>
5:13 pm - Sunday April 18, 6060

በኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራው መስተዳደር  የት ይደርስ ይሆን? (አፈንዲ ሙተቂ)

በተፈጥሮዬ ተጠራጣሪ (Skeptic) ነኝ። የአሰላሳይነት ባህሪም ያጠቃኛል። በመሆኑም ሌሎች በቀላሉ አምነው የሚቀበሉትን ነገር በቶሎ ማመን ይከብደኛል። በዚህም የተነሳ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር በክልሉ ታሪክ ባልታየ ሁኔታ የሚወስዳቸውን ድፍረት የተመላባቸውን እርምጃዎች ከልቡ የሚፈጽማቸው መሆናቸውን ለመቀበል ስቸገር ቆይቻለሁ። በተለይም የኦሮሞ ህዝብ “ጎበና” እያለ ሲተቸው የነበረው ኦህዴድ በአጭር ጊዜ ራሱን ቀይሮ ከተጽእኖ ነፃ በሆነ መንገድ ባለፉት አራት ወራት ያየናቸውን ታላላቅ ድርጊቶች ይከውናል ለማለት ሳይቻለኝ ቆይቷል።

ይሁንና ተጠራጣሪነትም ድንበር አለው። አንዳንድ መለስተኛ ጉዳዮች “ለይስሙላ የተደረጉ ናቸው” ብሎ መቀበል ቢቻልም ብዙዎችን የሚነካኩ ከበድ ያሉ ገቢሮችን ግን ለማስመሰል የተደረጉ ናቸው ማለቱ ይከብዳል። ለምሳሌ መስተዳድሩ በዚህ ሳምንት የወንጀል ተጠርጣሪዎችንና ኮንትሮባንዲስቶችን ወደ ህግ ለማቅረብ ያሳየው ድፍረት በጣም አስደናቂ ሆኖ ተገኝቷል።
—-
እርግጥ ኦህዴድ ከጥንት አቋሙ እየተለወጠ መሆኑን የተረዳነው ከሁለት ዓመት በፊት አቶ አባዱላ ገመዳ ሚሚ ስብሐቱን “ኦህዴድ ነፃ የሆነ ድርጅት ነው፣ እናንተ ግን እንደ ጉዳይ አስፈፃሚ ትመለከቱታላችሁ። ይህንን የተንሻፈፈ እይታ ቀይሩት” ባሉበት ጊዜ ነበር። በዚያው ሰሞን ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ “ማስተር ፕላኑ ወርቅ የሚያዘንብ ቢሆን እንኳ የኦሮሞ ህዝብ አልፈልገውም ካለ አይተገበርም” በማለት አስገራሚ ንግግር ተናግረው ነበር።

በክረምት ወር 2008 አቶ አባዱላ ገመዳ የአማራ ክልልን በጎበኙበት ጊዜም “የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን የመንግስትን በጎ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ድክመቶቹንና ጥፋቶቹን በማሳየት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሌሎች የመንግስት የሚዲያ ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው” በማለት እነ ሚሚ ስብሐቱን ያንጫጫ መግለጫ መስጠታቸውም ያልተጠበቀ ነበር።

ከነዚህና ከሌሎች ሁኔታዎች እንደተረዳነው ኦህዴድ ከማዕከል የሚመጡ ትእዛዞችን እንደ ቀድሞው በይሁንታ ተቀብሎ በእሺታ በመፈፀም ፈንታ “ለምን?” ብሎ የመጠየቅን ልማድ አምጥቷል። አሁን ስልጣኑን የያዘውና በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር “ለምን” ብሎ መጠየቅ በጀመረው አዲሱ የኦህዴድ ኃይል የተመሰረተ ነው።

የኦቦ ለማ መገርሳ መስተዳድር ወደ ስልጣን በመጣ ሰሞን በፕሮፓጋንዳ ስራዎች ላይ ነበር ያተኮረው። በስድስተኛው ወሩ ግን ከላይ ያነሳኋቸውን ድፍረት የታዩባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል። በጥቂት ወራትም ውስጥ ከኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጭምር ከፍተኛ አድናቆት አትርፏል።

በአቶ ለማ የሚመራው መስተዳድር በኦህዴድ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣቱን አብዛኛው ሰው አምኗል። እኔም ይህንን እምነት ከሚጋሩት አንዱ ሆኛለሁ። የለውጡ መነሻና መድረሻ ወደፊት በታሪክ የሚጠና ይሆናል። በበኩሌ ግን በአካሄዱ ገፍቶበት የሚደርስበትን ደረጃ ለማየት ከሚጓጉት ነኝ። ፈጣሪ ከቡዳና ከክፉ ዐይን እንዲያወጣውም መልካሙን ሁሉ እመኝለታለሁ።

Filed in: Amharic