>

የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ማር እስከጣፍ ዘፈን በአማራ ክልል አለመዘፈኑ ውዝግብ አስነሳ (ወንድወሰን ተክሉ)

የእውቁ አርቲስት ቴውድሮስ ካሳሁን[ቴዲ አፍሮ] ማር እስከጣፍ ዘፈን በአማራው ክልል እንዳይዘፈን የተከለከለበት ሁኔታ ፍትሃዊ አይደለም በማለት አንድ የምክር ቤት አባል ጥያቄ ማንሳቱ ተሰማ።
አቶ መርሃ ጽድቅ የተባሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል “ለምሳሌ የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ጣፍ እስከማር ዘፈን ስለጎጃምና ስለ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ የሚተርክ ድንቅ ዘፈን ሆኖ ሳለና አቶ ሀዲስ ዓለማየሁም የጎጃም ተወላጅ ሆነው ሳለ የአርቲስቱ ዘፈን ለምን እንደማይዘፈን አይገባኝም” ሲሉ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባሉበት ጥያቄ አቅርበዋል።

የደራሲ ሀዳሲ ዓለማየሁን ፍቅር እስከመቃብርን ታሪክ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ነው ይበልጥ ነፍስ የዘራበት ያሉት አቶ መርሃ ጽድቅ “ዛሬ ደግሞ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ዳግሞ እነጉዱ ካሳን፣ሰብለወንጌልን እና የጎጃምን ስፍራ እየጠቀሰ ያቀረበው ድንቅ ዘፈን ሆኖ ሳለ የአርቲስቱ ዘፈኖች ለምን በጎጃምና በአማራ ክልል እንደማይዘፈን ሊገባኝ አልቻለም “ሲሉ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የተሰኘ አልበሙን በባለፈው ፋሲካ ላይ ለአድማጭ ጆሮ ያደረሰው እውቁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ስራዎቹን በኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝብ እንዳያቀርብ በመንግስት በኩል እገዳ እንደተጣለበት የሚታወቅ ሲሆን የአልበሙን ምርቃት ብሎ በሂለትን ያዘጋጀውን ፕሮግራም እንካን በመጨረሻ ሰዓት ላይ እንደታገደበት ይታወቃል።

አርቲስቱ በ5ኛውና ኢትዮጵያ በተሰኘው አልበሙ በዓለም የሙዚቃ ቻርት ላይ በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠና የዓለም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ስራን ለህዝብ ጆሮ ማቅረብ የቻለ ሆኖ ሳለ በሀገሩ ግን በመንግስት በኩል እየደረሰበት ያለው ተጽእኖና በደል ብዙዎችን እንዳስገረመ ይታወቃል።

የአማራ ክልል መስተዳድር የመንግስት መገናኛ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለምክር ቤቱ አባል ጥያቄ ሲመለሱ “የአርቲስት ቴዲ አፍሮ ዘፈን በተለይም ማር እስከጣፍ መከልከሉን አላውቅም ሆኖም መከልከል የሚገባው ዘፈን አይደለም “በማለት ጉዳዩን እንደሚያጠሩ ከገለጹ በሃላ “የክልሉ መገናኛ ብዙሃን በነጻነት ሊያስተናግዱ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እውቁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን አልበም በአሜሪካን የተለያዩ እስቴቶች ተዘዋውሮ ለማሳየት ፕሮግራም ማውጣቱን አርቲስቱ ካሰራጨው ዜና የጉዞ ፕሮግራሙ ላይ መረዳት ተችላል።

Filed in: Amharic