>

የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ትግልና የኦህዴድ/ብአዴን ሚና (ተማም አባቡልጉ - የህግ ባለሞያ)

“ኢህአዴግ ማኪያቬላዊ ድርጅት ነው። ቃል ለኢህአዴግ የዕምነት ዕዳ አይደለምና የማያደርገውን የሚልና በተግባር ፈንታ አባባል (rhetoric)ን የተካ ነው”

” በአባዱላ ገመዳ ወይም በአቶ ለማ መገርሣ፣ የዛሬ ባህሪ ድርጊት እና በአቶ ሙክታር ከድር፣ በአቶ ሐሰን አሊና በአቶ ሙክታር ከድር የያኔው ባህሪና ድርጊት መካከል ልዩነት አለ ብዬ መቀበል ያቅተኛል”

“የአማራ ወዘተ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው”

¤¤¤

ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ኢህአዴግ ነው፣ እሱም አባልና አጋር ድርጅቶች አሉት። ኢህአዴግ አንድ ድርጅት ነው፣ ኦህዴድ ኢህአዴግ ነው። ብአዴን ኢህአዴግ ነው። በኦሮሚያ ክልል ኦህዴድ፤ ብአዴን በአማራ ክልል በኢህአዴግ ስም ምርጫ አሸንፈው በክልል የእነሱ፤ በብሔራዊ ደረጃ ደግሞ ኢሕአዴግ መንግስት እንዲመሰርት አስችለውታል። ወይም “እንደዚህ ነው ተብለናል” ስለዚህ በኦሮሚያ ክልል ያለው መንግስት ኢህአዴግ የመሰረተው መንግስት ነው፣ አሁንም ያለውን ስርዓት የመሰረተው ኢህአዴግ ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ተቋማት የመሰረተው ኢህአዴግ ነው፣ የኦሮሚያ ፖሊስ የኢህአዴግ ፖሊስ ነው።

አንድ ድርጅት መግለጫውና ማንነቱ ወይም ምንነቱ የሚታወቀው (የሚወሰነው) በዓላማው ነው፣ ድርጅቱ ዓላማውን ነው፣ የኦህዴድ ዓላማ የኢህአዴግ ዓላማ ነው።

“ኦህዴድ ኢህአዴግ ነው” ስንል የዓላማ አንድነት አላቸው ማለታችን ነው። “ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የዓላማ አንድነት አላቸው።” ስንል “የሕወሃትና የኦህዴድ ዓላማ አንድ ነው” ማለታችን ነው። የኢህአዴግ አባል ድርጅትነታቸው የዚህን የዓላማ አንድነት ማስጠበቂያ ዘዴም (መንገድም) ነው፣ ኢህአዴግ የእኩሎች ድርጅት እንዳይሆን የተደረገበት ብዙ ሥነ-ልቦናዊና ቁሳዊ መንገዶች አሉ። ስለዚህ ዛሬ የምለው የለም።

አንዳንድ የኦህዴድ አባላት በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ይህንን አሰራር ላይወዱ ይችላሉ፣ በህወሃት ባህሪ ሊበሳጩም ይችሉ ይሆናል፣ የኦህዴድ መሪዎች ስለህወሃት እና ስለኢህአዴግ ተበሳጭተው ሲናገሩ ልንሰማቸው እንችላለን።
ይህ ማለት ግን ከህወሃትና ከኢህአዴግ ጋር የዓላማ አንድነታቸውን ትተዋል (ቀርቷል) ማለት አይደለም።

እነዚህ የኦህዴድ መሪዎች የህወሃትን የኢህአዴግን አላማ እያስፈጸሙ አይደሉም ማለትም አይሆንም፣ ምክንያቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ ከህወሃት ጋር አንድና ተመሳሳይ የሆነውን የኢህአደግ ዓላማ የሆነውን የራሴን የሚለውን ዓላማ የማስፈጸም ግዴታ አለበትና ነው። ድርጅት ዓላማው ነውና ኦህዴድ የሚያስፈጽመው ዓላማ ከሌለው ድርጅትነቱ ይቀራል። የሚያስፈጽመው አሁን ያለው ዓላማው ደግሞ የኢህአዴግ ዓላማ ነው። የኢህአዴግ ዓላማ ደግሞ የህወሃት ዓላማ ነው።

