>

ይህ ጋሻና ጦር ታሪክ አለው - ታሪካዊ ቦታም ተቀምጧል (ሉሉ ከበደ)

በካናዳ ቫንኮቨርና አካባቢዋ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በቁጥር አስር ሺህ እንደርሳለን።32 አመት እድሜ ያስቆጠረ በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ያለፈ የኮሚኒቲ ማህበርም አለን። ይህን የማህበረሰባችንን አሰባሳቢ ማህበር ለመምራት የሁለት አመት እድል ተሰቶን ከሁለት አመት በፊት ተመርጠን እየሰራን ሳለ ከክፍለ ግዛታችን ብሪትሽ ኮሎምቢያ ዋና ከተማ የመንግስቱ መቀመጫ ከሆነችው ቪክቶርያ የመንግስታችን ፓርላማ ተወካዮቻችን እንዴት ስራቸውን እንደሚያከናውኑ በአካል እንድንጎበኝ ግብዣ ለኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቀረበ።

አመራር አካላቱ ስለግብዣው ተነጋግረን ስናበቃ፤ እንግዲህ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ወጋችን በሚያዘን መሰረት ሰው ግብዣ ሲጠራ ባዶ እጁን ስለማይሄድ የስደት አገር መንግስታችን ምስጋናም ስጦታም ስለሚያስፈልገው ስጦታውም መሆን ያለበት ኢትዮጵያዊ ታሪካችንን የሚያስታውስ ረጅም እድሜ ሊቆይ የሚችል ነገር በመሆኑ ይህን ጋሻና ጦር በውድ ዋጋ ገዝተን አዘጋጀን።
ሜይ 6/2015 ሰላሳ የምንሆን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን ጠዋት ላይ ወደ ዋና ከተማችን ቪክቶሪያ ፓርላማ በመርከብ ጉዞ ጀመርን።ወንዱም ሴቱም ያገር የክት ልብሱን ለባብሷል ። ባንዲራችንን በርከት አርገን ይዘናል ። እህቶቻችን ስንቃችንን ወታቦ በሚያካክል ትልልቅ አገልግል ሰርተውልን ይዘናል። እናም መኪኖቻችንንም ጭምር ነበር መርከቡ የሚያሳፍረው። እኔ በበኩሌ ያንቀን ጉድ አየሁ። የምንኖርባት ከተማ ቫንኮቨር የወደብ ከተማ በመሆኗ ትልቁም ትንሹም መርከቦች ላይ ታች ሲተላለፉ ከማየት በቀር በመርከብ ተጉዤ አላውቅም። መኪኖቻችሁንም ይዛችሁ ኑ ተባለና ከፊሎቻችን መኪና ይዘን ስንሄድና መርከቡ ማቆሚያ ውስጥ እየነዳሁ ስገባ እዚያው መሬት ላይ ያለሁ መስሎኛል ። ለካስ መርከብ ነው ያን ሁሉ መኪና አዝሎ ባህር ላይ ቁጭ ያለው። አንድ ትንሽ ወረዳ የሚያህል ጉድ ላይ ተሳፍረን ጉዞ ቀጠለ። መርከቡ ሱቆች አሉት ሆቴሎች አሉት ህዝብ ይተራመስበታል ።
“ሉሉ ይህን ጋሻና ጦር አንተ ያዝ ” ተባልኩ። እኔም ጀነን አልኩና ጋሻና ጦሬን ይዤ መርከቡ ፎቆችም አሉት አናቱ ላይ ግልጥና ሜዳ ነው ሰዉ እዚያ ላይ እየተተራመሰ የባህሩን አድማስና አንዳንዴም ጥጋጥጉ ላይ ያሉትን መኖሪያዎች እየተመለከተ ይጓዛል። እኔ ከጓደኝቼ ጋራ ጋሻና ጦሬን ይዤ ስንጎራደድ ” መርከብ ሰመጠ ሲባል ይሄ ነው እንዴ የሚሰምጠው ?” አልኩና ጠየኳቸው። “አዎና!” አሉኝ። “ባህሩስ ምን ሆዳም ቢሆን ነው ይህን የሚያህል ጉድ ውጦ ዝም የሚለው” አልኳቸውና ተሳሳቅን። እንዲሁ እየተቀላለድን ከአንድ ሰአት ተኩል ጉዞ በኋላ ቪክቶሪያ ደረስን።
ፓርላማው ስራ የሚጀምርበት ሰአት ገና ስለ ነበር ወደ ግቢው ከመግባታችን በፊት እዚያው አዳራሹ ያለበት ዙሪያ እየተዟዟርን አካባቢውን ስንጎበኝ ጋሻና ጦሩን ልብሴን ጨምሮ ያገሬው ጥያቄ እየተከታተለ መጣብኝ። የጠበኩት ነገር ስለነበር ለማስረዳት ተዘጋጅቻለሁ። ” ከየት አገር ነህ? ጋሻና ጦሩን ለምን ያዝክ? የለበስከው ልብስ የየት አገር ነው?” በየቦታው ላቆመኝ ሁሉ መልስ ከመስጠቴ በፊት አንድ ጥያቄ እጠይቅ ነበር።ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር የሚያውቁት ነገር ካለ መጀመሪያ ትንሽ እንዲነግሩኝ። ሶስት ነገሮችን በደንብ ያውቃሉ። የት ቦታ እንዳለች የማያውቃትን ጨምሮ። ጦርነት፥ርሃብና ሩጫ። ሩጫን በተመለከት በድሜ ገፋ ያሉት አበበ ቢቂላን፥ ሀይለስላሴን ይጠራሉ ፤ ወጣቶቹ በብዛት ሃይሌን አና ደራርቱ የሚል ስም ይጠቅሳሉ። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ታሪክ ያ ብቻ አለመሆኑን ፤ የጥንታዊ ስልጣኔ ታሪካችንን ፤ የሶስትሺህ ዘመን የነጻነት ታሪካችንን ፤ የሰው ልጅ ዘር መገኛ ምድር ባለቤት መሆናችንን አስረዳና ጋሻና ጦሩ አባቶቻችን ነጻነታቸውንና ሉአላዊነታቸውን ሲያስከብሩ የኖሩበት ጦር መሳሪያ መሆኑን ከነገርኳቸው በኋላ ለፓርላማው ልናበረክተው ያመጣነው መሆኑን አረጋግጥላቸዋለሁ። አንዳንዶች አብረውኝ ፎቶ ይነሱና አመስግነው እንለያያለን።
