>

የግል ኣስተያየት (አርአያ ጌታቸው)

እስከማውቀው ድረስ ቦይኮት ኮካ ኮላ ተብሎ የተጀመረ ይፋዊ ዘመቻ የለም፡፡ ነገር ግን በርካቶች ገና ባልተጀመረ ዘመቻ ላይ ሆነው የወረደ፣ ተራ፣ የዘቀጠ .. የሚሉ ቃላትን በመደርደር ለማጣጣል ሞክረዋል፡፡ ቴዲ አፍሮ ላይ ለደረሱበት የሞራል ኪሳራዎች እና ስም መጥፋቶች ግን ምንም ለማለት አልደፈሩም፡፡ ዛሬ አርቲስት ሁሉ ለሆዱ ባደረበት ወቅት ሀሳቡን ያለምንም ፍርሀት በአደባባይ ጮክ በመግለጽ ብቻውን በቆመ በዚህ ባላቴና ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እና ግፍ ግን አንስቶ መወያያትን በማህበራዊ ድረ- ገጽ ላይ ያለውን “የትግል እንቅስቃሴ” አቅጣጫ ያስቀይራል በሚል ለማጣጣል የሚደረግ ሙከራ መልካም አይመስለኝም፡፡

ኪነጥበብ በትግል ውስጥ ከምንም በላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ቀደም ባሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንኳ ብንመለከት በተለይ ከአቢዮቱ ጋር ተያይዞ ምን ያህል ህዝቡን ለማነሳሳት እንደተጠቀሙበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፣ ከዛም በእድገት በህብረት ዘመቻ፣ በኢትዬ ሶማሊያ ጦርነት እና በ17 ዓመቱ የእርስበርስ ጦርነት ወቅት ኪነጥበብ ከጦርቱ ባልተናነሰ በግንባር ቀደምትነት አገልግሏል፡፡ ወያኔ ጫካ በነበረበት ወቅት ለተለያዩ የጦር ክፍሎቹ ስሞች ፤ ለምሳሌ ምርኮኞቻቸውን ከያዙ በኋላ “ቦዶ 6” ውሰዷቸው ከተባለ እስር ቤት ማለት ነው፡፡ ባዶ 1 ማለት ደሞ የሙዚቃ ጓዶቻቸው ናቸው ፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ ከባዶ 1 ጀምሮ 2፣ 3፣ 4.. እያለ ብዙ ክፍሎችን ሲሰይሙ በአንደኛነት ያስቀመጡት ኪነጥበቡን ነው፡፡ አሜሪካኖች በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የምስራቁን አለም ያንኮታኮቱበት አንደኛው መሳሪያቸው በሆሊውድ ፊልሞች እና ሙዚቃዎች ባካሄዱት የባህል ወረራ እንደነበር አይረሳም፡፡

እዚህ ሁሉ ሀተታ ውስጥ የገባሁት ዛሬ በቴዲ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ነገ ለሚመጡት የኪነጥበብ ሰዎች መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡ ከፖለቲካ እና ከታሪክ ራቁ የሚል፡፡ ህዝባችን በፍርሀት ቆፈን ውስጥ በሚሰቃይበት በዚህ ወቅት ላይ ጠንካራ የኪነጥበብ ሰዎች ቢኖሩን ምንያህል ጉዟችንን ያቀሉልን ነበር? በዚህ አያያዝ ግን በተለይ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ ለመውጣት ግዴታ “Chop my Money” ወይም “My Money is My Mind” ብለው መዝፈን ሊኖርባቸው ነው፡፡
Heineken and Coca Cola ዛሬ እያደረጉ ያሉትን ዝም ብሎ ማያት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ነው፡፡ እየሞተ ያለውን የኪነጥበብ ትውፊት የበለጠ ማጥፋት እንዳይሆንብን እሰጋለሁ፡፡ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ አርቲስቱን ሳንሱር እያደረጉት እንደሆነ ልትረዱት ይገባል፡፡ ድርጅቶቹ በአርቲስቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትይጵያ ፖለቲካ እና ቀደምት ታሪክ ውስጥ ጭምር እጃቸውም ሳያስቡት አስገብተዋል፡፡
ቴዲ አፍሮ ይሄንን ወቅት በብቃት እንደሚወጣው ምንም ጥርጥር የለኝም፣ ምክንይቱም የመጀመሪያውን አልበም ካወጣበት ቀን ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ያለፈ ጠንካራ ልጅ ነው፡፡ በተለይ ”ጃ!…ዯስተሰርያል” በሚለው ስራው ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ አስከመታሰር እና በአጠቃላይ ከአመት በላይ በእስር ተቀጥቶ የወጣ ሲሆን፤ ወጥቶም ግን እንደተፈራው የሞራል ስብራት ሳይደርስበት በጥቁር ሰው አልበሙ በርካታ ድንቅ ሀገራዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስራዎቹን አስኮምኩሞናል፡፡ ከምንም በላይም ባገኘው መድረክ ለሀገራችን የሚበጀው ፍቅር እና ይቅር መባባል እንደሆነ ይሰብካል፡፡
ሰዎች ሲታሰሩ እና ሲሞቱ ብቻ የምንጮህ ከሆነ እና ነገሮችን በጣም አስፍተን እና ለጥጠን ማየት ካልቻልን እንዲሁም ለጠቅላላው ፍትህ ሳይሆን ለያራሳችን ኮዝ እሩጫ ከጀመርን ያለ አጋዥ መውደቃችን አያቀርም፡፡ አሁንም በጣም አርቀን ማለም የማንችል ከሆነ እና በስፋት እና በጥልቀት በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ ያሉት መገፋቶች እና በደሎች እያካተትን መሄድ ካቃተን እየተከፋፈልን እና ቁጥራችን እየተመናመነ መሄዱ አይቀሬ ነው፤ በተቃራኒው ቢያንስ ተቀራራቢ አቋም ላይ የምንገኝ አካላት ለኮዞቻችንን መደጋገፍ ብንችል እና አብረን ብንቆም መንገዶቻችንን ቀላል ይሆኑ ይመስለኛል፡፡
ለማንኛውም ኮክ ስቱዲዮ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ (የአለም ዋንጫ እስከሚጀመርበት ቀን ድረስ) ተጠቅሞ ቴዲ የደከመበት የልፋት ውጤት ይለቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሁሉም ነገር በሰላም እና በፍቅር እንዲጠናቀቅ የሁላችንም ምኞት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን የሚሆነውን ሁላችንም አብረን እናያለን፡፡ የአርቲስቱንም ምላሽ እንዲሁ እንጠብቃለን፡፡
ለመሰነባበቻ ቴዲ አፍሮ በ1997 የነበረውን ምርጫ በማስመልከት በጻፈው ግጥም እንለያይ፡፡
(ቴዲ አፍሮ በ1997 ዓ.ም የፖለቲካ ትኩሳት ወቅት የነበረውን ስሜት እንዲህ በግጥም ከትቦት ነበር፡፡)