ኦህዴድ ከኢህአዴግ አባልነት ወጥቶ አሁን ያለውን የፖለቲካ ዓላማውን እስካልቀየረ ድረስ፤ አሁን ያለውና የዛሬ አስር ዓመት የነበረው አንድና ተመሳሳይ ድርጅት (ኦህዴድ) ነው። አልተቀየረም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ድርጅት ተቀይሯል የሚባለው ዓላማውን ሲቀይር ነውና በዚህ ረገድ ከህወሃት ጋር የተጣሉ የሚመስሉት አቶ ለማ የሚመሩት ኢህዴድ ከአቶ ኩማና (ደመቅሳ) እና ሙክታር (ከድር) ይመሩት ከነበረው ኦህዴድ የተለየ አድርገን መውሰድ አንችልም።

ድርጅት ግለሰብ አይደለም፣ ግለሰብም ቢሆን አመለካከቱን ለውጧል ለማለት የምንችልባቸው መንገዶች አሉ። “አንድ ድርጅት አመለካከቱን ለውጧል” ለማለት አሰራሩን ብቻ ሳይሆን ዓላማውንም ለውጦ ማየት ይኖርብናል። ኦህዴድ ከኢህአዴግ አልወጣም፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙንም አልለወጠም፣ አላሻሻለም። አቶ ለማ ኦህዴድን የሚመሩት፣ ኦህዴድ ፕሮግራሙን እንዲያስፈጽም በፕሮግራሙ መሰረት ነው። አዲስ ባወጡለት ፕሮግራም አይደለም።

ኢህአዴግ ማኪያቬላዊ ድርጅት ነው። ቃል ለኢህአዴግ የእምነት ዕዳ አይደለምና የማያደርገውን የሚልና በተግባር ፈንታ አባባል (rhetoric)ን የተካ ነው። አቶ ለማም እንደኢህአዴግነታቸው የኢህአዴግን ዓላማ ለማሳካትና ድርጅታቸውን ለመታደግ አስፈላጊ ያሉትን አሰራርና አቀራረብ ተግባራዊ እያደረጉ ነው ተብሎ መታመን አለበት፤ ይህ መርህ ነውና።

ከዚህ መርህ በተለየ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ማመን የምንጀምረው፣ ኦህዴድ ከኢህአዴግ አባልነት ወጥቶ አሁን የያዘውን የፖለቲካ ፕሮግራሙን ሲቀይር ብቻ ይሆናል። የፖለቲካ መተጣጠፍና የራስ ያደረጉትን የኢህአዴግን አላማ ለማሳካት ከህዝብ የመብት ጥያቄ ማዕበል ሊጠብቁት በተጣጠፉ ቁጥር እኛ ኢትዮጵያኖች አብረን ዥዋዥዌ አንሰራም። መስራትም አይጠበቅብንም። ከህዝብ ትግል አንጻር የአደናቃፊነት ሚናቸውን ስለመለጠባቸው የማስዳት ሽክም ያለባቸው እነኦህዴድ ናቸው።

እኔ የኢትዮጵያ ህዝብን ደህንነት የራሴ ደህንነት አድርጌ እቀበላለሁ፣ አንድ የህዝቡ አንድ አካል ስለሆንኩም በህዝብ ላይ የሆነው ሁሉ በራሴም ላይ ይሆናል። ሀበሻ ሲመታ ያመኛል፤ ምክንያቱም እሱን ሲመቱ እኔንም፣ እኔንም ሲመቱ እሱንም ቢሆን እንጂ ሌላ ሊሆን ስለማይችል ነው። ህዝቤን ማታለል እኔንም ማታለል ነው። ባልተለወጡ አካላት የሚመራ የለውጥ ሂደት፤ ውጤቱ ክህደት ባይሆን እንኳን ታጥቦ ጭቃ ይሆናልና እንጠይቃለን።