በንዲህ ያለ ሁኔታ ቆይተን ፓርላማው ስራ ሊጀምር ነውና ለመግባት ተዘጋጁ ስንባል መግቢያው ላይ በሰልፍ ሆነን በስነስርአት ወደተዘጋጀልን ስፍራ አንዲቷ እየመራችን ገብተን ቁኝ አልን። አዳራሹ እንደትያትር ቤት የፓርላማው አባላት ቁልቁል የሚታዩበት ከፍታ ስለነበረው ቁልቁል ሁሉንም እናያቸው ነበር። እና አንዲቷ ያካባቢያችን ተወካይ ለፓርላማው አባላት የኛን መገኘት ካበሰረች በኋላ ስለሃገራችን የነጻነት ታሪክ በጽሁፍ ለፓርላማው ካነበበች በኋላ እንዲወክሉን የመረጥናቸው የየአካባቢያችን ተወካዮች ሁላችንንም በየስማችን እየጠሩ መምጣታችንን ካመሰገኑ በኋላ ፓርላማው ስራውን የሚጀምረው በጸሎት ነበረና በዚያን ሰሞን በሊቢያ አረመኔዎች ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ የተቀሉ 28 ኢትዮጵያውያንን በማንሳት ጸሎት ተደርጎላቸው ስራ ተጀመረ።
በኢኮኖሚው በፖለቲካው በማህበራዊ ኑሮው ጉዳይ በለቱ የተያዙ አጀንዳዎችን በየተራ እያነሱ መንግስቱን እየመራ ያለው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ አስገራሚ ነጻነት የሞላበት ክርክራቸውንና ጭቅጭቃቸውን ቀጠሉ። የክፍለ ግዛታችንን ጠቅላይ ሚኒስትር ተቃራኒዎቿ ታቅዷል አልተሰራም እያሉ ነገሮችን እየመዘዙ ከግራ ከቀኝ በጥያቈና በትችት ሲያርገበግቧት እሷና የፓርቲዋ ሰዎችም እያደረጉ እየሰሩ ያለውን ነገት ለማስረዳት ለማሳመን ሲረባረቡ ስናይ በሃገራችን ኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እያስታወስን ሃዘንም ቅናትም ተቀላቅሎብን ቆየን። እኔን ያሳዘነኝ ነገር በረት ውስጥ ከተሰበሰበ ከብት ምንም ልዩነት የሌላቸው ያገራችን ፓርላማ ተወካዮች ፤ ያሁሉ ሰው እወክለዋለሁ ስለሚለው ህዝብ አንዲት ነገር ሳያነሳ የፓርላማ ዘመኑን በሙሉ ለወያኔ ጌቶቹ እንዳጨበጨበ ያን ሁሉ ለደሞዝ የሚከፈለውን የሃገር ሀብት ጨርሶ መውጣቱ ነው።
እኔ በግሌ በዚያን ቀን የፓርላማ ውሎዬ የተማርኩት ነገር የህዝብ ተወካዮች እንዴት አንዱ ሌላውን እንደሚቆጣጠረው፥ እንደሚያስፈራውና ከስህተት የጸዳ ጥሩ ስራ ለሃገር እንዲሰራ እንደሚያደርገው ነው። ሃገራችን ፓርላማ ውስጥ ያለው ነውር በየትም አለም ያለ ግን አይመስለኝም።
በንዲህ ያለ ሁኔታ የፓርላማው ስራ እስኪጠንናቀቅ ቆየን።በኋላ የምግብ ግብዣ ተሰናድቶልን ኖሮ ጋሻ ጦሬን ለጊዜው ካስረከብኩበት የደህንነት ቢሮ ወሰድኩና ወደ ምግብ አዳራሽ ሄድን። አብዛኛዎቹ የፓርላማ ሰዎች ወደኛ መጡ። ተበላ ተጠጣ ። ብዙዎች ጋሻና ጦሩን እንደያዝኩ ፎቶ ተነሳን። ጓደኛዬ ደበበ ጉሉ “እባክህ አንድ ጊዜ ፉከራና ሽለላውን አስነካው ” እያለ ይጎተጉተኝ ነበር። ድንገት ይደነባብሩና ሌላ ታሪክ ይፈጠራል ብየ በጀ አላልኩትም። እናም መጨረሻ ላይ ስጦታችንን ሊቀመንበራችን በረከት በፓርላማ ተወካያችን በኩል ለምክር ቤቱ እንዲሰጥልን ጋሻውን ጦሩን ባንዲራችንን በስነስርአት አስረከብን። አሁን ይህ ጋሻና ጦር በፓርላማው አዳራሽ ግርግዳ ላይ በኢትዮጵያ ባንዲራ አጊጦ ተሰቅሎ እየተጎበኘ ነው። ለዘለአለም አይነሳም። ዛሬ የብሪትሽ ኮሎምቢያ ፓርላማ አዳራሽ ውስጥ የገባ ሰው የጀግንነት አርማችንንና ባንዲራችንን ያየዋል። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

Filed in: Amharic