>

በኢትዮጵያ የለውጥ ዋዜማ የሕወሐት ኢሕአዴግ መንታ ልብ (ዜግነት/ጎሰኝነት) ስሌት!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

የሕወሐት/ኢሕአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ እና የለውጥ እርምጃ አሁን ሀጋራችን ያለችበትን ውጥንቅጥ መፍትሔ ያላስገኘ በመሆኑ በህዝቡ ውስጥ ያለው ተቃውሞም ሆነ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው ሽኩቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እነዚህ ሁለት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ማለትም የህዝብ አልገዛም ባይነትና የግንባሩ የውስጥ ሽኩቻ የሀገራችንን የለውጥ እጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለሆነ በጥንቃቄና በቅርበት መከታተልና መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሰረት፡-
1. የኢሕአዴግ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የውስጥ ሽኩቻ የሀይል አሰላለፍ ከጊዜ ጋር ወደ የት ያዘነብላል?
2. ሕወሐት አሁን ያለውን ችግር በአሸናፊነት ለመወጣት ከመቀሌው ስብሰባ ምን ይዞ ይመጣል?
3. የለውጥ ሀይሉና የህዝብ ተቃውሞ መጨረሻው ምን ይሆናል?
የሚሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

1. የኢሕአዴግ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የውስጥ ሽኩቻ የሀይል አሰላለፍ ከጊዜ ጋር ወደ የት ያዘነብላል?

ብአዴን ከሕወሐት ጋር ያለው ቅራኔ “የሕወሐት የበላይነት አለ” የሚል ሲሆን ከሕወሐት ጋር ያለውን ቅሬታ ማስተናገድ የሚፈልገው ከትግራይ ጋር ያሉትን የወሰን ጥያቄዎችና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ እና የቅማንት እራስን የማስተዳደር ጥያቄ “ሕወሐት ለትግራይ ወገንተኝነት በማሳየት አማራን በድሏል የቅማንትንም ጥያቄ አማራን ለማዳከም ልዩ ድጋፍ አድርጓል” በሚል የህዝብን ጥያቄዎች እውቅና በመስጠት የህዝቡ ጥያቄዎች ብአዴንን አልፎ ወደ ሕወሐት እንዲያነጣጥሩ በማድረግ ሕወሐትን የማስፈፀም አቅም እንዲያጣ ትብብር መንፈግና በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች በለሰለሰ ሁኔታም ቢሆን የህዝብ ጥያቄዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ሽፋን በመስጠት ለህዝቡ የስነ ልቦና ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡
ኦሕዴድ ከሕወሐት ጋር ያለው ሽኩቻ በጉባኤው አቋም እንዳንፀባረቀው ለሕወሐት ላለመንበርከክና በህገ መንግስቱ የተሰጡት የክልሉ ስልጣኖች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ እና በፌደራል መንግስቱም ያለውን ተፅዕኖ እና የስልጣን ድልድል የማሳደግ የሚል ይመስላል፡፡ ስለዚህ ኦሕዴድ ከሕወሐት ጋር ያለው ቅራኔ መገለጫ ከብአዴን የአኩራፊነትና ያለመተባበር ደረጃ ከፍ ያለና የተጋፊነት አመለካከት ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ወደ ውጤት ለመቀየር በአብዛኛው ህገ መንግስቱ ይከበር የሚልና ከብአዴን ጋርም የትግል አጋርነት መፍጠር ነው፡፡
ደኢሕዴን አሁን ባለው ቁመና ሚዛን አስጠብቆ በጥንቃቄ ለመሄድ የወሰነ ቢመስልም የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ቦታ ስለያዘ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የወሳኝነት ሙሉ ስልጣን እስካረጋገጠ ድረስ ከሕወሐት ጋር የጎላ ቅራኔ ውስጥ የሚገባ አይመስልም፡፡
አሁን ያለው የግንባሩ አባል ድርጅቶች አሰላለፍ እሰከየት ይዘልቃል?
በመሰረቱ የድርጅት ሽኩቻ ከግለሰብ የስልጣን ጥም እስከ ንዑስ ቡድን ፍላጎት ከዛም ከፍ ሲል በእናት ድርጅቶች መካከልና እስከ ሀገራዊ ስልጣን የሚደርስ ነው፡፡ የወስጥ ሽኩቻው እያደገ ሂዶ የህዝብ ግፊት ሲጨምርና ወደ ውጤት ሲቀርብ “እኔና ድርጅቴ ከትግሉ ውጤት ምን ያህል ይደርሰናል” የሚለው ጥያቄ ግልፅ እየወጣ ይመጣል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኦሕዴድና ብአዴን ሕወሐትን ለማዳከም የፈጠሩት ትብብር ከውጤቱ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ፊት ለፊት መፋጠጥ ይጀምሩና ሕወሐትን ለማዳከም የነበራቸው ትብብር ፈርሶ ትብብሩ ወደ ፉክክርና ሽኩቻ ይቀየራል፡፡ ደኢሕዴንም በኦሕዴድና ብአዴን ትብብር ስለማይደሰትና የመገለል ስሜት ስለሚሰማው የህወሐትን የበላይነት ባይፈልግም በፉክክሩ ውስጥ ወደ ሕወሐት እንደሚያዘነብል መገመት ይቻላል፡፡

2. ሕወሐት አሁን ያለው ችግር በአሸናፊነት ለመወጣት ከመቀሌው ስብሰባ ምን ይዞ ይመጣል?