አባዱላ ገመዳ ከመንግስት ስልጣናቸውና ከኢህአዴግነታቸው ቢወጡ (ቢለቅቁ) ምንም ማለት የሚሆነው ኦህዴድን ከኢህአዴግ አባል ድርጅትነትና ኢህአዴግ ከመሰረተው መንግስት ጥምረት አብረው ይዘው ከወጡ ብቻ ነው። ካልሆነ ግን በአባዱላ ገመዳ ወይም በአቶ ለማ መገርሣ፣ የዛሬ ባህሪና ድርጊት እና በአቶ ሙክታር ከድር፣ በሐሰን አሊና በአቶ ኩማ ደመቅሳ የያኔው ባህሪና ድርጊት መካከል ልዩነት አለ ብዬ መቀበል ያቅተኛል። ከኦህዴድ መሪዎች ተጨባጭ ተግባራዊና ሕጋዊ የሆነ ማስረጃ እንፈልጋለን፣ አለበለዚያ “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” እንዳሉቱ አይጦች አድርጉ ብለን ለህዝባችን ያለመንገር ክህደት ይመስለኛል።

የኦሮሚያ ፖሊስ የኢህአዴግ ፖሊስ ነው። ህወሃት በኢህአዴግ በኩል ኦሮሚያን ሲገዛ የነበረውና ያለው በኦህዴድ በኩል ነው። ኦህዴድም ከህወሃት ጋር አንድ የሆነውን ዓላማውን በኦሮሚያ ላይ ተግባራዊ እያደረገ የነበረው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኖና ስለሆነ ነው።

ህወሃት ከኦህዴድ ጋር የዓላማ አንድነት እስካለው ድረስ የኦሮሚያ ገዥ ተባለ አልተባለ ኦሮሚያን እየገዛ የመሆኑን ሁኔታ አይለውጠውም። የኦህዴድ አባላት ሰደቡት አልሰደቡት አገዛዙ ላይ ለውጥ አያመጣም። እነአቶ ለማ የህዝብ ፍቅር ካላቸው ለህዝቡ ጥያቄ መልስ በመስጠት እንዲያሳዩን እንሻለን።

የኦሮሞ ህዝብ አልፈልግም ያለው ጭቆናን ነው። የዛሬውን ጭቆና የሚወክለው ደግሞ ኢህአዴግ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ጸረ-ጭቆና ትግሉ ጸረ-ኢህአዴግ ነው ወይም ይሆናል ማለት ነው። የኦሮሞ የፀረ-ጭቆና ትግል ፀረ-ኢህአዴግ ከሆነ ፀረ-ኦህዴድም ነው። ስለሆነም ትግሉ በእሱ ላይ ያነጣጠረ ድርጅት የሆነው ኦህዴድ የህዝቡን ፀረ-ጭቆና ትግል ይመራል ማለት በራሱ ላይ የሚደረግን ትግል ይመራል ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ለህዝቡ ጥሩ ነገር አይስመለኝም። ትግሉን ኦህዴድ ከመራለት የምንዋጋው የሌላኛው ጦር ፊታውራሪ ጦራችንን ይምራልን (እየመራልን ነው) ከማለት አይለይም። ካልሆነ ግን በተግባር የተለወጠ መሆኑን በተግባር አይተን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ይሆናል።

