚችሉ አከባቢዎች አሉ። እንያቸው
1 ኢፈርት በተወሰነ መልኩ የአፈፃፀም ልዩነት ሊያሳይ ይችላል ።ምክንያቱም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ምክትል ስራ አስፈፃሚ ከህዋሃት ስራ አስፈፃሚነት ስለተባረሩ ከኢፈርት ላይ መነሳታቸው አይቀሬ ነው።ስለዚህ ኢፈርት አከባቢ የተወሰነ የአፈፃፀም ለውጥ ሊኖር ይችላል።ቢንያስ የየድርጅቶቹ ስራ አስፈፃሚዎች መቀየራቸው አይቀርም።በኢህአዲግ ውስጥ የራስህን ኔትዎርክ ይዞ መምጣት የተለመደ ነው።ህዋሃት ደግሞ የኢህአዲግ እናት ናት።እናም ይደረጋል።
እዚህም ላይ የፖሊስ ለውጥ ተደርጎ ስንመኝ እንደነበረው ድርጅቱን ለትግራይ ህዝብ እና መንግስት በመሸጥ በሀገሪቷ የተንሰራፋውን የፓርቲ ንግድ ያስቀረዋል ተብሎ አይጠበቅም።ስለዚህ ኢፈርት ይበልጥ ሙሰኛ እና በዝባዥ ድርጅት ሆኖ የመቀጠል እድሉ ሰፍ ነው።ድርጅቱን ከዚህ አካሄዱ ሊፈታተነው የሚችለው እና በህልዊናው ላይ አደጋ ሊሆን የሚችለው የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በፍጥነት መሽመድመድ ነው።የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በፍጥነት መሽመድመድ በዋናነት እና በፍጥነት ሊጎዳ የሚችለው ከኢኮኖሚው በፍጥነት እና በዋናነት ተጠቃሚ የሆኑትን አካላት ነው።ስለዚህ ኢፈርት አመራሩን ቢቀይርም የፖለቲካ አመራሩ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ከውድቀት ካልታደገ በስተቀር የኢፈርት በኪሳራ መውደቅ በር ላይ ደርሷል።
2 ትግራይ ክልል ፣አሁን ሞንጀርኖ የክልሉ ሊቀመንበር የመሆን እድሏ ሰፍ ነው።እኔ የሳቸውን አቅም በደንብ አላውቅም።እሳቸው ጎበዝ ከሆኑ ክልሉ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።ግን ስለሞንጆርኖ በዱሮ ወዳጆቻቸው የተፃፈው ያንን አያሳይም።ለማንኛውም እኔ እሳቸው ጎበዝ እና ቀና ሆነው የትግራይ ህዝብ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ ቢያገኝ እጅግ ደስተኛ ነኝ።እንዲቀናቸውም ከልብ እመኛለሁ።
3 በሀገር ደረጃ በኢኮኖሚው ዘርፍ ፦ዶር አብረሃም ለረጅም ጊዜ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚንስትር ዴታ ናቸው።በተለይ በለፈው አንድ ዓመት ኢኮኖሚው ክፉኛ ሲጎዳ እሳቸው ሚንስትር ናቸው።ያደረጉት ማሻሻሻያ ግን የለም።አሁን እሳቸው የስራ አስፈፃሚ ሆነዋል።እድገት መሆኑ ነው።በተመደቡበት መስክ ምን ሰርተው እንዳደጉ የሚነግረን ሳይንትስት ካለ ለመስማት ዝግጁ ነን።በአጭሩ አንድ ድርጅት ከባድ ፈተና በገጠመው ዘርፍ ላይ የተመደበ ሰው የገጠመውን ችግር ቁጭ ብሎ የሚያይ ሰው ከሸለመ ማለት የሚቻለው መንገዱን ጨርቅ ያርግለት ማለት ብቻ ነው።ከዚያ በዘለለ ድርጅቱ የሀገሪቷን ኢኮኖሚም ሆነ የክልሉን ኢኮኖሚ እስትንፋስ ሊዘራበት የሚችል ንቁ እና ቀና የሪፎርም ሰው ስራ አስፈፃሚ ውስጥ አላካተተም።በውይይታቸውም ላይ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ መውደቅ የእህት ድርጅቶችን ማስቸገር ያህል የውይይት አጀንዳ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