ሕወሐት አሁን በያዘው አቋም ለአገዛዝ እንዲያመቸው ለ26 ዓመት የበተነውን ሀገር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ የሚጥር ይመስላል፡፡ ለማታልልና ለከፋፈፍለህ ግዛው ሲባል በህገ መንግስቱ ውስጥ የተደነገጉ የጎሳ መብቶች ክልሎች በሚጠብቁት መልኩ ባለመከበራቸው የሕወሐት የበላይነት አለ ብለው ፈራ ተባ እያሉም ቢሆን አቋም የወሰዱ ይመስላል፡፡ በሁሉም ክልሎች በሚነሱ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች “ተጠያቂው ሕወሐት ነው” በማለት የክልል መንግስታት መሪ ድርጅቶች የህዝብ ጥያቄ ሳይነካቸው ቀስቱ ወደ ሕወሐት እንዲወረወር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለሳለሰ ሁኔታም ቢሆን ሕወሐትን ባለመተባበር ክልሎች በሚቆጣጠሩዋቸው የመገናኛ ብዙሀን የህዝብን ጥያቄ ተገቢነት ሽፋን እንዲያገኝ የሚችሉትን ያደርጋሉ፡፡ ኢሕአዴግን በአባል ድርጅት የማስፈፀም አቅሙ እንዲዳከም ባለመተባበርና የህዝብ ጥያቄዎች ጫና ሕወሐት ላይ እንዲያርፍ በማድረግ ሕወሐትን በባለ ሁለት ስለት ሰይፍ የትግል ስልት ለማዳከም የሚሞክሩ ይመስላል፡፡
ሕወሐት ይሕንን ለመቋቋም የሚያደርገው ትግል ሁለት ነገሮችን ማለትም ጎሰኝነትንና ዜግነትን አጣምሮ እንዳስፈላጊነቱ እያጫወተ የተበተነውን ድርጅቱን ለመሰብሰብና የህዝብን ተቃዉሞ ለማርገብ ሲጣጣር ይሥተዋላል፡፡ ይህንን እስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ በፕሮፓጋንዳ ደረጃ የብሔረሰብ ጥያቄዎች እንዳይለጠጡና ከቁጥጥሩ እንዳይወጡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ በማድረግ የጋራ መስተጋብሮችን ማጉላት ሲሆን በሌላ ወገን በግንባሩ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ ለማርገብ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞ በማለት የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበርና የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት የማስጠበቅ ሀላፊነት አለበት በማለት በቁጥጥሩ ያለወን መከላከያና ደህንነት በሙሉ አቅሙ ሊጠቀም ይችላል፡፡

3. የለውጥ ሀይሉና የህዝብ ተቃውሞ መጨረሻው ምን ይሆናል?

በኢሕአዴግ ውስጥ ባለው ሽኩቻ ሕወሐት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ በሚወስደው እርምጃ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው አለመታዘዝና በደርጅቱ ተስፋ መቁረጥ ወደ ለየለት አቋም መውሰድና መክዳት ያድጋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሀገራችን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችንና የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስለምተስብ ሕወሐት ለከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ይዳረጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕወሐትን የተስፋ መቁረጥና የመደናገጥ እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል፡፡ በመጨረሻም የድርጅት ሽኩቻውና የህዝብ ተቃውሞ ተዳምሮ ኢትዮጵያ ወደ አይቀሬው ለውጥ ትቃረባለች፡፡
የለውጡን አይቀሬነት ከላይ በገለፅኩት ሁኔታ መገንዘብ ቢቻልም ለውጡ በአውንታዊ ወይም በአሉታዊ መልኩ ስለመጠናቀቁ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡ የለውጡን ውጤት ለመገመት አስቸጋሪ የሚያደርገው የአጭርና የረጅም ጊዜ ግብ አስቀምጦ ትግሉን በሃሳብ የሚመራ ጎልቶ የወጣ የፖለቲካ ሃይል ባለመኖሩ ነው፡፡
በእኔ እምነት ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የብተና አደጋ ለማዳንና ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደተወሰደው ዓይነት አቋም በሌሎች የእምነት ተቋማትም ተጠናክሮ መቀጠልና የህዝብ ወገንተኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡ የሲቪክና የሙያ ማህበራትም በቅርቡ የሰራተኛ ማህበር ከወሰደው ድፍረት የተሞላበት ግልፅ አቋም ትምህርት በመውሰድ ከህዝብ ጎን መቆማቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶችም የአገዛዙን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በማጋለጥና የህዝብ ጥያቄዎችን በመደገፍ ለውጡ በአወንታዊ መልኩ እንዲጠናቀቅና የጋራ አገራዊ ቅርፅ እንዲይዝ በሀላፊነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በመጨረሻም ከላይ ከጠቀስኳቸው አካላት የተውጣጣ “የባለ አደራ መንግስት” እንዲቋቋም በማድረግ ሀገራችንን ከብተና በመታደግ ወደ ዴሞክራሲ እድትሸጋገር ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በጥንቃቄና ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ ትግላችንን ማስተባበር አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡

Filed in: Amharic