ኦህዴድ ከኢህአዴግ አባልነት ወጥቶ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ካልለወጠ እሱን ሕዝባዊ አድርጎ መቀበል በሴራ ተጠልፎ ከመውደቅ ሌላ አይሆንም። እኔ ጭቆናን እጠላለሁ። ወንድሜ ቢነግስና ጨቋኝ ቢሆን አልቀበለውም። እኔ በግሌ ከሙክታር ከድር ጥል የለኝም፣ ኦህዴድን የማንቀበለው በማን በመመራቱ ወይም በመሪዎቹ ንግግር ሳይሆን፤ በፕሮግራምና ድርጊቱ ነው። ለማ ህዝቡን መሳደብ መተዉ ጥሩ ቢሆንም በቂ አይደለም። “ana natuun beelahin basu” (አናኛቱን ቤላ እንባሱ) እንዲል ኦሮሞ። /እኔን ይብላኝ ከረሃብ አያወጣም እንደማለት ነው/

የኦሮሞ ህዝብ ተሰልፎ እየጮኸ ይዋል፣ ለጩኸቱ ምላሽ ባንሰጥም፣ በአደባባይ የረሸኑትን ልንከላከልለት ባንችልም “ለምን መታችሁት ወይም ህዝቡን የመታው ቀይ የለበሰ ጦር ነው” ስላልንና ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ስለተናገርን ህዝባዊ እንሆናለን የሚለውን የሰሞኑን የኦህዴድ ባለስልጣኖች አካሄድ አልበቀለውም። ያላደረጉት፤ ህዝቡን ያልተከላከሉት ስላልፈለጉ ወይስ ስላልቻሉ ነው?

የምራቸውን ከሆነ፣ እነሱ መንግስትና አስተዳዳሪ (ገዥ) በሆኑበት ምድር፣ ማንም መጥቶ ህዝብን እንዳይገድል የማድረግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን አውቀው ድርጊቱን ማስቆም ነበረባቸው፣ አለባቸውም። ካልቻሉ ደግሞ ስልጣን የላቸውም ማለት ነውና ይህንኑ ለህዝብ በግልጽ ነግረው ከቦታው ዞር ማለት ወይም ኦህዴድን ከኢህአዴግና ከመንግስቱ በማስወጣት ለእነሱ እውነተኛ አቅም በሚሰጥ ሁኔታ ማደራጀትና መደራጀት አለባቸው። አቅም የሌለው መንግስት አሽከር አይደለሁም ቢል አሽከርነቱ አይቀርም።
ይህንን ካላደረጉና እስላካደረጉ ምንም የተለየ ነገር እያደረጉ አይደለምና እየሸወዱን ነው ማለት ብቻ ይሆናል።
ድርጅት የሚለካው በፕሮግራሙና በድርጊቱ ነው። “የአህያ  ባል ከጅብ አያስጥልም” የሚለው በእነኦህዴድ ላይ እየሰራ የሚቀጥለው ከኢህአዴግ አባል ድርጅትነታቸው እስካልወጡና የፕሮግራም ለውጥ እስካላደረጉ ጊዜ ሁሉ ነው። ፕሮግራማቸውን አንበሳ በሚያደርጋቸው መልክ አሻሽለው ለመቅረጽ ደግሞ አህያ ከሚያደርጋቸው የኢህአዴግ አልባነት መውጣት ቅድመ ሁኔታ (ግዴታ) ይሆናል። ይህም ሰሞኑን በአምቦና በተለያየ ቦታ ህዝቡ ሲመታ የጮሁት አቅም ስላጡ እንጂ ለማስመሰል አይደለም ካሉን ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታና ትንሹ ቅድመ ሁኔታ ይሆናል፤ ካልሆነ ግን እያታለሉን መሆኑ ግልጽ ይሆንልናል።