4 በፖለቲካው ሪፎርም ይጠበቃል? በኢትዮጵያ በፖለቲካው ሪፎርም አድርጎ አለግባብ የታሰሩትን ለመፍታት እና ውጥረቱን ለማስተንፈስ የአቶ ጌታቸው መስሪያ ቤት ድርሻ ወሳኝ ነው።እሳቸው ደግሞ ያንን ማድረግ ብፈልጉ ማንም ከልካይ አልነበራቸውም።ማድረግ ይችሉ ነበር። ስለዚህ በዚህ ረገድ በግምገማው ምክንያት ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው።
5 ለመሆኑ በፌደራል ደረጃ የህወሃት ሊቀማንበር ላለፉት 5 ዓመታት ማን ነበር?በእርግጠኝነት አባይ ወልዱ ነው ብሎ የሚመልስ ሰው የለም።ያው ዶር ደብረፅዮን ነበሩ።ዶር ደብረፅዮን ምክትል ሊቀመንበር በመሆናቸው በፌደራል ደረጃ እሳቸው ፈልገው አቶ አባይ ወልዱ ባለመፈለጋቸው ሳይሆን አንድም የቀረ ነገር የለም።በተቃራኒው አቶ አባይ ፈልገው ዶር ደብረፅዮን ተቃውመው የሆነ ነገርም የለም።ዶር ደብረፅዮን በስራ የህወሃት ሊቀመንበር ነበሩ ማለት ማጋነን አይደለም።
ስለዚህ የአሁኑ የዶር ደብረፅዮን በሊቀመንበርነት ተመርጠዋል ዜና የሴሬሞን ጉዳይ ብቻ ነው።ምክንያቱም እኛ በፊትም የድርጅቱ ሊቀመንበር እሳቸው መሆናቸውን ነው የሚናውቀው።
6 አዲስ ነገር ካለ የራያው ልጅ የጌታቸው ረዳ ስራ አስፈፃሚ ሆኖ መመረጥ ብቻ ነው።ሰውዬው ግዴለሽ ናቸው እንጅ በችሎታቸው የዚህ ትውልድ ተወካይ መሆን የሚችሉ ሰው ናቸው።እውነት ለመናገር እሳቸው የችሎታቸውን ያህል ጠንካራ እና ጠንቃቃ ሰራተኛ ቢሆኑ እና ህወሃት እሳቸውን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ ብመርጣቸው ድርጅቱ ለሪፎርም ተዘጋጅቷል ብዬ ቃሌን እሰጥ ነበር።ነገር ግን እሳቸውም ለህዋሃት ዓይነቱ ፖለቲካ ያንን ያህል ጥንቃቄ እና ጥንካሬ የቋጠሩ አይመስለኝም።ህዋሃትም ለዚያ አልተዘጋጀችም።ለወደፊቱ ግን ሁለቱም መዘጋጀት ይችላሉ።ያ የሚሆነው ኢህአዲግ ከዚህ ውጥንቅጥ ከተረፈ ወይም በዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና ህወሃት ሳልሳዊ ግምገማ ከተቀመጠ ብቻ ነው።ትዝ ይላችሁ ከሆነ ህወሃት ጥልቅ ታሃድሶ ብሎ የዛሬ ዓመት አከባቢ መቐለ ነበር።
ከዚያ ውጭ ለጊዜው የጌታቸው ረዳ የስራ አስፈፃሚ ሆኖ መመረጥ ከዶር ቴውድሮስ እጣፋንታ በብዙ መልኩ አይለይም።ተመሳሳይ ውጤት ሊኖረው ይችላል።
7 ቀጣዩ ጊዜ ለግንባሯ የግጥሚያ ጊዜ ነው።ህወሃት ከሞላ ጎደል ለመደራደር ሳይሆን ለመግጠም የመጨረሻ ተሰላፍ ይዞ ቀርቧል።አሸናፍ የመሆን እድሉ ግን እጅግ ጠባብ ነው።ምክንያቱም ይዞ የቀረባቸው ተጨዋቾ ላለፉት ረጅም ዓመታት ስጫወቱ የነበሩትን ነው።አሁን መሸነፋቸውን ሲያውቁ ከጨወታው ህግ ውጭ ፋዎል እንዳይነኩ ብቻ ይመከሩ።
በመጨረሻም የህወሃት የመጨረሻው ተሰላፊ ከእህት ፓርቲዎች ጋር ካለው ግጥሚያ በተጨማሪ ከመከላከያው ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ እንደሚኖረው አልዘነጋሁትም።እዚያ ላይ አንዳንድ ተጨዋቾች ጉዳት ደርሶባቸው ለዋንጫ ጨወታው ላይቀርቡ ይችላሉ ብለው አንዳንድ የህወሃት ደጋፍዎች ስጋታቸውን ከመግለፅ አልፈው የወዳጅነት ጨወታው እንዲቀር ፍርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል።
Filed in: Amharic