>

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም Vs ታማኝ በየነ  (ዳንኤል ሺበሺ)

 

አትጠራጠሩ! አሁንም እየሆነ እንዳለው ሁሉ፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ዓለም ሁሉ ወደ እርሳቸው፤ ወደ እነርሱ ሀሳብ ይገሰግሳል!!

ከጋሽ መስፍን ወ/ማርያም ጋር በመኖሪያ ቤታቸው በሞቀ ጨዋታ ላይ ነን፡፡ ያቺ የምወዳት ቡናዬ እየተቆላች አልፎ አልፎ አይኖቼ ወደ ሲኒዩ ያማትራል፤ አብዘኛው ቀልቤ ግን ከርሳቸው ጋር ነበር፡፡ ስለጤናቸው ሁኔታ ጥየቃ፣ ቀልዱ ፣ ትረባው ነቆራው … ቀጥሏል፡፡ በጨዋታችን መካከል የሀገሬ ኢትዮጵያ ስም በተደጋጋሚ ይነሣል፤ እንደየሙያው፣ እንደየዝንባለው፣ እንደየመደቡ … የአርቲስቱ፣ የቱጃሩ፣ የፖለቲከኛው፣ የሃይማኖተኛው ወዘተ ስም ይነሳል፤ ዕውቀታቸው ክብራቸውና ውርደታቸው ይታኘካል፣ ይዋጣል ይተፋል ወዘተ ፡፡

በዚህ መሃል የአርቲስትና አክቲቪስት #ታማኝ_በየነ ስም ተነሳ፡፡ ያለ ባሕርያቸው ፈጠን ብለው ጣልቃ ገቡና “ታማኝ በየነ” አሉ ፕሮፍ፡፡

ታማኝ’ኮ “ከአርቲስትነት ወደ ፈላስፋነት የላቀ” ሰው ነው አሉን፡፡ የጥልቅ ሀሳብ ባለቤት፤ የፍልስፍና ሊቅ ማለታቸው ነው ፡፡ የሚገርም አገላለጽ ነበር ፡፡
በአገላለጻቸው ተቃውሞም ሆነ ድምፀ-ተዓቅቦ አልገጠማቸውም ፡፡

ጋሽ መስፍን የሰው ልጅ በሕግ ፊትም ሆነ በተፈጥሮ (በሰው’ነት) ዕኩል ነው ብለው ፍጹም ያምናሉ፡፡ ለርሳቸው #ወርቅ የሆነም ያልሆነም ሕዝብ/ሰው የለም፡፡ የሰው ልጅ ከቁስ በላይ ነው ይላሉ፡፡ በጎሣና በቋንቋ ወይም በብሄረሰብ፣ በቆዳ ቀለምና በዓይን ፓትረን … መለያየት ምክንያት መናቆርን አጥብቀ፤ አጥብቀው ከነፍሳቸው ይጠላሉ፡፡ ጉራጌውን፣ ኦሮሞውን፣ ወላይታውን፣ ሶማሌውን፣ አማራውን፣ ስዳማውን፣ አፋሩን፣ ጋሞውን፣ ትግሬው፣ ሀዲያውን፣ ጋምቤላውን፣ ጥቁሩን ነጩን ወዘተ በእኩል የሚቀበል፤ በፍቅር የሚወድ ታላቅ ሰው፤ ታላቅ ምሁር ናቸው፡፡ ታላቅነታቸው ታዋቂ ወይም ፕሮፌሰር ስለሆኑ አይደለም፡፡ አዋቂም ስለሆኑ እንጂ፡፡ ለፕሮፌስርነት ለፕሮፌስርነትማ የም/ቦርዱ፤ የመከ.ኢታ …ማናቸው? አሉ አይደል!?

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ለሰው ልጅ መብትና ክብር የሚጮህ ኃያል ሰው፤ ሰመጉ መሥራች ናቸው፡፡ ሐቁ ይህ ነው፡፡ ከክልልዊነትና ከዘር አስተሳሰብ አጥር ያለፉ፤ እውነተኛውን የሰው ወሰነ-ልክ የደረሱ ሊቅ፤ ዛሬ በ87ኛ ዓሜታቸውም ባለ ብሩኀ ዐዕምሮ ባለቤት ናቸው፡፡
የምገርመኝ ነገር ፦ ምን አይነት ርግማን እንደሆን ባላውቅም፤ ይህች ሀገር ብዙ መልካምና አርቆ-አሳቢዎችን ያፈራች ሀገር ቢትሆንም፤ በአንፃሩ እነ ጋሽ መስፍንና መሰሎቹንም በድፍረት የሚሳደቡ ዜጎችን፤ በፊኛቸው ላይ የጠለዙ ዕውቄት “ማሰቢያ-አልባ ወታደሮችንም ጭምር ያፈራችም የተሸከመችም ሀገር ናት፡፡ የድሮ ነገር፤ ያለፈው ውሎታ በአንድ ጀምበር የሚደመስስበት፤ አዋቂዩ፣ ሀያሲዩ፤ አዛውንቱ አሮግቷ ወዘተ በጅምላ #ከባንዳ እኩል የሚሰደብበት ትውልድ ባለቤት የሆነች ሀገር ፡፡

ሰዎች ነንና ማናችም ብንሆንም እንደለመለምን አንኖርም፡፡ ሽምግልናን እንደ ኃጢዓት ውጤት አድርገው የሚያስቡ ትውልድን ያፈራች ሀገር፡፡ ሀገርን እየገደሉ ያሉ የሚከብሩባት፤ ሀገርንና ትውልድን ለማዳን ደፋ ቀና የሚሉና በጡረታ ዘመናቸውም ጭምር የሚለፉትንም ጭምር ክፏኛ የሚሰደቡበት ሀገሬ-ኢትዮጵያ፡፡

አሃ! ሀገርማ ሀገር ናት ምን ታደርግ? ችግሩ ከወደት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለማንኛውም “… የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ …” በርግጥም ትክክል ነበር፡፡
እኔ በግሌ ክብር ለሚገባው #ክብር ሰጥችያለሁ!ሰላም፡፡

Filed in: Amharic