የኦሮሞ ህዝብ ቁስል የሚሰማቸው የህዝብ ልጆች፤ በኦህዴድ ከሚመራው የኦሮሚያ ፖሊስ ጋር እየሰሩ መሆኑን እየሰማን ነው፣ የኦሮሚያ ፖሊስም በህዝቡ ላይ ያለመተኮሱ የተጣለበትን በሰው ላይ ያለመተኮስ ግዴታውን መወጣት መጀመሩን ያሳያል። በዚህም ወንጀል መስራት ተወ (እየተወ ነው) ልንለውም እንችላለን። ምክንያቱም ሰላማዊ ሰልፍ የወጣን ህዝብ ተኩሶ ግደል ወይም ቀጥቅጦ መሰባበር ወንጀል ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልም ነውና ነው። የታጠቀው የኦሮሚያ ፖሊስ ግን፤ ቀይ ለባሽ የተባሉት በአምቦና በሌሎች ቦታዎች ሰልፍ የወጣን ህዝብ ሲገድሉ በተመሳሳይ መንገድ ከድርጊታቸው ታቅበው እንዲገኙና በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አላደረጋቸውም። ለምን?

ህዝብ መብቴን ጥሶብኛል የሚለው የኢህአዴግ አገዛዝ ነው። ትግሉም ፀረ-ኢህአዴግ አገዛዝ ነው። ኦህዴድና የኦሮሚያ ፖሊስም የዚህ የኢህአዴግ አገዛዝ አባልና አካል ናቸው። እነዚህን የህዝብ ልጆች ለዚህ አካል አጋልጦ መስጠት ጥሩ እምነት እንጂ ብልጠት ሊሆን አይችልም። በተለይ ከኛ የተደበቀ ወይም የማናውቀው ሌላ ሁኔታ ከሌለ በቀር በዚህ አካሄድ ልጆቻችን ላይ የሚደርስ ጉዳት አይኖርም ማለት ያቅተናል። በእኛም ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ የህዝብ ልጆች፣ በኦህዴድ በኩል ኢህአዴግ እንዲሆኑ ከተደረገ በህዝቡ ላይ የተፈጸመ ክህደት ይሆናል፣ ኦህዴድ አባል ለሆነበት ድርጅትና መንግስት አደጋ የሆነውን የህዝብን የመብት ጥያቄ የደገፉ ወይም የመሩ ወይም ሊመሩ ይችላሉ ተብለው የሚታመኑትን እነዚህን ወጣቶቻችንን እየመዘገበ ወይም በሌላ መልኩ ለኢህአዴግ እያስጠቆራቸው ሆኖ ተሰብስበው ቢታሰሩ ወይም ለህዝብ ትግል አስተዋጽኦ ማድረግ በማይችሉበት ሁኔታ እንዲገኙ ቢደረግ ወይም ኒውትራላይዝ ቢደረጉ በህዝቡ ትግል ላይ ውሃ መድፋትና በህዝቡም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ይሆናል።
ይህ ሲደረግ የነበረ ነው። “አሁን ለምን ያ አይደገምም?” ብለን ማመን አለብን? “የህዝቡ ትግል ስለተጠናከረ” የሚለው መልስ አይሆንም። ምክንያቱም የህዝቡ ትግል ስለጠነከረበት፣ ህወሃት/ ኢህአዴግ አሁን የኦህዴድ መሪዎችና አባላት እያደረጉት (እሳያዩት) ባለድርጊትና ባህሪ ይህንን ትግል ለማለዘብ እየሰሩ ሊሆንም ስለሚችል ነው። የህዝብን ጥያቄ እየመለሱ አይደለም፣ አሁንም የኦሮሞ ህዝብ በተለያዩ ወገኖች እየተገደለ ነው። እየታሰረና እየተፈናቀለ ነው። የተለወጠው የኦህዴድ አባባል (rhetoric) ብቻ ነው። ይህ የአባባል ለውጥ፣ የታክቲክ ለውጥ ቢሆንስ የምንለው ከእነዚህ ሁሉ በመነሳት ነው። ፖሊሱም ባይደበድበንም ከመደብደብ እየጠበቀን አይደለም።