የሳባን ዘመን ሚስጥር የያዘው
አክሱምም መጣ የተገረዘው፤
መች ተገርዘናል እኛስ ሁላችን
ፍቅር ማጣት ነው ሸለፈታችን፤
በአክሱም አለቶች ሳባን አሻግሮ
የቃልኪዳኑን ሚስጥር መርምሮ፤
በእምነት የእኩል ቤት በፍቅር መክሮ
በሀያላን ላይ ዙሪያውን አጥሮ፤
ስራን ቢሰራ ወገኔ ነቅቶ
ይነሳ ነበር እንዳይቀር ሞቶ
እንዳይሰማ ግን ትዕቢት ተሞልቶ
ተረትን ናቀው፣ ታሪኩን ናቀው፣ የራሱን ናቀው፣ መጽሐፍ በልቶ፤
በሰው መጽሐፍ ያበደ አዋቂ ለጥፋት ሁሉ ነው ተጠያቂ
የራሱን ሳይጥል የሰው ቢሰማ
ይረዳን ነበር እንድንስማማ
የራሱን ጥሎ የሰው ከሰማ
በቃ ሆነናል እንዳንስማማ፤
ሁሉም ሲመጣ ነው ተናጋሪ
መመሪያው ላይ ግን የለም ፈጣሪ፤
በሌሎች መንገድ ለማንድን እኛ
ስሙን ይሉናል ጆሮ አለን እኛ?
ሙቱ ይሉናል መች ኖረን እኛ?
ጆሮስ ሚሰማ አፍስ ቢናገር
እውነት ካልሆነ የሚነጋገር
ምጣድ ነው እንጂ የታል ሚጋገር፤
አንዳቸው ጋግረው እኛ እንዳንበላ
ዱቄቱ የእኛ እርሾው የሌላ
ይለቅ ይልቅስ
ፍስሀ እንዲሆን ደስታ እንዲሆን እንዲቆም ሙሾ
ከሽማግሌዎች እንዋስ እርሾ፤
የነሱ እርሾ የነፋው ቡኮ
ከእኛ አልፎ ለሰው ይተርፋል እኮ
ግን ምን ያደርጋል አትሰሙም እኮ
እረ እባካችሁ አቃተን እኮ
ደከመን እኮ!
ይህ ሁሉ ሲሆን ያገሬ ሰዎች ያሳዝኑኛል
ይህንንም ስል
ከመስማት ይልቅ ማነህ ይሉኛል፤
ትንሽ ልጅ ተናግሮ ትልቅ ሰው ሲሰማ
እውቀት ነው ብሎ ሰው አይስማማ፤
ይህንን እውቀት ያሳጣው አቻ እኔ አይደለሁም ፈጣሪ ብቻ
ለቀረን ጉዞ ማስተዋል ጠፍቶ ቀና መንገድ
አደራ እላለሁ ለገዢው ፓርቲም ለተቃዋሚም ደም እንዳይፈስ
የኋላ ኋላ ጠፍቶ የሚሰማ፤ በዝቶ የሚናገር
ከእነ ልጆቿ እንዳትሞት ሀገር
ከየራሱ ጋር ሰው ይነጋገር፡፡
( ቴዲ ኣፍሮ Teddy  1997 ዓ.ም)

 

Filed in: Amharic