>

የጋሽ ለማ በገበያ በሁለት ቢላዋ ጭውቴ የማቆምያው ሰዓቱ ተቃረበ (ዮናስ ሃጎስ)

እነ ለማ ሚናቸውን በግልፅ የሚለዩበት ጊዜ አሁን ነው። ወይ እኛ ስንል እንደነበረው ሲሰሩት የነበረውን ‹ድራማቸውን› አቁመው ትክክለኛ ኢህአዴግ ኢህአዴግ መሽተት አለባቸው አሊያም ሌሎች ተቃዋሚዎች ተስፋ እንዳደርጉባቸው የሕዝብ መሆናቸውን ተጨባጭ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ አለባቸው።
***
ተጨባጭ ስል ያው ገብቷችኋል አይደል? ይሄ ‹ሱሴ› ምናምን ዓይነቱን ቅፈላ አቁመው በዓይን በሚታይ እና በእጅ በሚዳሰስ መልኩ ማለቴ ነው።
***

BTW እኔ ተቃዋሚው በለማ ‹ሱሴ› ንግግር እንዴት እንደተሸወደ ሳስበው ግርም ይለኛል። ኢሕአዴግ እኮ የ2010 ትልሜ ኢትዮጵያዊነት ነው ብሎ ፕላን ነድፎ ይፋ ያደረገው በሐምሌ ወር ላይ ነበረ። ከዚያ በኋላ ካሁን በፊት አልሟቸው የማያውቁ እንደ ‹ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ዘመን መመለስ› ( ድሮ ያለፉት ስርዓቶች እያሉ እንዳላማረሩ)፣ የባንዲራ ቀን (ሐገሪቷን በአስራ ምናምን ባንዲራ ስር ከፋፍለው ብሔራዊውን ባንዲራ በጨርቅነት እንዳልመሰሉ) እንዲሁም ያ 22 ሚልዮን ብር የወጣበት ሸብ ረብስ እንዴት ይረሳል?
***
ታድያ ዛሬ ደርሶ ለማ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሲያወራ ደርሰን የተደነቅነው ለምንድን ነው?
***
በነገራችን ላይ ‹ኢትዮጵያዊው ለማ› ካቢኔው በፊት የጀመረውን ‹በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ኦሮሞ ተወላጆች ልዩ ጥቅም›ን በተመለከተ ሰሞኑን ወደ ስራ ላይ ለማዋል ተግባራዊ ውይይት መጀመሩን ታውቁ ይሆን?
***
ለማንኛውም ፌደራሉ በነለማ ደስተኛ አይደለምና ጠ/ሚ/ሩ በመከላከያ ሚንስትሩ ታጅበው የሰጡት መግለጫ ወደዛ አካባቢ የሚዘመትበት አካል መኖሩን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሆኗል። ጋሽ ለማ በገበያ በሁለት ቢላዋ የሚያደርጉትን ጭውቴ የማቆምያው ሰዓቱ መቃረቡን ማስተዋል ይቻላል።
***
ድሮም ብለናል… አይደለም በአምባገነን ስርዓት ውስጥ በማገርነት የሚያገለግል አካል ቀርቶ ከውጭ ላለነው እንኳን middle line የሚባል ነገር የለም። ወይ ከአምባገነን ጋር ነህ አሊያም ከሕዝብ ጋር ነህ… አለቀ!
***
የጠሚሩ መግለጫ አንኳር ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል...
~ የክልሎች አመራሮች እየተካሄዱ ያሉ ሕገወጥ ሠልፎችንና ግጭቶችን ማስቆም አለባቸው፤
~ የአሸባሪዎችን ባንዲራ ይዘው ሕገወጥ ሠልፍ የሚያደርጉ አካላት አሉ፤
~ ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ የክልል አመራሮች የማስቆም ግዴታ አለባቸው፣ ይህ ተፈጻሚ ካልሆነ ግን ራሳቸው በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ፤
~ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ተሳታፊ የነበሩ የፀጥታ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች ነበሩ፤
~ በግጭቱ ወቅት ለብሔራቸው ወግነው ግጭቱ እንዲባባስ ያደርጉ የነበሩ የጸጥታ አካላት ነበሩ፤
~ እነዚህ ሰዎች በብሔራዊ ደኅንነት የተለዩ ሲሆን በቅርቡም ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል::
***
ያው እንግዲህ ጃዋር ባለፈው ‹ሂሳቡ በኔ ነው…› ምናምን ያለውን እንደማይዘነጋ በማመን ፈንዲሻችንን ይዘን አንድ ጥግ ተሰይመን ድራማውን መጨረስ ነው።
Filed in: Amharic