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እስር ቤት ናቸው፣ የኦሮሞ አርቲስቶች የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸው ታስረው ፍርድ ቤት ይመላለሳሉ። ኮሎኔል ደመቀ እና የህዝብን የሃይማኖትና የሌላም መብቶችን ጥያቄ ለኢህአዴግ መንግስት ያቀረቡ ሰዎች ከእስር አልተፈቱም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ታስረው ዛሬም ድረስ አልተፈቱም።

የኦሮሞ ህዝብ መብት ከአማራው ወይም ከሌላው ህዝብ መብት አይለይም፤ አንድ ነው። ለኦሮሞ የምለው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተፈጻሚ ይሆናል። ኦህዴድ ኢህአዴግነቱ ሳይቀር ለህዝባዊነት ሊቀየር አይችልም። ለኦህዴድ መታዘዝ ለኢህአዴግ መታዘዝ ከመሆን አይለይም። ኦህዴድን መቀበል ኢህአዴግን መቀበል ነው። የተለየ አይሆንም። ህዝቡ አልቀበልም ያለው የኦህዴድ – ኢህአዴግን አገዛዝ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ይህ ፎርሙላ ደግሞ አልተለወጠም።

የህዝብን ጥያቄ ያልመለሰው ኦህዴድ/ኢህአዴግን በህዝብ ጉያ እንዲገባ መፍቀድ ስህተት ነው። ለታክቲክ ነው የሚልን ምላሽም አንቀበልም። ኢህአዴግም እያደረገ ያለውን የሚያደርገው ለታክቲክ ሊሆን ስለሚችል ይህ ያለመሆኑን ሳታስረዱን ለታክቲክ ነው ብትሉን ለመቀበል ያዳግተናል። እዚህ ሀገር በታክቲክ ስም የሚቀልጡ አድርይባይ ድርጅቶችን ማየት የተለመደ ነው። ከዚህ የሚጠብቀን ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ማሰጠትን እንደግብ ማስቀመጥ ብቻ ይሆናል።

የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አልተመለሰም። ኦህዴድ የህዝቡን ጥያቄ ለማስመለስ እየሰራም አይደለም ወይም ለዚህ ስልጣንና አቅም ለማግኘት እየሰራ አይደለም። ታዲያ ለምን እናግዘዋለን? ለምን እንቀበለዋለን?

የኦሮሞ ህዝብ በየአደባባዩ የሚደበደበው መብቱን ለመጎናጸፍ ነው። ግቡ መብቱንና ነጻነቱን መጎናጸፍ ነው። ድብደባ ቢቀርለት ለጥያቄው መልስ የሆነውን መብቱንና ነጻነቱን መጎናጸፍን (ምላሽ) አገኘ ማለት አይደለም። ድብደባ ለማስቀረት በሚል ከደብዳቢውና መብት ረጋጩ ጋር መተባበርና ድብደባ ስለቀረ ድል የተገኘ ማስመሰል ክህደት ለምን አይሆንም? በታክቲክ ላይስ ቀልጠን እየቀረን መሆኑን ለምን አያሳይም እንላለን?

ከሌላው ኢትዮጵያዊ የሚደበቅ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ (ዓላማና ግብ) እና አካሄድ ሊኖር አይችልም። የኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ አማራን፣ ጉራጌንና ሌሎችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይመለከታል። የአማራም ወዘተ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው። የኦህዴድ ዓላማ የህዝብን ጥያቄ ማስመለስና መመለስ ሆኖ ከኢህአዴግ በመውጣትና ወይም የፕሮግራም ለውጥ በማድረግ ተደራጅቶ ካላየነው በቀር ከህዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አንጻር መዝነን ኦህዴድን መቀበልና መደገፍ አይቻለንም።

