>
5:13 pm - Saturday April 19, 8177

ፖለቲካ ልክ እንደ ቼዝ ጨዋታ ነው። ጠጠሮችህን  በጥንቃቄ ካልመራሃቸው ተሸናፊ ትሆናለህ! (ዮናስ ሃጎስ)

ሮበርት ሙጋቤ ሚስቱ ግሬስ ሙጋቤን ወደ ስልጣን ለማምጣት ሙከራ ባያደርግ ኖሮ ከስልጣኑ ንቅንቅ አይልም ነበረ!
***
ፖለቲካ ልክ እንደ ቼዝ ጨዋታ ነው። ጠጠሮችህን ስታንቀሳቅስ ወደ ትክክለኛው መስመር ካልመራሃቸው የጨዋታው ተሸናፊ ትሆናለህ።
***
ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ንግስቲቷን ጠጠር ትክክለኛ ወዳልሆነ አቅጣጫ አንቀሳቅሶ ጨዋታውን የመሸነፍ አደጋ ውስጥ ቢገባም ቅሉ የ37 ዓመት የመሪነት ጉዞውና የትግል ታሪኩ ባደረጉለት አስተዋፅዖ ጨዋታውን በአቻነት ለማጠናቀቅ የቻለ ምናልባትም ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዳንዔል አራፕ ሞይ ወዲህ ሁለተኛው የአፍሪካ መሪ ነው።
*

ኬንያን ለ27 ዓመታት በብቸኛነት የመራው ዳንዔል አራፕሞይ ባሁኑዎቹ ተቀናቃኞች በነራይላ ኦዲንጋና ኡሁሩ ኬንያታ ግፊት እንዲወርድ ሲደረግ በስልጣን ዘመኑ ያፈራቸውን ሐብቶች ላይነጠቅና ለሰራቸው ወንጀሎች በሕግ ላይጠየቅ ውል ተዋውሎ ነው ከስልጣኑ የወረደው። በአሁኑ ሰዓት በኬንያ ውስጥ በኃብት ደረጃ አንደኛ ሲሆን የሚኖረውም ለአንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በሚገባ ክብር ጥበቃ ከመንግስት ተመድቦለት ነው።
*
ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ደህና እስከመጨረሻው የሕይወት ዘመኑ ስልጣኑን መጨረስ የሚችልበትን እድል ሚስቱን ወደ ፖለቲካው ዓለም ለማምጣት ባደረገው ሙከራ የስልጣን ዘመኑ ባጭሩ (37 ዓመት ምናላት? ምፅ!) ተቀጭቶበታል። የዚምቧቤ ሕዝብ ሐገሪቱ ያለችበትን የኢኮኖሚ ክራይሥ አጥብቆ ቢጠላውም ቅሉ ከነጮች ቀጥተኛና እጅ አዙር አገዛዝ ነፃ ባወጣው ሙጋቤ ላይ የሚጨክን አንጀት ሊኖረው አይችልም። እናም በቅርቡ መሞቱ የማይቀረውን ሙጋቤን ለመታገስ ሰፊ ትዕግስት ነበረው። ሆኖም ሙጋቤ ትውልደ ናሚቢያ የሆንችውን ግሬስን ወደ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ለማምጣት መጥፎ እንቅስቃሴ በመጫወቱ ሕዝቡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ከሙጋቤ አገዛዝ ራሱን ለማላቀቅ ችሏል።
***
ሙጋቤ ታድያ እንዲሁ ወደቤቱ አልተሸኘም። ልክ እንደ አራፕ ሞይ በስልጣን ዘመኑ ያፈራቸው ሐብቶች እንደማይነኩበትና በምንም ዓይነት ወንጀል ተከሦ ፍርድ ቤት እንደማይቀርብ ዋስትና ካገኘ በኋላ ነው ዛሬ ስልጣኑን ለመልቀቅ የተስማማው። በውሉ መሰረት ሙጋቤ በዚምቧቤ ውስጥም ሆነ ከዚምቧቤ ውጭ ያሉት ሐብቶቹ አይነኩበትም። የሚኖረውም ልክ እንደ ፕሬዝዳንትነቱ ዘመን በሚደረግለት ጥበቃ ውስጥ ሲሆን ሲሞትም ለአንድ ፕሬዝዳንት በሚደረግ ክብር ይቀበራል። Win/Win situation ይሉሃል ይኸው ነው።
***
ኢትዮጵያስ መሪዎቻችንን እንዲያው የያዛችሁትን ይዛችሁ ከሐገር ውጡልን የሚል ጦር መሪ መቼ ይነሳልን ይሆን?
Filed in: Amharic