>

“ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ

አምደጽዮን ሚኒሊክ

ለዳግማዊ አጤ ምኒልክ አስተዳደር መቃናትና ስኬት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ባለቤታቸው ጣይቱ ብጡል የእቴጌነት ዘውድ የተጫነላቸው ከዛሬ 128 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም) ነበር፡፡

ከ1857 ዓ.ም ጀምሮ የሸዋ ንጉሥ ሆነው ሸዋን ሲያስተዳድሩና ወደ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ ግዛት ሲያሰፉ የቆዩት ንጉሥ ምኒልክ፣

በ1881 ዓ.ም አጤ ዮሐንስ መተማ ላይ ከተሰው በኋላ የየግዛቱ ሹማምንት ለምኒልክ ታማኝነታቸውን በማሳየታቸው ምኒልክ ንጉሰ ነገሥት ለመሆን ምንም የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ሆኑ፡፡

 ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም ‹‹ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሱ፡፡

 ምኒልክ የውጫሌን ውል (‹‹Wuchale Treaty››) ተዋውለው አዲስ አበባ ከገቡ ከአራት ወራት በኋላ፣ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም በእንጦጦ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ ተቀብተው ‹‹ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሱ፡፡

ምኒልክ በነገሱ በሦስተኛው ቀን (ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም) ባለቤታቸው ጣይቱ ብጡል ‹‹እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የእቴጌነት ዘውድ ተደፋላቸው፡፡

የኢጣሊያውን ዲፕሎማት አንቶኔሊን ጣይቱ እንዲህ አሉት፡- “ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም!! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” ሲሉ ተናግረዋል። በሀገራቸው ሉዐላዊነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያደርጉ በትንታግ ንግግራቸው አሳውቀዋል።

. ታሪካዊው የጣይቱ ሆቴል ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀውም ከዛሬ 110 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 25 ቀን 1900 ዓ.ም) ነበር፡፡

‹‹(እቴጌ) ጣይቱ ሆቴል›› በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሆቴል መሆኑን በርካታ ድርሳናት መዝግበዋል፡፡ የሆቴሉ ግንባታ በነሀሴ ወር 1898 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ጥቅምት 25 ቀን 1900 ዓ.ም ተመርቆ መከፈቱን ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ፀሐፊ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በተባለው መጽሐፉ ይገልጻል፡፡

 በዘመኑ በነበረው ባህልና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ምክንያት በወቅቱ ሆቴል ከፍቶ ‹‹ገንዘብ ከፍላችሁ ምግብ ተመገቡ፤ መጠጥም ጠጡ›› ማለት፣ እንዲሁም ሆቴሉ እንኳን ቢገኝ ከፍሎ መመገብ እንደነውር የሚታይ በመሆኑ፣ ህዝቡም ሆነ መኳንንቱ ስለማይፈጽሙት ጉዳዩ ንጉሡን አጼ ምኒልክንም ሆነ እቴጌ ጣይቱን እጅጉን አሳስቧቸው ነበር፡፡ እናም ምኒልክና ጣይቱ ይህንን መፈጸም ነውር እንዳልሆነ በቅርባቸው ላሉ መኳንንት ከማስረዳት ባለፈ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነባሩን ባህልና ልማድ ባጠበቀ ማህበረሰብ ውስጥ አዲስ ባህልን መትከል ቀላል አይደለምና፡፡ የጳውሎስ ትረካ እንዲህ ይላል …

 ‹‹ … እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ፡፡ እንኳን ምግብ መብላት ይቅርና ከግሪኮች ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ መጠጣት ነውር ነበረና ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይሆን ጀመር፡፡

የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኩዋንንቶች ‹‹ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ›› ብለው ወሰዱዋቸው፡፡ መኳንንቱ ሁሉ በሉ ጠጡና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡

በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፡፡ እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለመሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሣ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡

 በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት ‹‹ሰማችሁ ወዳጆቼ … በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል›› ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ ‹‹እርስዎን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ›› እያሉ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዙ ጀመር፡፡

ገበያውም እየደራ ሄደ፡፡ ‹‹ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ›› የሚለው ሰው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ›› ይላል፡፡

ምንጮች፡

እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ከ1832 – 1910 ዓ.ም

፩. የኢትዮጵያ የአምስት ሺ ዓመታት ታሪክ ከኖህ – ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ – መጽሐፍ 1: ከኖህ – ዳግማዊ አጤ ምኒልክ (ፍስሃ ያዜ ካሳ)
፪. አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት (ተክለፃዲቅ መኩሪያ)

እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ በሕይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ እንድትቆይ ከማስቻል አልፈው … ለአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን (በተለይም ለወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች) በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ

Filed in: Amharic