ኢህአዴግ የማያደርገውን የሚናገር ወይም ያደረገውን የሚክድ ብቻ አይደለም። ድርጅቱ የሌሎችን አጀንዳ እና ንግግርም በመንጠቅ እንደራሱ አድርጎ በማቅረብም ይታወቃል። በእሱ ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ወገኖች የሚጠቀሙባቸውን አባባሎች በመጠቀም ህዝቡን ያደናግራል። አጀንዳቸውንም በመንጠቅ በራሱ መንገድ በማቅረብ ያከሽፈዋል፤ መልስ አይሰጥም። የራሱን ጥያቄ አውጥቶ በመመለስ የህዝቡ ጥያቄ እንዲድበሰበስና ወደሁለተኛነት እንዲገፋ ያደርጋል። ቀጥሎም ያረሳሳል።
ለምሳሌ፣ በቅርቡ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል የሰላም ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ነበር። የአማራና ኦሮሞ ህዝብ እየተጣላ አይደለም። ተጣልቶም አያውቅም። በኦሮሚያና በሌላም ቦታ ባሉት አማሮችና ኦሮሞዎች ላይ ጠብ የሚያስነሱት ካድሬዎች መሆናቸውን ኢህአዴግም ነግሮናል። ስለሆነም ካድሬዎቹን ህዝብን (ሰውን) አታጋጩ ብሎ አደብ ማስገዛት እንጂ የሰላም ኮንፈረንስ መጥራት አያስፈልገውም ማለት ነው።

ታዲያ ያንን ለምን አደረገ? አንደኛ፣ ካድሬዎቹን አደብ ማስገዛት ስላልፈለገ ይህንን ችግር መልስ ሳይሰጥበት እንዳለ ትቶ ችግር ባልሆነው የኦሮሞንና የአማራን ህዝብ የማስታረቅ ስራ እንድንጠመድና ሃሳባችንና ትኩረታችን ተቀይሮ ወደዚያ ዞሮ እንዲታሰር ስለፈለገ ነው። በዚህም “የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ!” የሚሉትን ወገኖች አጀንዳ ይቀማል። “ኢህአዴግ በተለይ ህወሃት አማራና ኦሮሞን በማጣላት ስልጣን ላይ ቆየ” የሚሉትን አፍ ያዘጋል። “ሁለቱን ህወሃት ያጣላቸው ነበር።” የሚባለውም ውሸትና የጠላት ወሬ የነበረ ያስመስልበታል።

ሁለተኛ፣ ብሄራዊ ዕርቅ የተደረገ ያስመስልበታል። ሶስተኛው፣ ከህዝብ ጥያቄዎች ላይ ሃሳባችንና ትኩረታችንን ወደኮንፈረንሱና ውጤቱ በማዞር የህዝቡን ጥያቄዎች በዚህ ያረሳሳበታል። አራተኛውና ዋናው ግን ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ተቃውሞና ተቀባይነት የማጣት አደጋ ያጋጠማቸው በኦሮሚያና በአማራ ክልል የኢህአዴግ ተወካይ የሆኑት ኦህዴድና ብአዴን ስለሆኑ እነዚህ ሁለቱ ህዝባቸውን በመወከል አንዳቸው በሌላኛቸው ክልል የሰላም ኮንፈረንስ የጠሩ ስለሆነ የህዝብ ተወካይነትና ተቀባይነት ካባቸውን መልሶ ያስደርብላቸዋል።
አምስተኛ፣ “ብአዴንና ኦህዴድ በህወሃት ላይ ተነሡ!” ወይም “በነጻነት ወስነው ማስፈጸም ጀመሩ” ብለን ለማመን የሚያስችል የውሸት ማስረጃ እንዲሆነን ፈልጎ ነው። (ይመስለኛል አላልኩም)

