>

የጥበብ መገኛ የሃይማኖት አገር! (ሃብታሙ አያሌው)

በርግጥም በዚያ ምድር እነዚያን ድንቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የገነቡት እጆች ዳግም የተወለዱ ይመስላል። እነዚያን አፍ የሚያስከፍቱ ድንቅ ውቅሮችን የገነቡት ጥበበ ጌራ ወርቆች ራሳቸው ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ለማብሰር የክሂላቸውን ልህቀት ዳና በብርሃን ፀዳል አጅቦ የሚገልጥ ሌላ የእጃቸው ሥራ ሌላ የህያውነታቸው ምልክት ከ800 ዓመታት በኋላ ዳግም በቅዱሳን ምድር በወሎ ሌላ ትንግርት ሌላ ግርምት ሆነ።

የተራዘመው ጥናት ባለቤት እነ ግራሃም ሃንኩክ የላሊበላን ውቅሮች አሻራ ከኢትዮጵያውያኑ ህልው ማህደረ ጥበባት ነፍገው ለአውሮፓውያኑ የህንጻ ጥበበኞች (ቴምፕላሮች) ለመስጠት ባጅተው ነበር፤ ይህ ይሆን ዘንድም ህንፃ ህላዌ አመክንዮአቸውን ብዙ በጥናት መጥሐፋቸው አትተዋል፤ አንዳንዶች የሰዋስቲካን ምልክት አይተው ከህንዶች ጋር አያይዘውታል፣ ሌሎችም ደግሞ የዚያ አሻራ ባለቤቶች ከዚህ ዓለም ውጭ የሆኑ የሰለጠኑ እንግዳ አካላት ናቸው ብለዋል ከዩፎፎ አለም አመክንዬ ለማዋሰብ ቧግተዋል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ወዲያም ተባለ ወዲህ ሊቃውንቱ በቅዳሴ “የጥበብ ሃገሯ ወዴት ነው ? ማደሪየዋ ወዴት ነው ? ቦታ ጎዳናዋ ከወዴት ተቃኘ? ዝናና ወሬዋ ከወዴት ተገኘ? ፈልጎ የገዛት ማነው በቀይ ወርቅ፣ ባህሩን ተሻግሮ ስሟን በማወቅ? ” እያሉ መርምረው አስሰው አስሰው የጥበብን ዳና ወሎ ላይ አትመው፤ ሁለቱን ዘመን አሳስበው ባዶውን ስፍራ በእጃቸው ጥበብ ሞልተው ዘመን አስታርቀዋል። አሁን በዚህ ዘመን ግን የላሊበላ ውቅሮች አምሳል በእኛው ዘመን ሰዎች ተፈልፍለዋል።
.
ከታች በምስሉ ላይ የሚታዩትን ህንጻወች አንድ የበራለት ዲያቆን እና ሌሎች መናኒ አባቶች እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 መጨረሻ ድረስ ከመሬት ውስጥ ፈልፍለው ለዚህ አብቅተዋቸዋል። እስካሁን ድረስም በራሳቸው ወጭ እና በራሳቸው ጉልበት አምስት ውቅር ህንጻወች ተፈልፍለው ይገኛሉ። እነዚህ ህንጻወች ከወልዲያ ከተማ 126 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛሉ። ከወልዲያ ወደ ጎንደር የሚወስደውን አውራ ጎዳና ይዘን በመሄድ ጋሸና የምትባለው መገነጣጠያ ከተማ ስንደርስ ወደ ላሊበላ የሚያስኬደውን መታጠፊያ በመከተል ከጋሸና ከተማ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እናገኘዋለን። የሚታዩት ፍልፍል ህንጻወች በሙሉ ከአንድ አለት ላይ የወጡ ናቸው፣ ምንም ዓይነት ሲሚንቶም ሆነ ሌላ የህንጻ ግብዓት አላረፈባቸውም። እኒህ ህንጻወች የተፈለፈሉበት አለት እንደ ላሊበላው ቤተ መድሐኔዓለም ሁሉ ወደ ጥልቁ እጅን ሲልኩ እጅ ከውሃ ይገናኛል፤ የጥበብ መፍለቂያ የሃይማኖት አገር ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ኑሪ።

የመረጃው ምንጭ ብሩክ አበጋዝ እና ፎቶን በአካል ሄዶ ያነሳው መታገስ ዋለ ከፍ ያለ ምስጋና ይድረሳችሁ።

Filed in: Amharic