>

“በጉሽ ጠላ እየተገፋ ስልጣን ለቅቄያለሁ ማለት አይሰራም” (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተመስርቶ ሳይውል ሳያድር ስልጣን መረከብ አለበት”

ተመስገን ቅዳሜ ጥቅምት 25/10 ከወጣው ሸገር ታይምስ መፅሄት ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የተወሰደ።

ተመስገን ደሳለኝ “የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ባስቸኳይ ይቋቋም” ብሎ ከተናገረው መካካል

ሀላፊነት የሚሰማቸው እና የሕዝብ አመኔታ ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶችን… ያሰባሰበ ‹‹የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› ተመስርቶ ሳይውል ሳያድር ሥልጣኑን መረከብ አለበት፡፡ ይሄ ሃሳብ በ1983 ወያኔ ወደ አዲስ አበባ ሲንደረደር አዛውንቱ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም አቅርበውት ከነበረው ‹‹የሽማግሌ መንግሥት›› ጋር ይመሳሰላል፡፡ ፕሮፍ ለነፃነት ታግለናል ብላችሁ እንደተንደረደራችሁ ስልጣን መያዝ አግባብ አይደለም፡፡ የሽማግሌ መንግስት ይቋቋም ሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ፓርቲ ተወዳድሮ ተአማኝና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ስልጣን ለሚይዝ አካል ይስጥ ብለው ነበር፡፡ መለስ ዜናዊና ጠመንጃ ነካሽ ጓደኞቹ ግን የታገሉት ለግል ስልጣን ስለነበር መንግስታዊ ኃላፊነቱን ይዘው ባለፉት 26 አመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ አደቀቁ፤ ህዝባችንን በሀይማኖትና በብሔር ከፋፍለው እነሆ እንዳንተማመን አደረጉ፡፡

ተመስገን ስለ “አብዮቱ” ከተናገረው መካካል

እኔና ጓዶቼ የታመንለት አብዮት እንደ ብሉይ አብዮት ጠብመንጃ ያነገበ አይደለም፡፡ በቀዘቃዛው ጦርነት ዘመን እንደነበረው አይደለም፡፡ የእኛ መንገድ በፊሊፒንስ ከተካሄደው የ1986ቱ (እ.ኤ.አ) የቀለም አብዮት ጋር የሚጋመድ ነው፡፡ የቀለም አብዮት ላይ ጠመንጃ የለም፤ መንግስት እንደሚለውም ጭራቅ አይደለም፡፡ በታሪክ ፀሀፊዎች የመጀመሪያው የቀለም አብዮት የተባለው የቢጫ አብዮት የሚል ስም የተሰጠው ፊሊፕንስ ውስጥ የተካሄደው ነው፡፡ ፈርዲናንድ ማርቆስ የተሰኘው አምባገነን መሪ በስልጣን ተሸንፎም ስልጣን አለቅም አለ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን አሰረ፡፡ ያኔ ወጣቶቹ መዲናዋን ማኒላን አጥለቀለቋት፡፡ መሪው ታንክ ቢያዘምትባቸውም ቢጫ አበባ ይዘው ለታንከኞቹና ለወታደሮቹ አጠለቁላቸው፡፡ ባለታንከኞቹ ከወጣቱ ጋር ተቀላቀለው ስርዓቱን ቀየሩ፡፡ ታሪክ ፀሀፊዎች የወጣቶቹን ቢጫ አበባ አይተው ‹‹ቢጫ አብዮት›› ብለው ጠሩት፤ የብርቱካን፣ የቡልዶዘር፣ የቬልቬት….. አብዮት እየተባለ ቀጠለ፡፡ ሆንግኮንግ ላይ ወደ አደባባይ የወጡ ሰዎች ዝናብ በመዝነቡ ጃንጥላ ይዘው ወጡ፤ ክስተቱን የተከታተሉ ፀሀፊዎችም ‹‹የጃንጥላ አብዮት›› ሲሉ ሰየሙት፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ‹‹የስካርፕ አብዮት›› ሊባል ይችል ይሆናል፤ ማን ያውቃል?

ታሪኩ ደሳለኝ

Filed in: Amharic