ብዙዎቻችን “ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ብሄሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል መካከል ጠብ የለም። አልነበረምም” እያልን እናቀርባለን። ይህ እውነት የሆነ እምነታችን ነው። ጨቋኝ ብሄር የሌለ መሆኑ እንናገራለን። ኢህአዴግ ግን በተዘዋዋሪ አንዱ ብሔር ሌላውን ይጨቁን እንደነበረ እንዲታመን ይሰራ ነበር። በቀጥታ “ጨቋኝ ብሔር የለም!” ብሎ አይናገርም ነበር። ነገር ግን ይህንን ለውጦ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ አማርኛ ዝግጅት ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በተላለፈው ላይ የብአዴን የአማራ ክልል ቃል አቀባይ ይህንን ተናግረዋል። በቀጥታ “በኢትዮጵያ ጨቋኝ ብሔር የለም” ባይሉም “አማራና ኦሮሞ ወይም ሌላው እንደህዝብ ተጣልተው አያውቁም” ብለዋል።

አሁን ግን እነአቶ ሃይለማርያም ይሉት እንደነበረው “ህዝቡን የሚያጋጩት የእኛ ካድሬዎች ናቸው” አላሉም። ህዝቡን ማን እንዳጋጨው መናገር ትተው፣ የህዝቡን ግጭት የብሔር ግጭት መስሎ እንዲቀርብና ያንን ቅርጽ በመያዙ የሚጠቀሙ ወገኖች መኖራቸው ማንነታቸውን ሳይገልጹ በመጥቀስ አወገዟቸው። የሰላም ኮንፍረንሱም እነዚህን አካላት የፈለጉትን ለመንሳት ያደረጉት መሆኑንን እንድንቀበል የፈለጉም መስለዋል ወይም ይህንን የብሔር ጥል የሚፈልግ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ካለ (ስላለ) እሱንም የፈለገው እንዳይሳካለት ለማድረግ የፈጸሙት ሊሆን ይችላል ብለን እንድንገምት ቀዳዳም ለመፍጠር ጥረዋል። በዚህም እውነትም እነብአዴንና ኦህዴድ ከህወሃት ፍላጎትና ፍቃድ ውጪ መንቀሳቀስና ወስነው መፈጸም ይችሉ እንደሆነ ለማመን (እንድናምን) ተጨማሪ ምክንያት ሊያቀብሉን ሞክረዋል። በተለይም ህወሃት የሁለቱን የሀገሪቱን ታላላቅ ብሔሮች መከፋፈል ስልጣን ላይ የመቆያው ዋናው ታክቲክ አድርጎ በመጠቀሙ የሚያምኑ ወገኖች በዚህ የብአዴንና ኦህዴድ ድርጊት የህወሃትን ፍላጎት በመንካት ጭምር መስራት እንደቻሉ አድርጎ በማቅርብ እምነታቸውን በመናድ የፈለጉም መስለዋል።

ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም የኦሮሞ ወይም የአማራ ህዝብ ጥያቄ አልተመለሰም። እየተደረገ ባለው ግን ህዝቡ ጥያቄዎቹን በራሱ ወይም የእኔ ከሚላቸው ጋር ሆኖ በህጋዊ መንገድ አስገድዶ ማስመለስን ትቶ የኢህአዴግ አባል ከሆኑት ኦህዴድና ብአዴን በኩል ተስፋ እንዲፈጥር (እንዲጠብቅ) እየሆነ ያለ ይመስላል። የዚያ አዝማሚያ አየታየ ነው። ወደጠባቂነት የተመለሰ ህዝብ ደግሞ የተሽነፈ ነው።

ህዝቡ ከኢህአዴግ ተስፋ በማጣቱና ኢህአዴግን መፍራት በማቆሙ አገዛዙ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኗል። ህዝቡ በራሱ ስለተማመነ ሌላ ሰው ሳይፈልግ በራሱ መብቱን መጠየቅ ጀምሯል። ቀጥሎም የራሱን መሪ ሊያበጅ መሆኑን የተረዳው ኢህአዴግ፤ የተወሰኑ የራሱን አባል ድርጅቶች በመሪነት ለህዝቡ ልኮ፣ ህዝቡን ወደቤቱ እየመለሰ አይደለም የምትሉ ካላችሁ ማስረጃ እንፈልጋለን

Filed in: Amharic