>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9048

ከነስዬ ውድቀት መማር ተገቢ ነው (ያሬድ ጥበቡ)

እኔ እንደሚመስለኝ ወያኔ ስብሰባ የሚያራዝመው አዲስአበባ ለመመለስ ስለፈራ ሊሆን ይችላል ብለን መጠርጠር ተገቢ ነው ። ዘገባው እንደሚለው የወያነ መሪዎች መወያየት አቅቷቸው ተራ ዘለፋና ስድብ ውስጥ ከገቡ፣ የቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እነሱን ቁጭ ብለው መጠበቅ የለባቸውም ። ወያኔ መቐለ ባለበት ሰአት ሶስቱ ድርጅቶች ተገናኝተው ለወቅቱ የሚመጥን እርምጃዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ። ካስፈለገ ወያኔ የሌለበት መንግስታዊ ሥልጣንን በጊዜያዊነት ወይም በሽግግር መልክ እስከማደራጀት እንደ አማራጭ ማየት ይኖርባቸው ይሆናል ። የሃገር ኢኮኖሚ እየዳሸቀና የአመራር ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ ባለበት ሁኔታ ዝም ብሎ መቀመጥ ኋላ ውድ ዋጋ ያስከፍላል ። ከጎንደር አዳራሽ ከደረሱን ዘገባዎች አንዱ፣ አቦይ ስብሃት “ለምን ከኦሮሞዎች ጋር መገናኘት አስፈለጋችሁ” ብለው ጠየቁ የሚለው እውነት ከሆነ ፣ ወያኔ አዲስ አበባ ሲመለስ እነ ለማን ለመቅጣት እንዳሰበ ያሳብቅ ይመስለኛል ። ታዲያ ዝም ብሎ ተቀምጦ መጠበቁ ምን የሚሉት ነው? ከነስዬ ውድቀት መማር ተገቢ ነው ። ድርጅታዊ ጉባኤ አካሂደን በህጋዊ መንገድ እናወርደዋለን ብለው ሲቀናጡ ነው፣ ህገወጥ በሆነ የካድሬ ስብሰባ አስወግዞ ደህንነቱንና መከላከያውን በማዘዝ መለስ ጉድ ያደረጋቸው ። ማን ድርጊትህ ህገወጥ ነው ብሎ መለስን አስቆመው? ማንም ። የኢህአዴግ የጥገና መሪዎች ከራሳችሁ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ተማሩ ። ነገ ጌታቸው አሰፋ ከመቐለ ሲመለስ አንድ አስራችሁን ቢረሽን ትግሉ የሚቀጥል ይመስላችኋል? ኦሮሚያ በወጣት አመፅ ለተወሰኑ ወራቶች ይታመስ ይሆናል ሆኖም የተጀመረው ለውጥ ለጊዜውም ቢሆን ይገታል ። አርቃችሁ አስቡ ። በፅናትም ቁሙ ። የሞትን ፅዋም ዛሬውኑ ጭልጥ አድርጋችሁ ጠጡ ። ሞትን እንደመቀበል የሰውን ልጅ አርነት የሚያወጣ የለም ። አይዟችሁ!
Filed in: Amharic